1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጊኒ ቢሳው ምርጫ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 6 2006

ጊኒ ቢሳው ውስጥ አጠቃላዩ ምርጫ እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን፥ 2006 ዓም ሲካሄድ ዋለ። የሀገሪቱ ሕዝብ እአአ በ2012 ዓም መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ ወዲህ አንድ ሕጋዊ መንግሥት እንዲመሠረት ሲጠብቅ ነው የቆየው። ለብዙ ጊዜ ሲተላለፍ በቆየው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ

https://p.dw.com/p/1Bgi5
Wahl Guinea-Bissau 2014
ምስል SEYLLOU/AFP/Getty Images

በዕጩነት ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች መካከል አራቱ ደህና የማሸነፍ ዕድል እንዳላቸው ይነገራል። በጊኒ ቢሳው እአአ በ1991 ዓም የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከተዋወቀ ወዲህ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ፣ እስከ ጥቂት ጊዜ በፊት ድረስ በሰፊው ሕዝብ ዘንድ ያን ያህል ታዋቂ ያልነበሩት አራቱ ዕጩዎች ይወዳደራሉ፣ ከነዚህም የተወገደው መንግሥት የገንዘብ ሚንስትር የነበሩት ኾዜ ማርዮ ቫዝ የቀድሞውን የነፃነት ፓርቲ በምሕፃሩ፣ ፔይጄክን ይወክላሉ። የፔይጄክ አባል የሆኑት የምጣኔ ሀብት ጠቢብ ፓውሎ ጎሜሽ በነፃ ተወዳዳሪነት ቀርበዋል። ኑኖ ናቢያም እና አቤል ኢንካዳ ደግሞ የማህበራዊው ህዳሴ ፓርቲ ዕጩዎች ናቸው።

Wahl Guinea-Bissau 2014
ምስል SEYLLOU/AFP/Getty Images

በወቅቱ የሀገሪቱን የሽግግር መንግሥት የሚመሩት ፕሬዚደንት ማኑዌል ሴሪፎ በምርጫ አልተዋዳደሩም። ከሥልጣን የተወገደው መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት እና አሁን በፖርቱጋል/ኬፕ ቬርዴ በስደት የሚኖሩት ካርሎስ ጎሜሽ ጁንየርም በምርጫው አልተሳተፉም፣ እንደሚታወሰው፣ መፈንቅለ መንግሥቱ በተካሄደበት ጊዜ ሊደረግ በነበረው ሁለተኛ ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ ጎሜሽ ደህና የማሸነፍ ዕድል ነበራቸው።

በአሁኑ ጊዜ አንድ የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት ድርጅት፣ ኤኮዋስ ሰላም አስከባሪ ጓድ በሀገሪቱ ቢሠማራም፣ በጀነራል ኢንዲዣይ የሚመራው የሀገሪቱ ጦር መኮንኖች አሁንም ትልቅ ተፅዕኖ እንዳሳረፉ ነው።

የገንዘብ ሚንስትር በነበሩበት ጊዜ የመንግሥት ገንዘብ አባክነዋል በሚል የቀረበባቸውን ወቀሳ ያጣጣሉት ኾዜ ማርዮ ቫዝ ከ2012 ዓም ወዲህ ሀገሪቱ የምትገኝበትን አዳጋች የኤኮኖሚ ችግር ለማስወገዱ ተግባር ቅድሚያ እንደሚሰጡ በምርጫው ዘመቻ ወቅት አመልክተዋል።

« የሀገራችንን ኤኮኖሚ ማጠናከር እና የሀገራችንን ኤኮኖሚ እንደገና ማነቃቃት፣ እንዲሁም፣ የስራ ቦታ መፍጠር የተሰኙት ዋነኛ ትኩረቴ የሚያርፍባቸው ይሆናሉ። »

ፓውል ጎሜሽም ልክ እንደ ቫዝ ኤኮኖሚውን በማሳደግ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻሉ ተገባር ላይ እንደሚያተኩሩ ነው የገለጹት።

Präsidentschaftswahl in Guinea-Bissau 2014
ምስል DW/Braima Darame

በ3ኛው ዕጩ አቤል ንካዳ አንፃር በቀድሞው ፕሬዚዳንት ኩምባ ያላ የሚደገፉት የፓርቲያቸው አቻ ኑኖ ናቢያም ደህና ዕድል እንዳላቸው ታዛቢዎች ይናገራሉ። ከዚህ ሌላም ከጦሩ ጀነራልም ጋ ያላቸው ቅርበት ከሀገሪቱ ሕዝብ መካከል አንድ ሦስተኛውን የሚሸፍኑትን በብዛት ከባላንታ ጎሣ የሚወለዱትን የጦር ኃይል አባላትን ድምፅ እንደሚያስገኝላቸው ይገመታል። ኑኖ ናቢያ የፀጥታውን ሥርዓት እንደሚያሻሽሉ አስታውቀዋል።

« የፀጥታውን ዘርፍ ማሻሻል አስፈላጊ ነው ብየ አስባለሁ። ግን የተሀድሶው ለውጥ በሚገባ መጤን ይኖርበታል። ውይይትም ሊደረግበት ይገባል። »

ምርጫውን ከአፍሪቃ ህብረት ፣ ከምሥራቅ ቲሞር እና ከኒውዚላንድ የተውጣጡ 550 ታዛቢዎች ይከታተሉታል።

በምርጫው አንዱም ዕጩ አስፈላጊውን ድምፅ ካላገኘ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ቦታዎች የሚይዙት ዕጩዎች እአአ ግንቦት 18፣ 2014 ዓም ለመለያ ምርጫ ይወዳደራሉ። ሀገሪቱ እአአ በ1974 ዓም ከፖርቱጋል ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ ሥልጣን ከያዙት አሥሩ የሀገሪቱ ፕሬዚደንቶች መካከል አንዱም ሙሉ የሥልጣን ዘመኑን አጠናቆ አያውቅም።

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