1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጉግል መዋዕለ ንዋይ ፍሰት በአፍሪቃ 

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 13 2014

ጉግል አፍሪቃ ውስጥ በአራት ሃገራት መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ማቀዱ መነጋገሪያ ሆኗል። ሃሳቡን በአዎንታዊ የሚያዩት የመኖራቸውን ያህል ፤ ተገቢው ቅድመ ምርመራ ቢደረግ የሚመክሩም አሉ። በሌላ በኩል ሱዳን በተቃውሞ እየተናጠች ነው።

https://p.dw.com/p/424Hs
USA Google Büro in New York
ምስል Spencer Platt/Getty Images

ትኩረት በአፍሪቃ

ጉግል በአፍሪቃ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ መነሳቱ ተሰምቷል። በቅርቡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሳንደር ፒቻይ ይፋ ባደረጉት መሠረት ጎግል ለአምስት ዓመት በተለያዩ ዘርፎች አፍሪቃ ውስጥ አንድ ቢሊየን ዶላር ሥራ ላይ ለማዋል ተዘጋጅቷል። በዚህ የጉግል መርሃግብር ናይጀሪያ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ጋና ቀዳሚዎቹ ተጠቃሚ ሃገራት ይሆናሉ። ጉግል በእነዚህ ሃገራት የኢንተርኔት ግንኙነትን ከማስፋፋት በተጨማሪ በአነስተኛ ደረጃ ለተጀመሩ ሙከራዎች ድጋፍ አደርጋለሁ ብሏል።  

ይኽ የዓለማችን ቴክኒዎሎጂ ዘርፍ ግንባር ቀደም ተዋናይ ድርጅት አፍሪቃ ላይ ገንዘቡን ሥራ ላይ ለማዋል የመነሳቱ ዜና የተሰማው ቀጥተኛ የውጪ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት በመላው ዓለም ደረጃ በተቀዛቀዘበት በዚህ ወቅት መሆኑ ጥያቄዎችን አስነስቷል። የልማት ኤኮኖሚ ምሁር ለሆኑት ሹዋቡ ኢድሪስ ግን ጉግል የወሰደው ርምጃ አፍሪቃ እንደእሱ ባሉ ትላልቅ ኩባንያዎች እውነተኛ የሥራ አጋር ተደርጋ የመወሰዷ ማሳያ ነው።  

«እንደጉግል ያለ የዓለም ግዙፍ ኩባይና ስለአፍሪቃ ማሰቡ እና ገንዘቡን አፍሪቃ ውስጥ ሥራ ላይ ማዋል መፈለጉ፤ ብታውቀው የሚያስደስት ነገር ነው።» 

ጋናዊው የኢንተርኔት ቴክኒዎሎጂ ባለሙያ ማክሲሙስ አሜቶርጎ ግን የጉግል አፍሪቃ ውስጥ የመሥራት ዕቅድ በጥንቃቄ ሊፈተሽ ይገባል ባይ ናቸው። 

«ጥቅምና ጉዳቱን በወጉ መለካት አለብን፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉ የቴክኒዎሎጂ ጎልያዶች በትናንሽ ንግዶች ውስጥ ገንዘባቸውን ሥራ ላይ ያውሉና እነዚያን ትናንሾቹን ይውጧቸዋል፤ መለያቸውን ይወስዳሉ። እናም ለእነዚያ ጅምር ሥራዎች ዋጋ ከፍለው ስለሚወስዷቸውም፤ አፍሪቃ ወደተለመደ እርሻው ይመለሳል።»  

ሆኖም ጋናዊው የቴክኒዎሎጂ ምሁር የጎግል መዋዕለ ንዋዩን አፍሪቃ ውስጥ የማፍሰስ ሃሳብ ችግር እንዳለሆነ አጽንኦት ይሰጣሉ፤ ሆኖም የዚህ ገንዘብን ሥራ ላይ የማዋል የመጨረሻ ግብ ምንድነው? የሚለው በወጉ እንዲመረመር ያሳስባሉ። 

Data visualization Mobile Internet Africa - map price differences

«ለእኔ ባለቤትነት የሚባለው ነገር በጣም ዋነኛ ጉዳይ ነው። በየትኛውም መስክ መዋዕለ ንዋይ ቢያፈሱ በረዥም ጊዜ ሂደት ንብረትነቱ የአፍሪቃውያን ማለትም ሃሳቡን የጀመሩት ሰዎች ይሆናል ወይስ በጎግል በራሱ ይወሰዳል?» 

