1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጋምቤላ ታፍነዉ የተወሰዱት ሕጻናት ጉዳይ

ረቡዕ፣ መጋቢት 6 2009

ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን በጎን እና በጆር ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ዉስጥ ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በጣሉት ጥቃት ከአስራ ስምንት ሰዎች በላይ መገደላቸዉንና ከ 22 በላይ ሕጻናት ታግተው መወሰዳቸውን ተቀማጭነቱን ለንደን ላይ ያደረገዉ «አኝዋ ሰርቫይቫል» የተሰኘዉ ድርጅት ገለፀ።

https://p.dw.com/p/2ZENH
Äthiopien Pressebilder Anywaa Survival Organisation
ምስል Anywaa Survival Organisation/Nyikaw Ochalla

Gambela_Kindesentfüh rung und Gewalt in Gambella, Äthiopien/mmt - MP3-Stereo

«አኝዋ ሰርቫይቫል» የተሰኘዉ የጋምቤላ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መንግሥት ምንም አይነት ርምጃ አለመዉሰዱን ገልፀዋል። የአካባቢዉ ነዋሪዎች በበኩላቸዉ ታጣቂዎቹ በየጊዜዉ ጥቃት በመጣል ልጆቻችንን አፍነዉ ሲወስዱ መንግሥት ድርድር ይካሄድ ከማለት በስተቀር ርምጃ ለመዉሰድ እና አካባቢዉን ከጥቃት ለመከላከል ዝግጁ አይደለም ሲሉ ያማርራሉ። የጋምቤላ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሕጻናቱን ለማግኘት ጥረት ላይ መሆኑን ተናግሯል። 

«አኝዋ ሰርቫይቫል» የተባለዉ የጋምቤላ ሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት ለዶቼቬለ በላከው መረጃ  መሰረት ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሊ ታጣቂዎች መጋቢት አንድ ምሽት ላይ በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን ጉድ ወረዳ ኦባዋ ቀበሌ ባደረሱት ጥቃት ነዋሪዎችን ገድለዋል ህጻናትንም አፍነው ወስደዋል ። መንግሥት ምንም አይነት ርምጃ ባለመውሰዱ ታጣቂዎቹ ከአንድ ቀን በኋላ የመንግሥት የጥበቃ ኃይላት ብዙም ሳይርቁ በሚገኙበት ጆር ወረዳ አንጌላ ቀበሌ በከባድ መሣሪያዎች ተጨማሪ ሰዎችን ገድለዋል ፣ሕጻናትም አፍነዉ ወስደዋል ንብረትም አውድመዋል ሲሉ የድርጅት ሃላፊ ኒኪያዉ ኦቻላ ገልፀዋል።

Äthiopien Pressebilder Anywaa Survival Organisation
ምስል Anywaa Survival Organisation/Nyikaw Ochalla

«በመጀመርያ ደረጃ የካቲት ወር አካባቢ ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ታጣቂዎች ኦትዊልን በማጥቃት ስምንት ሰዎችን ገድለዋል። ከዝያ በኋላ 18 የሚሆኑ ሕጻናትን አፍነዉ ወስደዋል። ይሄ የመጀመርያ ጊዜ አid,ለም። ነገርግን በከፍ መልኩ ሁለትቀን ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ኣ,ንጌላና ኦባዋ በሚባል ተከታታይ ጥቃት ሰንዝረዋል። በዚህ ወቅት በአንጌላ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ አራት ሕጻናት ታፍነዉ ተወስደዋል።  ኦባዋ ላይም በከፍ መልኩ ንብረቶች ወድመዋል፤ መንደር በአጠቃላይ ተቃጥሎአል፤ በዝያ ወቅe የሞቱት ሰዎች ከ 18 በላይ ይሆናሉ የሚል መረጃ ነዉ የደረሰን። 22 ሕጻናቶች ታፍነዉ ተወስደዋል፤ እስካሁን ግን የመንግሥት ምላሽ ይህ ነዉ ማለት አይቻልም። ዝምታዉ ለምን እንደሆነ የሚገርም ነገር ነዉ።»

በእሁድ እለቱ ጥቃት ከ 60 በላይ መኖርያ ቤቶች መቃጠላቸዉን በጋምቤላ አስተዳደር የዉኃና ፍሳሽ አገልግሎት ኃላፊ ፔተር ገብርኤል ገልፀዋል።

