1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋሪሳው ጥቃት አንደኛ ዓመት

ዓርብ፣ መጋቢት 23 2008

በኬንያው የጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ላይ የአሸባብ ታጣቂዎች ጥቃት ከጣሉ ነገ አንድ ዓመት ይሆነዋል ። ምንም እንኳን ዩኒቨርስቲው ባለፈው ጥር ሥራ ቢጀምርም ተማሪዎች አሁንም ከፍርሃት አልተላቀቁም ። ብዙዎቹ እንደሚሉት ያን አሰቃቂ አደጋ በቀላሉ ሊረሱት አልቻሉም ።

https://p.dw.com/p/1INq5
Kenia Garissa Universität Eingang Sicherheitskräfte
ምስል Imago/Xinhua

ኬንያ ከዌስትጌቱ የገበያ ማዕከል አደጋ ሳታገግም የደረሰው የጋሪሳው ጥቃት በኬንያ ምድር በአሸባሪዎች ከተጣለ አደጋ የብዙ ሰዎች ህይወት የጠፋበት ነው ።
በጎርጎሮሳዊው ሚያዚያ 2 ፣2015 ዓም የአሸባብ ታጣቂዎች አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የሆኑ 147 ሰዎችን የገደሉበት ሰሜን ምሥራቅ ኬንያ የሚገኘው የጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተጠግኖ እንደገና ከተከፈተ ሦስት ወር ይጠጋል ። ጥቃቱ ከደረሰ ከአንድ ዓመት በኋላ የጋሪሳ ዩኒቨርስቲ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ወደ ዚያ የተጓዘው የየዶቼቬለው አንድሪው ዋሲኬ እንደዘገበው የእሩምታ ተኩስ የተከፈተበት የዩኒቨርስቲው የተማሪዎች መኝታ ክፍል በሚገኝበት ህንፃ ዙርያ ለሞቱት መታሰቢያ ዛፎች ተተክለዋል ።የዶቼቬለው አንድሪው ዋሲኬ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ግን አሁንም የዛሬ ዓመቱን ጥቃት የሚያስታውሱ በጥይት የተመቱ መስኮቶች ግድግዳዎች ይታያሉ ። የጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ዳይሬክተር አህመድ ኦስማን ዋርፋ ያኔ የሆነውን ሲያስታውሱ
«መስጊድ ሄጄ ፀሎት ማድረስ ነበረብኝ ። ሆኖም ወደ እዚያ እንዳልሄድ ስሜቴ ስለነገረኝ ቤቴ ፀለይኩ ። ወንበር ላይ ቁጭ ብዬ የመጀመሪያውን ጥይት ድምፅ ሰማሁ ። ሰዎቹ በዚህ አድርገው በኮሪደሩ አለፉ ።በስተግራ በኩል የክርስቲያን ህብረት የተባለው ማህበር ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች በመፀለይ ላይ ነበሩ ። ታጣቂዎቹ የመጀመሪያዎቹን 12 ተማሪዎች የገደሉት እዚያ ነው ።»
ዋርፋ ስለ ጥቃቱ ሳያስቡ የቀሩበት አንድም ቀን የለም ። ፓሊስና ጦር ሠራዊት ሲመጣ የሟቾች ቁጥር ይቀንሳል የሚል እምነት ነበራቸው ።ግምታቸው ስህተት መሆኑን የተረዱት ግን ኋላ ላይ ነው ።
«ጦር ሠራዊቱ ራሱ ዘልቆ ከመግባት ይልቅ በርቀት ደጋግሞ ይተኩስ ነበር ።ሦስት ወይም አራት ወታደሮች ሰዎችን ለማዳን ቢገቡ ይቀል ነበር ።ሆኖም ያን አላደረጉም ። ይህ ደግሞ እኔን በእጅጉ አስደንግጦኛል ። »
ከትምህርት ቤቱ በግማሽ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የኬንያ ጦር ሰፈር እያለ ፣ወታደሮች አደጋው ወደ ደረሰበት የጋሪሳው ዩኒቨርስቲ ዘግይተው መምጣታቸው የኬንያ ባለሥልጣናትን ክፉኛ አስተችቷል ።ከጥቃቱ በኋላ በርካታ ነጋዴዎች አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል ።147 ሰዎች ከሞቱበት አደጋ ከተረፉት መካከል አንዳንዶቹ እስካሁን የምክር አገልግሎት እየተሰጣቸው ነው ። አደጋው ባስከተለው የስነ ልቦና ችግር ምክንያት ተመልሰው ወደ ዩኒቨርስቲው ያልመጡም አሉ ።
«ከተማሪዎቹ አብዛኛዎቹ ወደ ሞይ ዩኒቨርስቲ ተዛውረዋል ። ብዙ የምክር አገልግሎት ተሰጥቷል ። አሁንም የምክር አገልግሎት የሚሰጣቸው አሉ ። ቀላል አይደለም ። የሆነው ቀላል ነገር አይደለም ። አንዳንዶች ደግሞ በስነ ልቦና ችግር ምክንያት ተመልሰው መምጣት አልቻሉም ። ሆኖም አሁን አብዛኛዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል ።የ24 ዓመትዋ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ሶፍያ ኑር ሶይያን ከአደጋው ከተረፉት አንዷ ናት ። በአደጋው ህይወታቸን ያጡትን ምን ጊዜም አንረሳቸውም ትላለች ።
«ትምህርታችንን ቀጥለናል ። በርካታ ተማሪዎች ተመልሰው መጥተው ትምህርታቸውን ቀጥለዋል ። በአደጋው ህይወታቸው ያለፈ ብዙ ጓደኞች አሉኝ ። በሆነው ስሜታችን እጅግ በጣም ተነክቷል ። በየቀኑ እናስታውሳቸዋለን ። »
ከጥቃቱ በኋላ በዩኒቨርስቲው ፖሊስ ጣቢያ ተቋቁሟል ። ጣቢያው 25 ከባድ መሣሪያ የታጠቁ ፖሊሶች አሉት ። በግቢው ዙሪያ አስፈላጊ የሆኑት መብራቶች ተተክለዋል የዩኒቨርስቲው ተማሪ ፋይሰል አደን እንደሚለው አሁን የጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ፀጥታ ጥበቃ አያሰጋውም ።
«የፀጥታ ጥበቃው መጠናከር በአካባቢው ያለውን ስሜት ቀይሯል ። የአካባቢው ነዋሪዎችም ጠንካራ የፀጥታ ጥበቃ እንደሚካሄድ ያውቃሉ ። ለሊትም ብዙ እንቅስቃሴ የለም ። »
ወደፊት ደግሞ ግቢውን በግንብ ለማጠር ታስቧል ።

Kenia Garissa Universität Anschlag Faisal Aden
ምስል DW/A. Wasike
Kenia Garissa Universität Anschlag Mohammed Farouk
ምስል DW/A. Wasike

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