ሲሉም ይጠይቃሉ። ጥያቄያቸውም በዚህ አያበቃም። ጉግል እነዚያን ትናንሽ ጅምሮች ራሳቸውን ችለው ሥራውን አስፋፍተው እንዲቀጥሉ ያደርግ ይሆን የሚለውንም ያነሳሉ። 

«መቼ ይሆን ራሳቸውን ችለው እንዲሠሩ ይለቋቸዋል ወይንስ በራሳቸው ስልት ውስጥ ውጠው ይይዟቸውና አፍሪቃ የእነዚህ ሃሳቦች እና እሴቶች መገኛ ማሕጸን ብቻ ሆና ያላትን ለግዙፉ የቴክኒዎሎጂ ተቋም አስረክባ ከዚህ የሚገኘውን ጥቅም ታጣለች? ከዚያም አህጉሪቱ እንደገና ሁሉንም እንደአዲስ እንድትጀምር ትደረጋለች?» 

መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ከውጭ ርዳታ ከመቀበል የተሻለ እንደሆነ የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። የፖለቲካ ተንታኙ አኮ ጆን አኮ ዕዳ ለበዛባት አፍሪቃ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የውጭ መዋዕለ ነዋይ ፍሰት ይበጃል ባይ ናቸው።  

«አንድ ኩባንያ መጥቶ ሊፈጥራቸው ለሚችላቸው የሥራ ዕድሎች ፍላጎት አለ። በዚህ ረገድም ከውጭ ርዳታ ይልቅ ከውጭ የሚመጣ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት የበለጠ ይረዳል። ከዚህ አንጻርም የውጭ ርዳታ የበለጠ ዕዳ ነው፤ ሆኖም በውጭ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት አፍሪቃውያን ይጠቀማሉ።» 

UK Google Büro London
ምስል Hannah McKay/REUTERS

ሹዋቡ ኢድሪስ ይህን ሃሳብ አይቀበሉም። ወደኋላ መለስ ብለውም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አውሮጳ ከገባበት የኤኮኖሚ ውድቀት ለመውጣት መዋዕለ ንዋይ ፍሰትን መጠቀሙን ያስታውሳሉ። እንደእሳቸው አገላለጽም ከምዕራቡ ዓለም ጋር ከነበራት አሳዛኝ ታሪክ ጋር በተገናኘም የውጭ መዋዕለ ነዋይ ፍሰትንም ሆነ የውጭ ርዳታን መመዘኑ ለአፍሪቃ አስፈላጊ ነው። 

 «እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አውሮጳውያኑ ሃገራት እንደ ግሪክ፣ ጣሊያን እንዲሁም ሌሎችም በኤኮኖሚ ደካማ ናቸው፤ ሆኖም በርዳታ እና በውጭ መዋዕለ ነዋይ ፍሰት አሁን አውሮጳ ከደረሰችበት ለማድረስ ችለዋል። ለአፍሪቃም ምናልባትም ግዙፍ ቀጥተኛ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትም ሆነ ከፍተኛ ርዳታ ለማግኘት ከአሁን የተሻለ ጊዜ አይኖርም።» 

ኢድሪስ በእርግጥም ባለፉት ሁለት ምዕተ ዓመታት በቅኝ አገዛዝ እና በባርያ ንግድ መዘዝ እጅግ የተጎዳችው አፍሪቃ ይኽን ማግኘት ይገባታልም ብለው ያምናሉ። እንደተገለጸው አፍሪቃ ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ ሥራ ላይ ለማዋል የተነሳው ጎግል ቅድሚያ የሚሰጣቸው የኢንተርኔት ግንኙነትን ማስፋፋት እና የተጀመሩ ትናንሽ የቴክኒዎሎጂ ሥራዎችን ማጠናከርን ያካትታል። ጆን አኮ ደግሞ በዚህ መርሃግብር ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገባቸው ዋነኞቹ መካከል የኢንተርኔት ቴክኒዎሎጂ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት ቢካተት እንደሚበጅ ያስረዳሉ።  

«እንዲህ ያሉ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰቶችን ለመሳብ ቀዳሚው የኢንተርኔት ቴክኒዎሎጂ እውቀትን ማዳበር ነው። ለዚህ ደግሞ ትምህርት ቤቶች ያስፈልጋሉ። ይታያችሁ ካሜሮን ውስጥ ያለን እንዲህ ያለ ዩኒቨርሲቲ አንድ ብቻ ነው፤ አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራት ደግሞ ጭራሽ አንድም የላቸው።»  