« በርግጥ እሁድ እለት ማታ ኦባዋ በሚባል ቀበሌ የሙርሊ ታጣቂዎች ወደ 13 የሚሆኑ ሰዎች ሞተዋል ፤ 21 የሚሆኑ ሕጻናት ታፍነዉ በሞርሊ ተወስደዋል። 60 የሚሆኑ ቤቶች ተቃጥለዋል።  ነገሩ አሳዛን ነዉ።» ከደቡብ ሱዳን የሚመጡት የሙርሊ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደም ያደረሱት ጥቃት ያስታወሱት የአኝዋ ሰርቫይቫል ድርጅት ሃላፊ ኒኪያዉ ኦቻላ መንግስት ስለ ባለፈዉ ሳምንቱ ጥቃትና ስለ ታፈኑት ሕጻናት ጉዳይ የገለፀዉ ነገር የለም ይላሉ ።

« በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን እስካሁን ስለ ጋምቤላ ስለአኝዋክ ብሔረሰብ የሞቱ ሰዎችና የታፈኑ ሕጻናቶች በምን አይነት መንገድ ወደ ቤተሰቦቻቸዉ እንደሚመለሱ መንግሥት ያወጣዉ መግለጫ የለም። እና ይህ ትንሽ ሃላፊነት የጎደለዉ አካሄድ ነዉ ብዬ ነዉ የማምነዉ።» ይህን ችግር በድርድር ከመፍታት ይልቅ መንግሥት ርምጃ ቢወስድ ታጣቂዎች ወደ ቦታዉ ዳግም ባልመጡ ነበር ያሉት፤ በጋምቤላ አስተዳደር የዉኃና ፍሳሽ አገልግሎት ኃላፊ ፒተር ገብርኤል ነዋሪዉ የመንግሥትን ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

« የሙርሊ ታጣቂ ሃይል ከደቡብ ሱዳን ነዉ የሚመጡት ፤ ለምን መንግሥት ዝም ይላል? ለምን ርምጃ አይወስድም? ተደራጅተዉና ድንበርን አቋርጠዉ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ሲገባ እርምጃ አለመዉሰዳቸዉ ነዉ። ሁልጊዜ የሚደረግላቸዉ ድርድር ነዉ፤ ስለዚህ በሙርሊ ላይ ርምጃ ካልተወሰደ ጥቃታቸዉን መቼም አይተዉም። ሕዝቡ አሁን ተሰዶ ሜዳ ላይ ነዉ ያለዉ ። ስለዚህ የመንግሥት ቁጥጥር ላልቶአል።   የድንበር አዋሳኝ በሆኑ የጋምቤላ አካባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር እየሰራ መሆኑን የገለፁት በጋምቤላ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኦሞት ኦቶዎ በበኩላቸዉ ፤ ሁኔታዉ በመረጋጋት ላይ ነዉ፤ የመንግሥት ሰራዊት እየተከታተለ ነዉ። » ከሃያ በላይ ታፍነዉ የተወሰዱት ሕጻናትስ ጉዳይ እንዴት ነዉ? « ሕጻናቱ ያሉበት ቦታ አይታወቅም ገና አልተገኙም» ባለፈዉም ጊዜ ከ መቶ በላይ ሕጻናት ታፍነዉ ተወስደዉ ነበር 90 ሕጻናት ተመልሰዉ 40 ሕጻናት ቀርተዋል። አሁን ግን የታፈኑት ሕጻናት 22 ናቸዉ። አዲስ ነገር ካገኘን ይፋ እንናገራለን።»  

Äthiopien Pressebilder Anywaa Survival Organisation
ምስል Anywaa Survival Organisation/Nyikaw Ochalla

መንደር ቀዉድመዉ ሕጻናትን እያፈኑ ወስደዉ የሚሸጡት የሞርሊ ታጣቂዎች ቀደም ባሉት ዓመታት የቀንድ ከብትን ለመዝረፍ ብቻ ነበር ሲሉ በጋምቤላ አስተዳደር የዉኃና ፍሳሽ አገልግሎት ኃላፊ ፒተር ገብርኤል ተናግረዋል።  

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