1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የገና በዓል አከባበር በጀርመን ፍራንክፈርት

እሑድ፣ ታኅሣሥ 29 2010

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባት እና " ትንሿ አዲስ አበባ " እየተባለች በምትሞካሸው የፍራንክፈርት ከተማ ላሉ ለብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን የዘንድሮው የገና በዓል በእረፍት ቀን መዋሉ ደስታን ፈጥሯል።

https://p.dw.com/p/2qSwy
Deutschland Äthiopisch-orthodoxe Tewahedo St. Immanuel-Kirche in Berlin
ምስል Leonard Bahr

የገና በዓል አከባበር በጀርመን ፍራንክፈርት

እንዲህ እንደዛሬው አውደ-ዓመት ሲመጣ በተለይም በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኖሩበት፣ ያደጉበት ባህል እና ወግ፤ ተካፍሎ መብላቱ፣ የወዳጅ ዘመድ እንዲሁም የሃገር ትዝታ ናፍቆቱ ሁሉ በእዝነ-ልቦናቸው ውልብ ማለቱ አይቀርም። ምንም እንኳ በግ እና ስጋ ማረዱ፣ የቄጠማ እና አሪቲ ጉዝጓዙ፣ ድፎ ዳቦ ሲጋገር አየሩን የሚያውደው የኮባ ቅጠል እና የኩበት ጭሱ ፣ በጋራ ባህላዊ ዘፈን እየዘፈኑ እና እየጨፈሩ ችቦ እና ደመራ ማብራቱ፣ የጾም መፈሰኪያ አክፋይ እና ስጦታ መለዋወጡ፣ የበዓል ገበያ ግርግሩ፣ የለመለመው ምድር እና የአየሩ የተፈጠሮ መዓዛ በተለይም በነጻነት አብሮ ማውካት መጫወቱ ቢቀርም እንደየሚኖሩበት ሃገር ባህል እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤ በጋራም ይሁን በተናጥል ቤት ያፈራውን አዘጋጅተው በዓሉን ማክበራቸው አይቀርም።

አንዳንዶቹ የኢትዮጵያ የሃይማኖት በዓላት ከጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በተለየ ቀን እንደሚከበሩ ይታወቃል።  በተለይም በስራ ቀናት ሲውሉ በዓሉን በተለየ ስሜት ለማክበር ትንሽ ከበድ ይላል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባት እና " ትንሿ አዲስ አበባ " እየተባለች በምትሞካሸው የፍራንክፈርት ከተማ ላሉ ለብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን የዘንድሮው የገና በዓል በእረፍት ቀን መዋሉ ደስታን ፈጥሯል። በዓሉ በሰንበት ቀን በመዋሉ በተለይም ጾመኛ የነበሩት ገና በማለዳው በሃገር ባህል ልብስ አምረው እና ተሸልመው፤ እንደ ሃገራችን ባህል ወደ አብያተ ክርስትያናት ልጆቻቸውን ይዘው በመሄድ፤ ሥርዓተ ቅዳሴ አስፈጽመው ተመልሰዋል።ከቅዳሴ በኋላም ለበአሉ ያዘጋጁትን ቤት ያፈራውን በያይነቱ የፍስግ ምግብ፣ ድፎ ዳቦ እና ጣፋጭ ኬኮች አቀራርበው እንዲሁም ባህላዊ ቡናቸውን አፍልተው፣ እጣናቸውን አጫጭሰው፣ ፈንድሻ እና ሌላም የቡና ቁርስ አሰናድተው፣ ሞቅ ደመቅ ባለ ስሜት እያከበሩ መሆናቸውን ነግረውናል። በስራቸው ልዩ ባህሪ ምክንያት የዛሬውን በዓል በስራ የሚያሳልፋ ኢትዮጵያውያንም መንገድ ላይ አጋጥመውናል።  ኑሮን ለማሸነፍ እና ሃገር ቤት የሚኖሩ ቤተሰቦቻችንን ለመርዳት በውጭው ዓለም ተግተን መስራት አለብን ምንም ምርጫ የለንም ብለውናል። 

30 Jahre Äthiopisch-Orthodoxe Kirche in Deutschland
ምስል Azeb Tadesse Hahn

እንደ ሃገራችን ሁሉ በውጭውም ዓለም ረጅም ዘመን ትውውቅ ያላቸው ጓደኛሞችና ቤተሰቦች በዓላትን በየተራ ቤታቸው እየደገሱ ተጠራርቶ በጋራ የማክበሩ ባህልም አሁን አሁን እየተለመደ መጥቷል። 

አውደ ዓመት ሲመጣ ባህል ሲከበር በተለይም በውጭው ዓለም ኑሮ በስራ የደከመን አዕምሮ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ዘና ማድረግ ተገቢ ቢሆንም በችግር አለንጋ የሚጠበሱ፣ የሚላስ የሚቀመስ ያጡ፣ ሃገር ቤት የሚገኙ ወገኖቻችንን ማስታወስ፣ ተካፍሎ መብላት እና እንደየአቅማችን መርዳትም ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን የሞራል ግዴታችንም ጭምር መሆኑን የገለጹልንም ነበሩ።

አብዛኛው ተራርቆ ቤቱን ቆልፎ ብቸኝነትን መርጦ የግል ህይወቱን በሚመራበት በውጭው ዓለም የተትረፈረፈ ምግብ አለ፤ ሙሉ ደስታ ግን የለም። እናም ዓውድ አመት ለእኔ ምንም የተለየ ትርጉም አይሰጠኝም ሲሉ የገለጹልን ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።

 

እንዳልካቸው ፈቃደ

ተስፋለም ወልደየስ