እንደኢድሪስ ያሉ የዘርፉ ምሁራን ደግሞ በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በኩል ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው አህጉሪቱ በአብዛኛው ጥቅም የምታገንበት እንዲሆን የእርሻ እና ማዕድን ማውጫው ዘርፍ መሆን አለበት ባይ ናቸው።  

BG Konzerne mit den höchsten Profiten 2020 | Alphabet |Sundar Pichai
የጎግል ሥራ አስኪያጅምስል Fabrice Coffrini/AFP

«የሆነ ሸቀጥ አምርቶ በጥሬው ወደውጪ መላክ ብቻ አይደለም። በእርሻው ረገድ የሚኖረው የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ከማምረት እና ማከማቸት አንስቶ ወደሌላ ምርትነት ሂደት ውስጥ አሳልፎ ወደ ውጭ እስከመላ መሆን አለበት። በእኔ እምነት እነዚህ ናቸው በአፍሪቃ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባው።» 

ለአፍሪቃ የቱ ይበጃል የሚለው እንዲህ ያሉት የተለያዩ አስተያየቶች እንዳሉ ሆነው ከጉግል የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ዕቅድ ከማሳካቱ አንጻር ሌሎች ተግዳሮቶችም አሉ። ከእነዚህ መካከልም ሥር የሰደዱ የፖለቲካ ችግሮች እንዲሁም የማክሮ ኤኮኖሚው አለመረጋጋት፣ ሙስና፣ ደካማው መሠረተ ልማት እና መጥፎ አስተዳደርን ተቋቁሞ መንቀሳቀስ ግዙፉን የቴክኒዎሎጂ ኩባንያ ይጠብቁታል። ኢድሪስ ግን መፍትሄ ስላለው በተለይ ሙስና ያን ያህል እንደ እንቅፋት ሊታይ አይገባም ባይ ናቸው። 

«የሰው ኃይልን በሚመለከት በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት የሰለጠነ ወጣት ትውልድ አላቸው። እነዚህን ቀጥሮ ማሰልጠን እንዲሁም በቂ ደሞዝ መክፈል ከተቻለ፤ አብዛኛው የተለመደው የሙስና ሂደት ይወገዳል።» 

ጋናዊው አሜቶርጎ ግን ጉግል ሊያጋጥመው የሚችለው ትልቁ ተግዳሮች ከአፍሪቃውያን ችግር ጋር እጅግም አይገናኝም ነው የሚሉት። ይልቁንም ሚዛናዊነት ካጣው ዓለም አቀፍ ስርዓት ጋር ይበልጥ ይያያዛል። ከምንም በላይም ዋናው ስጋት ያሉትን መዋቅሮች ጎግል ምን ያኽል ይቆጣጠራቸውል የሚለው ያሳስባቸዋል።  

«ጎግል በዓለም ትልቁ መረጃ የመፈለጊያ ስልት ነው። ዩትዩብ የእነሱ ነው፤ ይኽም ሁለተኛው ትልቅ ዘርፍ ነው። የእኔ ስጋት ያተሳበው ሁሉ እስኪከናወን ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል? በዚያም ላይ ናይጀሪያ እና ሌሎች ቦታዎች ላይም የኢንተርኔት ክፍያ በ21 በመቶ እንዲቀንስ ለማድረግ ይፈልጋሉ። እነዚህ ሃሳቦች ተግባራዊ እና ዘላቂ እንዲሆኑ ደግሞ ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር መሥራት ይኖርባቸዋል።» 

Symbolbild - Ägyptisches Pfund - und US Dollar Währung
ምስል picture-alliance/F. El-Geziry

ጉግል በአፍሪቃ ለማካሄድ ስላሰበው የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ጉዳይ ይፋ ማድረጉ ይኽን መሰሉን ጥያቄ ቢያስነሳም ሲልከን ቫሊ የሚገኘው ግዙፍ ተቋም ከ54 የአህጉሪቱ ሃገራት ለጊዜ ያተኮረው አራት ሃገራት ላይ ባቻ ነው። ኩባንያው ዕቅዱን ካላሰፋ መዋዕለ ንዋይ ፍሰቱ በመላው አፍሪቃ የሚኖረው ተጽዕኖ አናሳ እንደሆነ ነው አሜቶርጎ ያመለከቱት።  

