1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሮበርት ሙጋቤ መንግስት ደሞዝ መክፈል ተስኖታል

Eshete Bekeleረቡዕ፣ ሐምሌ 20 2008

ከዓለም የገንዘብ ድርጅት፤ ዓለም ባንክ እና የአፍሪቃ ልማት ባንክ የተበደረችውን 1.8 ቢሊዮን ዶላር ባቀደችው ጊዜ መክፈል የተሳናት ዚምባብዌ ከለት ወደ ለት ኤኮኖሚዋ እየተቃወሰ በመሄድ ላይ ይገኛል። ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ መክፈል የተሳነው የሮበርት ሙጋቤ አስተዳደር ከውጭ ምንዛሪ እጥረት በተጨማሪ የአደባባይ ተቃውሞዎችም እየገጠሙት ነው።

https://p.dw.com/p/1JWkO
Simbabwe Proteste in Harare
ምስል Getty Images/AFP/J. Njikizana

የገንዘብ እጥረትና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ በዚምባብዌ

ባለፈው ሐምሌ 21, 2016 የተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ኮንፈረንስ ይፋ ያደረገው 'የብድር ይዞታ እና የልማት ፋይናንስ በአፍሪቃ' የተሰኘ ዘገባ የአፍሪቃ አገራትን የብድር ሥጋት ዝቅተኛ፤መካከለኛ እና የከፋ ሲል በሶስት ይከፍለዋል። በጎርጎሮሳዊው ኅዳር 2015 ሥሌት መሰረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት አገሮች አነስተኛ የብድር ሥጋት ካለባቸው ጎራ ተመድበዋል። ደቡብ ሱዳን እና ማሊን የመሰሉ በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ውስጥ የሚዋዥቁ የአፍሪቃ አገሮችን ጨምሮ 20ዎቹ የዕዳ ሥጋታቸው መካከለኛ ነው። ጅቡቲ፤ጋና እና ቡሩንዲ ከሌሎች አራት አገሮች ጋር ከፍተኛ የዕዳ ስጋት እንዳለባቸው ዘገባው ይጠቁማል። ሁለቱ አገሮች ግን ከአበዳሪዎች የወሰዱትን ገንዘብ በአግባቡ ማስተዳደር እና መክፈል ተስኗቸው ከብድር ቀውስ ውስጥ ገብተዋል። ምሥራቅ አፍሪቃዊቷ ሱዳን እና የፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤዋ ዚምባብዌ

ዘገባው «የአፍሪቃ የውጭ ብድር ምጣኔ ሊገራ የሚችል» ቢሆንም መንግስታት ፈጣን የብድር እድገት ወደ ብድር ቀውስ እንዳያመራ እርምጃ መውሰድ አለባቸው ሲል አስጠንቅቋል። ይህ ግን ለሱዳን እና ዚምባብዌ የሚሆን አይመስልም።

10.8 ቢሊዮን ዶላር የአገር ውስጥ እና የውጭ እዳ ያለባት ዚምባብዌ ብድር ፍለጋ ብድር ለመክፈል የያዘችው እቅድ አልተሳካም። የፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ መንግስት ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ፤ የዓለም ባንክ እና የአፍሪቃ ልማት ባንክ የተበደረውን 1.8ቢሊዮንዶላር ባለፈው ሰኔ 30 ከፍሎ ሌላ ሊበደር አቅዶ ነበር። ዚምባብዌ 5.6ቢሊዮን ዶላር የመንግስት፤ 2.2ቢሊዮን ዶላር የዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት፤ 2.7ቢሊዮን ዶላር የፓሪስ አበዳሪዎች ቡድን እና 700ሚሊዮን ዶላር የሌሎች ብድር አቅራቢዎች እዳ እንዳለባት የዓለም ባንክ መረጃ ይጠቁማል። በአገሪቱ በዋናነት በመገበያያነት የሚያገለግለው የአሜሪካን ዶላር እጥረት መንግስት ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ ማዕቀብ እንዲጥል አስገድዶታል። ነጋዴዎች የዶላር እጥረት ገና ካሁኑ በሱቆቻቸው መደርደሪያዎች ላይ እየተስተዋለ እንደሆነ ያማርራሉ። አነስተኛ ነጋዴዎች ለአከፋፋዮች የሚከፍሉት አጥተዋል። የኃይማኖት መሪዎች እና የተቃውሞ ፖለቲከኞችን ጨምሮ የአገሪቱ ዜጎች አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ማሰማት ጀምረዋል። ወቅታዊው የኤኮኖሚ ምስቅልቅል ለዚምባብዌ ዜጎች ተቃውሞ ተጨማሪ ገፊ ምክንያት ሆኖ ይሆን? ሊይስል ሎው ቮድራን የአፍሪቃ የጸጥታ ጥናት ተቋም አማካሪ እና ተመራማሪ ናቸው።

