1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጊኒ ወታደሮች በሲቭሎች ላይ የፈጸሙት ግድያ፣

ማክሰኞ፣ መስከረም 19 2002

በምዕራብ አፍሪዊቷ ሀገር፣ በጊኒ መዲና በኮናክሪ የተቃውሞ ፓርቲ የፖለቲካ ስብሰባ ባካሄደበት እስታዲየም የወታደራዊው መንግሥት ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች በሩምታ ተኩስ፣ ቁጥራቸው ከ 157 የማያንስ ሲቭሎችን መግደላቸውን ፣ የአገሪቱ የሰብአዊ መብት ተማጓች ቡድን ፕሬዚዳንት ቲርኖ ማጁ ሶው አስታወቁ ።

https://p.dw.com/p/JtcG
በኮናክሪ እስታዲየም፣ ተሰብስበው በነበሩ 50 ሺ ያህል የተቃውሞ ፓርቲ ደጋፊዎች ላይ ሩምታ ተኩስ ተከፍቶ ከ 157 የማያንሱ ሰዎች እንዲገደሉ ትእዛዝ የሰጡት የጥቂት የጦር መኮንኖች መንግሥት(«ሁንታ» ) መሪ ፣ ሻምበል ሙሳ ዳዲስ ካማራ፣ምስል AP

በምዕራብ አፍሪዊቷ ሀገር፣ በጊኒ መዲና በኮናክሪ የተቃውሞ ፓርቲ የፖለቲካ ስብሰባ ባካሄደበት እስታዲየም የቆሰሉትም ከ 1250 በላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ ሙን፣ እንዲሁም የዩናይትድ እስቴትስ መንግሥት ፣ የአያሌ ሰዎች ህይወት መጥፋት መቁሰልና የንብረትም መውደም እጅግ እንዳስደነገጣቸው ነው የገለጡት። የ አውሮፓው ኅብረትም ፣ በፊናው ድርጊቱን አውግዟል። ተክሌ የኋላ--

ጊኒ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ፣ እ ጎ አ መስከረም 28 ቀን 1958 ዓ ም ነጻ የወጣችበትን ቀን ለማስታወስ፣ መስከረም 28 እየተባለ በሚጠራው እስታዲየም ትናንት 50 ሺ የሚሆኑ የተቃውሞው ወገን ደጋፊዎች ተሰብስበው የፖለቲካ ንግግር በማደመጥ ላይ ሳሉ ነበረ፣ ባፈው ዓመት በታኅሳስ ወር በወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ሥልጣን የጨበጡት የሻምበል ሙሳ ዳዲስ ካማራታማኝ ፀጥታ አስከባሪዎች እሩምታ ተኩስ ከፍተው፣ ቢያንስ 157 ሰው የረፈረፉት። የጊኒ ዴሞክራቲክ ኃይሎች ኅብረት የተሰኘው ዋናው የተቃውሞ ፓርቲ መሪ Cellu Diallo ከሌሎች የፖለቲካ ትግል ከሚያራምዱ ወገኖች ጋር ተይዘው ታሥረዋል። ሌሎች የተቃውሞው ወገን መሪዎች ድብደባ ደርሶባቸዋል። ወታደሮቹ ስለፈጸሙት ተግባር ፣ ስለግድያውና ድብደባው፣ ከጊኒ የተቃውሞው ወገን የአመራራር አባላት መካከል፣ ሙክታር ዲያሎ፣ እንዲህ ነው ያስረዱት።

«በየአቅጣጫው ነበረ የሚተኩሱት፣ በዱላ ድብደባ አካሂደዋል። ሴቶችን አስገድደው ደፍረዋል። ሰዎች በየቦታው ተረፍርፈው ይታዩ ነበር። እኛም የፓርቲ መሪዎች፣ ተደብድበን በጠና ነው የቆሰልን። የ«ሁንታ»ው መሪ ባስተላለፉት ትእዛዝ መሠረት በአንድ አንድ የጤና ጣቢያ እንድንሰባሰብ አድርገዋል። የሞቱት ከ 100 በላይ ናቸው።»