«ለአፍሪቃ ከዚህ ከፍ ያለ ሚዛን መስጠት ካልቻለ ወይንም ደግሞ እነሱ ያተኮሩባቸው አራት ሃገራት ብቻ በመሆናቸው፤ አፍሪቃ ውስጥ ይኽ ምን ዓይነት መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል የሚለው አይታየኝም።» 

የልማት ኤኮኖሚ ምሁሩ ኢድሪስ በበኩላቸው ይኽ የጎግል የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ከአንዳንድ ሃገራት ስፋት አኳያ ሲታይ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያመጣ እንደሚችል ያስባሉ።

«ለምሳሌ ናይጀሪያን ብንወስድ 210 ሚሊየን ሕዝብ አላት። ከ210 ሚሊየን ውስጥ 60 በመቶው ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች ነው። ናይጀሪያ ላይ መዋዕለ ንዋይ ስታፈስ በ16ቱ የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ትብብር አባል ሃገራት ውስጥ ገንዘብህን ለሥራ እንደማዋል ነው።» 

ዝሆን በመባል የሚታወቀው ግዙፉ የኢንተርኔት ቴክኒዎሎጂ ኩባንያ ጉግል አሜሪካን ውስጥ በጎርጎሪሳዮው 2020 ዓ,ም በገበያው ዋጋ አንድ ትሪሊየን ዶላር ያስመዘገበ ሦስተኛ ኩባንያ ነው። እናም የፖለቲካ ተንታኙ አኮ ጆን አኮ ኩባንያውን የሚያንቀሳቅሰው የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ትርፍ ነው ባይ ናቸው። እንዲህ ያሉ ኩባንያዎች ደግሞ ትርፍ ወደሌለበት ፈጽመው እንደማይሄዱም አጽንኦት ይሰጣሉ። እናም በኢንዶ አሜሪካው የዘርፉ የንግድ ሰው ፒቻይ ሳንደርራጃን ወይም በስፋት በሚጠሩበት ሳንደር ፒቻይ ሥራ አስኪያጅነት የሚንቀሳቀሰው ጉግል በአፍሪቃ አራት ሃገራት መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ መዘጋጀቱ አንድም ለትርፍ አንድም በአፍሪቃውያን የተወጠኑ ጅምር የዘርፉን ሥራዎች ለማበልጸግ ወይስ ለመዋጥ የሚለው የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል። 

ተቃውሞ የተቀጣጠለባት ሱዳን  

በዚህ ሳምንት ሲዳን ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ አስተናግዳለች። የተቃውሞ ሰልፉን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ «የከፋ እና እጅግ አደገኛ ቀውስ» ብለውታል። ተቃውሞው አምባገነኑ ኦማር አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ ከጎርጎሪዮሳዊው 2019 ወዲህ የታየ በመላው የሀገሪቱ ክፍል ብዙዎች የተሳተፉበት የሕዝብ ቅሬታ ነው። ሐሙስ ዕለት ከተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ ዋና ዋናዎቹ ወታደራዊ አገዛዝን እንደሚቃወሙ በይፋ ድምጻቸውን አሰምተዋል። በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ  ጦሩ ሥልጣኑን እንዲረከብ የሚጠይቅ ሰልፍ ተካሂዷል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የተለያዩ ሱዳንን የተመለከቱ ትንታኔዎችን የጻፉት በብሪታንያ የሱዛክስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው ዳን ዋትሰን ይኽ ሁሉ ወደ ጥፋት ያመራል ይላሉ። 

Sudan I Protest in Khartoum
ተቃውሞ በካርቱምምስል Marwan Ali/AP/picture alliance

«የሱዳን ፖለቲካ እንደቼዝ ጨዋታ ነው፤ ሁሉም ተጫዋዎች እኩል ዕድል ሳይኖራቸው የተወሰኑት አምስት ርምጃ ወደፊት የሚሄዱበት አይነት።»  