Simbabwe Inflation
ምስል AFP/Getty Images

«ይመስለኛል።ባለፉት አመታት የተፈጠሩ ኩነቶችን ብንመለከት በማንኛውም ተቃውሞ ላይ በተለይም በ2008ቱ ምርጫ ወቅት በመንግስት ጥብቅ ቁጥጥር ምክንያት ቸልተኝነት ይስተዋል ነበር። በርካታ የዚምባብዌ ዜጎች አገሪቱን ጥለው ተሰደዋል። አሁን ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ባለመከፈሉ ምክንያት እና በአገሪቱ በተፈጠረው የከፋ ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ሰዎች ተሰላችተዋል።»

Simbabwe Proteste in Bulawayo
በዚምባብዌ ሁለተኛ ከተማ ቡላዋዮ እንስቶች ኤኬኖሚያዊ ቀውሱን ለማሳየት ባዶ ብረት ድስት ይዘው ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋልምስል Getty Images/AFP/Z. Auntony

የዚምባብዌ የመገበያያ ገንዘብ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ በፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ የሥልጣን ዘመን የከፋው ነው ይላሉ ተንታኞች። የሮበርት ሙጋቤ መንግስት ውጥረቱን ለመፍታት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ተጨማሪ ብድር ፍለጋ ላይ ነው። የዶላር እጥረትን ለመፍታት ባለፈው ግንቦት ወር አዲስ የግምጃ ቤት ሰነድ ጥቅም ላይ ለማዋልም ለዜጎቹ ቃል ገብቷል። ይህ ከሆነ የዚምባብዌ ዶላር በአሜሪካ ዶላር ከተተካ ከሰባት አመታት በኋላ ሐራሬ አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ይፋ ታደርጋለች ማለት ነው።

ገዢው ዛኑ ፒ.ኤፍ ፓርቲ የጉምቱውን መሪ ተተኪ ፍለጋ በሚዋትትበት ወቅት የተፈጠረውን ኤኮኖሚያዊ ቀውስ የአገሪቱ ፖለቲከኞች የተቆጣጠሩት አይመስልም።

«መንግስቱ የተተኪ ፍለጋው ላይ ያተኮረ ይመስላል። በእጁ ላይ ለሚገኙ ችግሮች ተገቢ እና ዘላቂ መፍትሔ እየፈለገ አይደለም። የጥሬ ገንዘብ እጥረቱን ለመፍታት የአጭር ጊዜ መፍትሔ እየፈለጉ ነው። ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አዲስ ብድር ለማግኘት ማመልከቻ አስገብተዋል። የፋይናንስ ሚኒስትሩም በተደጋጋሚ ወደ ለንደን ይመላለሳሉ። ለፖለቲካዊ ችግሮች ያበጁት መፍትሔ የለም። ገዢው የዛኑ ፒ.ኤፍ ፓርቲ ፕሬዝዳንቱን ለመተካት በሚደረገው ትንቅንቅላይ ተወጥሯል።» ይላሉ ሊዝል።