ሙክታር ዲያሎ ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ የዐይን ምሥክሮችና የህክምና ሠራተኞችም፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዳስታወቁት፣ በጥይት ከተገደሉት ሌላ፣ በቢላዋና በሳንጃ እየተወጉ የቆሰሉ ሰዎችም ጥቂቶች አይደሉም። የፖለቲካ ዲስኩር በተደረገበት እስታዲየም የተገኙ ሴቶችም ልብሳቸው በወታደሮች እየተቀደደ፣ መደብደባቸውንና መደፈራቸውን ራሳቸው የግፍ እርምጃው ሰለባዎችና የዐይን ምሥክሮች ቃላቸውን ሰጥተዋል።

በጊኒ ኮናክሪ ፣ የምርጫ ሥርዓትን በተመለከተ ለአንድ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት የሚሠሩት Elizabeth Cote የተባሉት ሴትዮ ፣ «ያን መሰል የኃይል እርምጃ መወገዝ አለበት » ነው ያሉት።

«የተወሰዱት እርምጃዎች በአርግጥ መወገዝ አለባቸው። ይሁንና አሁን እንደሚመስለኝ ጠቃሚው ጉዳይ፣ መንግሥታት በመላ ድርጊቱን ማውገዛቸው ነው። በተጨማሪም፣ ሸምጋዮች በመሆን ጊኒን መርዳት ይጠበቅባቸዋል። በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እንዲካሄድና አገሪቱ በዴሞክራሲ ጎዳና መራመድ የምትችልበት እርምጃ እንዲንቀሳቀስ ማገዝ ይኖርባቸዋል።»

ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ጊኒ በተፈጥሮ ሀብት ብትታደልም በድኅነት እጅግ ከተጎሣቆሉት አገሮች የምትመደብ ናት። ይህችው ሀገር እ ጎ አ በ1958 ዓ ም ነጻነቷ።ን ከተጎናጸፈችበት ጊዜ አንስቶ፣ በፈላጭ ቆራጭ፣ ጨካኝና በሙስና በተዘፈቁ ገዥዎች ሥር ስትማቅቅ መኖሯ የሚታበል አይደለም። ባለፈው ዓመት በታኅሳስ ወር እርስ በርስ የተመራረጡ ጥቂት የጦር መኮንኖች፣ 24 ዓመታት አገሪቱን የገዙት የቀድሞውፕሬዚዳንት ላንዛና ኮንቴ ካረፉ በኋላ፣ ለቡድናቸው የዴሞክራሲና ልማት ብሔራዊ ም/ቤት የሚል ስያሜ በመስጠት፣በጉልበት ሥልጣን ጨበጡ። ባለፉት 9 ወራት፣ ይኸው የጥቂት የጦር መኮንኖች መንግሥት «ሁንታ» ፣ ፈላጭ- ቆራጭነት አልተለየውም። ካማራ የበላይነቱን ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ፣ በ 2009 ማለትም ዘንድሮ ምርጫ ይካሄዳል ሲሉ ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን ፣ እርሳቸውም ሆኑ የምክር ቤታቸው አባላት ለፕሬዚዳንትነት እጩ ሆነው እንደማይቀርቡም አስታውቀው ነበር። ይሁንና ጊዜው እንዲገፋ ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ፣ የውጭ መንግሥታት ባደረጉባቸው ተጽእኖ፣ ባለፈው ነሐሴ 11 ቀን 2001 ዓ ም፣ እ ጎ አ ጥር 31 ቀን 2010 ዓ ም ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይካሄዳል ሲሉ አስታውቀው ነበር፣ የምውጥ መኮንኖቹ መንግሥት መሪ የሆነው ሆኖ ቃላቸውን በማጠፍ ለፕሬዚዳንትነት እወዳደራለሁ በማለታቸው፣ ከህዝቡ በኩል ላቅ ያለ ጥላቻን ነው እያተረፉ የመጡት።

በትናንቱ ዕለትም ለጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ትእዛዝ በመስጠት የጭካኔና የግፍ ተግባር እንዲፈጸም አድርገዋል። የጊኒ የጭቆና አገዛዝ ታሪክ አላከተመም።

ተክሌ የኋላ/አርያም ተክሌ፣