ራሳቸው የጦር መኮንን የነበሩት የቀድሞው የሱዳን መሪ ኦማር አልበሽር በኃይል ከሥልጣን እስኪወገዱ ድረስ ለ30 ዓመታት ገዝተዋል። በመፈንቅለ መንግሥቱ ወቅት በመጀመሪያ አካባቢ ጦሩ ሥልጣኑን ለማስረከብ ፈቃደኛ አልነበረም። ሆኖም የሕዝቡ ከፍተኛ ተቃውሞ እየተጠናከረ በመሄዱ በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ ለመሳተፍ ተስማማ። የሲቪል ኃይሎች ተካተውበትም የሽግግር ሂደቱ ተጀመረ።  የሽግግር መንግሥቱ ምርጫ እስኪካሄድ እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2023 ዓ,ም ድረስ እንዲቆይ ነበር የታሰበው። ሆኖም በሲቪሉ እና በወታደራዊው ኃይሎች መካከል ልዩነት እና ከፍተኛ ፉክክር እያደገ መጣ። አሁን የሚታየው ችግር መነሻው መስከረም ላይ የተሞከረው ወታደራዊ መፍንቀለ መንግሥት መሆኑ ይታሰባል። ለዋትሰን ግን የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ተአማኒነቱ አናሳ ነው። 

«ሆኖም መፈንቅ መንግሥት ሙከራው ብዙም ተአማኒነት ያለው አይመስልም። በርካታ ሰዎች ቀደም ብሎ በጦር ኃይሉ የተፈጠረ ወይም የተደረገ ነው ብለው ያምናሉ።» 

የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ከአልበሽር ጋር አብሮ የኖረ እንደውም በርካቶች ተባባሪዎቻቸውን የያዘ ስብስብ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋልም ባይ ናቸው። «ሙስ እና ጥቃት በሱዳንን የኤኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ እንደትልቅ መሣሪያ እንደሚያገለግሉ፤ ፖለቲካዊ ወታደሪዊ አመራሩም ገቢና ሀብቶችን እንዲሰበስብ እንደሚፈቅዱ» በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የሱዳንን የፖለቲካ ገበያ አስመልክቶ በለንደን ስኩል ኦፍ ኤኮኖሚክስ ተመራማሪዎች የተካሄደ ጥናት ይፋ አድርጓል። በ2018 ተቃዋሚዎች ሙስናው እንዲቆም እና ይኽን የሚያስተካክል ማኅበራዊ ኮሚቴ እንዲቋቋምም ጥሪ አቅርበው ነበር። የተለወጠ ነገር ግን የለም። የሐሙሱ ተቃውሞ እንዳመለከተውም የአልበሽርን ሥርዓት ያወገዘው ተመሳሳይ ድምጽ አሁንም እየተሰማ ነው።

Polen Kriegsschiffe der chinesischen Marine
ምስል picture-alliance/dpa/A. Warzawa

በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ ሕጎችን እና በአንጃነት የቆሙ ቡድኖችን በተመለከተ ስምምነት የለም። በዚያም ላይ የሱዳንን ወሳኝ ወደብ እየዘጉ በሀገሪቱ የአስፈላጊ ነገሮች እጥረት ያስከተሉ ጎሳዎች አሉ። የፋይናንስ ማሻሻያው የባሰ የኤኮኖሚ ውጥረት እና ግሽበትን አስከትሏል። ባለፈው ዓመት ከአማጺ ቡድኖች ጋር የሰላም ስምምነት ቢደረስም ላለፉት 12 ወራት በፖለቲካ አመጽ ምክንያት የሚሞተው ሰው ቁጥር ጨምሯል። ከከተማ ውጭ ያሉ በአልበሽር ሥርዓት ውስጥ የየአካባቢው መሪዎች የነበሩት ወገኖች ዴሞክራሲን ፍለጋ የሚካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች የእነሱን ሥልጣናት ለመጋፋት እንደሆነ እንደሚያስቡት ያመለከቱት ሌላው የሱዳን ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አሌክስ ደ ዋል፤ ወደብ የመዝጋቱ ችግር ከዚህ ጋር መያያዙን ያመለክታሉ። በዚህ መሃል ግን ተስፋ እንዳልጨለመ የሚናገሩም አሉ። ከዚህ ቀደም በሱዳን የተካሄዱ ሽግግሮች በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች ቢቋጩም አሁን ግን ጦሩ ይኽን አላደርግም ብሏል። ያመነው ያለ ግን አይመስልም። አሌክስ ደ ዋል «ጦሩ የሀገሪቱ ሕዝብ ሆነ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብን ማሞኘት አይችልም፤» ይላሉ፤ እናም ሁሉም ጨዋታውን በማወቁ ይቋቋማቸዋል፤ አሁንም ይኽንኑ እያደረገ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ሸዋዬ ለገሠ