የዚምባብዌ ዜጎች መንግስት ግልጋሎት ላይ ሊያውለው ያቀደው አዲስ መገበያያ ኤኮኖሚያዊ ቀውሱን ለመፍታቱ ጥርጣሬ አላቸው ገበያው ላይ የተፈጠረው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ግን ከኤኮኖሚው ተሻግሮ ፖለቲካው ላይ የከፋ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። የዶይቼ ቬለ የሐራሬ ወኪል ሙስቫንሂሪ ፕሪቪሌጅ በአገሪቱ ተቀስቅሶ በነበረው ተቃውሞ ወቅት ያነጋገራቸው ወጣቶች መካከል አንዱ «በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የሥራ እድል የለም። በአገሪቱም ሙስና ተንሰራፍቷል።» ሲል ተናግሯል። «ከሥራ ገበታችን በመቅረት ለመንግስት ለውጥ እንደምንፈልግ እየተናገርን ነው። ለውጥ እንፈልጋለን። አንዳች መፍትሔ እንሻለን።» የሚል አስተያየትም ነበር።

በፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ እና መንግስታቸው ላይ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ከሚመሩት መካከል አንዱ የሆኑት ፓስተር ኢቫን ማዋሪሬ ለደቡብ አፍሪቃው ታይምስ ላይቭ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ «ዚምባብዌ ያለ ፕሬዝዳንቱ ምን ልትመስል እንደምትችል አላውቅም። ቢሆንም አማራጭ መፈለግ ይኖርብናል።» ሲሉ አገራቸው የገባችበትን አጣብቂኝ ተናግረዋል። ኢቫን ማዋሪሬ በመሩት ተቃውሞ ወጣቶች ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣን መውረድ አለባቸው የሚሉ መዝሙሮችን ዘምረዋል። አገራቸው ይፋ ሊያደርግ ያቀደውን አዲስ መገበያያም ነቅፈዋል። ኢቫን ማዋሪሬ የመንግስትን እቅድ በመተቸት ቀዳሚው ናቸው።

Evans Mawarire
ፓስተር ኢቫን ማዋሪሬምስል picture-alliance/AP Photo/T. Mukwazhi

«መንግስት የመገበያያ የግምጃ ቤት ሰነድ ይፋ ማድረግ ይፈልጋል። በአሁኑ ወቅት በዚምባብዌ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ገጥሞናል። እኛ ዜጎች የገንዘብ እጥረቱ የተፈጠረው በባለፉት አመታት በታየው የመግስት ብኩንነት የተፈጠረ ነው ብለን እናምናለን። አሁን በባንኮች ያስቀመጥንውን ገንዘብ አውጥተው ለራሳቸው ጥቅም ሊገለገሉበት ይፈልጋሉ። ይህ ስህተት ነው። ገንዘባችንን ወደ ባንክ መልሱ የመገበያያ የግምጃ ቤት ሰነድም ጥቅም ላይ አታውሉ የሚል መልዕክት እያስተላለፍን ነው። ምክንያቱም በ2008 ጥቅም ላይ ውለው እንደነበሩት ቼኮች ይህም ጥቅም አይኖረውም።»

የዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት የዚምባብዌ መንግስት ገቢ በ12በመቶ የቀነሰ ሲሆን ይህም መንግስት በግምጃ ቤት ሰነድ 245ሚሊዮን ዶላር (ከጠቅላላ አመታዊ የምርት መጠን 1.7 በመቶ) እንዲበደር አስገድዶታል። ለቀሪዎቹ የዓመቱ ወራት 600ሚሊዮን ዶላር ገቢ መሰብሰብ አሊያም የዛኑ ያክል መበደር ይኖርበታል። የመንግስት ሰራተኞች የሰኔ ወር ደሞዝ እና የጡረተኞች ክፍያ በሶስት ሳምንት ዘግይቷል። ተንታኟ ሊይስል ሎው መንግስት የአገሪቱን ጦር ደሞዝ ለመክፈል ጭምር መንገዳገዱን ይናገራሉ።

«መንግስት ለሰራተኛው በተለይም እጅግ አስፈላጊ ለሆነው ለአገሪቱ ጦር ደሞዝ መክፈል አለመቻሉን አምኖ ለመቀበል ተቸግሯል። ይህ ደግሞ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖበታል። በሰኔ ወር መጨረሻ የደሞዝ ክፍያ ተንገዳግዷል። ደሞዝ ለሁሉም ሰራተኛ ስለመዳረሱ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። በዚምባብዌ በመገበያያነት የሚያገለግለው የዩናይትድ ስቴትስ ዶላር አልቋል። አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የላትም። ምን አልባት ከደቡብ አፍሪቃ ምርቶች ማስገባት እንዲቆም ማድረጉ መንግስት ገንዘብ ከአገሪቱ እንዳይወጣ የሚያደርገው ሙከራ ምልክት ሊሆን ይችላል።»

Simbabwe Harare Robert Mugabe
የ92 አመቱ ሮበርት ሙጋቤ ዚምባብዌን ለ36 አመታት መርተዋልምስል picture-alliance/dpa/A. Ufumeli

የዚምባብዌ መንግስት የአሜሪካን ዶላር እጥረትን ለመፍታት የመገበያያ ካርዶችን ዜጎች እንዲጠቀሙ እያበረታታ ነው። ኩባንያዎች ሌሎች የውጭ ምንዛሪዎችን በተለይም የደቡብ አፍሪቃውን ራንድ ችግሩ እስኪቀረፍ እንዲገለገሉ ጠቁሟል። የፋይናንስ ሚኒስትሩ ፓትሪክ ቺናማሳ ቢሮ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ቢኖርበትም ዘግይቶም ቢሆን ደሞዝ መክፈል ችሏል። ይህ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታቱ ማስተማመኛ አይደለም። ጥያቄው ግን በሰኔ ወር መገባደጃ ምንም ገንዘብ ያልነበረው መንግስት ከሶስት ሳምንታት በኋላ ከየት አምጥቶ ደሞዝ ከፈለ? የሚለው ነው። ይህ ለሊዝል ሎው የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ነው።

«ይህ የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ይመስለኛል። ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ብድር ለማግኘት በሚደረገው ውይይት ዚምባብዌ መጀመሪያ ብድሯን መክፈል እንዳለባት ተወስኗል። ከዛ ከአፍሪቃ ልማት ባንክ እና ሌሎች አገሮች ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ታቅዷል። ዘገሪቱ እንዴት ብድሯን ከፍላ ሌላ ብድር እንደምታገኝ ግን ግልጽ አይደለም። መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ ደሞዝ ለመክፈል ይችል ይሆናል። ነገር ግን ይህ የሚሆነው ለጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት ብቻ ነው። ከዚያ አይበልጥም።»

ቀድሞም የማይወዷቸው ምዕራባውያን ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን ልጣቸው የራሰ መቃብራቸው የተማሰ አድርገው ይስሏቸዋል። አወዛጋቢውን ፖለቲከኛ በሰላ ብዕራቸው ሲተቿቸው የኖሩ የምዕራቡ መገናኛ ብዙኃን የቀብራቸው ዕለት የሚነብብ የሕይወት ታሪካቸውን ጽፈው አዘጋጅተዋል። የ92 አመቱ ሮበርት ሙጋቤም ዚምባብዌ የገባችበትን ኤኮኖሚያዊ ቀውስ መፍታት ስለመቻላቸው በርካቶች ጥርጣሬ አላቸው። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ ግን አገሪቱን ብድር በቃሽ እያሉ ነው።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