የጋና አጠቃላይ ምርጫ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 29 2005
ለከፍተኛው የሀገሪቱ ሥልጣን ስድስት ዕጩዎች በተወዳዳሪነት ቢቀርቡም፡ ዕድል አላቸው የሚባሉት ሁለት ተወዳዳሪዎች የብሄራዊው ዴሞክራቲክ ኮንግረስ መሪና የወቅቱ ፕሬዚደንት ጆን ድራማኒ ማሃማ፡ እንዲሁም የተቃውሞው የአዲሱ አርበኞች ፓርቲ መሪ ናና አኩፎ አዶ ናቸው። የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ጆን አታ ሚልስ ባለፈው ሐምሌ ድንገት ከሞቱ በኋላ በዚያን ወቅት ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት ሥልጣኑን የያዙት ማሃማ በዚሁ ሥልጣን ለመቆየት ጠንካራ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን፡ ተፎካካሪያቸው እና እአአ በ 2008 ዓም በተካሄደው ምርጫ በጆን አታ ሚልስ በጠባብ የድምፅ ብልጫ የተሸነፉት ናና አኩፎ አዶ ዕድላቸውን ዘንድሮ እንደገና ሞክረዋል።
የብሄራዊው ዴሞክራቲክ ኮንግረስ እና የተቃውሞው የአዲሱ አርበኞች ፓርቲ፡ ሁለቱም በምክር ቤታዊው እና በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ድል ለመቀዳጀት ይችሉ ዘንድ ባለፉት ወራት ጠንካራ የምርጫ ዘመቻ ነበር ያካሄዱት። በሁለተኛዋ ትልቋ የጋና ከተማ ኩማዚ የሚገኙት የአዲሱ አርበኞች ፓርቲ የወጣቶች ቡድን አስተባባሪ ሀቢቡ ሱዋላሂ ለምሳሌ ፓርቲያቸው ለድል ለማብቃት ያለፉትን ሦስት ወራት ያላሰለሰ የቅስቀሳ ስራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል። ሱዋላሂ በተለይ በከተማይቱ ዋነኛ የገበያ ቦታ በመዘዋወር ባለመደብሮች የብሄራዊ አርበኞች ፓርቲን እንዲመርጡ ሲያግባባ ነው የከረመው።
« በብሄራዊ አርበኞች ፓርቲ የሚመራ መንግሥት እንዲቋቋም ነው የምንፈልገው፤ ሕዝቡ የሚፈልገውን ያውቃሉና። ሥልጣን በምትይዝበት ጊዜ ሕዝቡን የሚጠቅም፡ ለምሳሌ፡ የጤና መድን ዋስትና ለሁሉም ተደራሽ ማድረግና ለወጣቱ የሥራ ቦታ መፍጠርን የመሳሰሉ ተግባራትን እውን ማድረግ ይኖርባሀል። »
የአዲሱ አርበኞች ፓርቲ ጠንካራ ሠፈር በምትባለው እና የአሻንቲ ሕዝብ በሚኖርባት ኩማዚ እና አካባቢዋ የፓርቲው ዕጩ ናና አኩፎ አዶ ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ 72 ከመቶ የመራጩን ድምጽ ነበር ያገኙት። በዘንድሮውም ምርጫ በዚሁ አካባቢ የብዙኃኑን ድምፅ ማግኘታቸው እንደማይቀር ነው የሚጠበቀው። ይሁንና፡ በጠቅላላው የምርጫ ውጤት ላይ በ 30,000 የመራጭ ድምፅ ልዩነት በተፎካካሪያቸው ጆን አታ ሚልስ መሸነፋቸው ይታወሳል። በምርጫው ዘመቻ ወቅት ሁለቱም ተወዳዳሪዎች ማሀማኒ እና አዶ ተመሳሳይ አጀንዳ ይዘው ነበር የተንቀሳቀሱት። ምክንያቱም፡ ባለፉት ዓመታት የጋና ሕዝብ በዓለም ሦስተኛ የካካዎ እና የነዳጅ ዘይት አምራች ከሆነችው የሀገሩ የተፈጥሮ ሀብት ገቢ ተጠቃሚ አልሆነም። በዚሁ ረገድ ገና ብዙ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚገባውና በሀገሪቱም አስፈላጊውን የማሻሻል ርምጃ የማነቃቃት የተሻለ ችሎታ እንዳላቸው ወቅታዊው ፕሬዚደንት ገልጸዋል።
« የመፀዳጃውን ዘርፍ በማስተካከሉ ረገድ ጠቃሚ ፖሊሲ አለመነደፉ እና ይህን የሚያዘጋጅ ጠንካራ ተቋም አልተገነባም። በሚቀጥለው ሣምንት ማብቂያ ላይ ያካባቢ ልማት ሚንስቴር አንድ ብሔራዊ የቆሻሻ ማስወገጃ እና የመፀዳጃ መርሀግብር ይፋ ያደርጋል። »
ትምህርት፡ ጤና ጥበቃ ፡ ብልፅግና የተሰኙትን ጉዳዮች በተመለከተ ሁለቱ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ዕጩዎች ሊያደርጉት በገቡት ቃል መካከል ብዙም ልዩነት አልታየም። ማሀማ እና አዶ ከሀገሪቱ የነዳጅ ዘይት እና የካካዎ ሽያጭ የሚገኘውን ግዙፍ ገቢ የትምህርቱን እና የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻያ እንደሚጠቀሙበት ቃል ገብተዋል። እርግጥ፡ ጋና በምዕራብ አፍሪቃ ካሉት ጎረቤቶችዋ በጉልህ በተሻለ ደረጃ ላይ ብትገኝም፡ አሁንም በመልማት ላይ ከሚገኙት ሀገራት መደዳ ነው የምትመደበው። 182 ሀገራትን የተመለከተው የተመድ የልማት ዕድገት ሠንጠረዥ እንደሚያሳይ፡ ይህችው የምዕራብ አፍሪቃ ሀገር 152 ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በሀገሪቱ ሙስና አሁንም አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆን ይገኛል። መንበሩን ጀርመን ያደረገው የሙስናን ደረጃ የሚመረምረው ድርጅት « ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል » 176 ሀገራትን አወዳድሮ ከጥቂት ቀናት በፊት ባወጣው ዓመታዊ ሠንጠረዡ፡ ጋና 64 ነጥቦችን በማግኘት 49 ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ጋና በአፍሪቃ አስተማማኙ መረጋጋት የሰፈነባት ሀገር ናት። ባለፉት በርካታ ዓመታት ሥልጣኑን የሀገሪቱ አመራር በብሔራዊ ዴሞክራቲክ ኮንግረስ እና በአዲሱ የአርበኞች ፓርቲ መካከል በሰላማዊ መንገድ ሲሸጋገር ታይቶባታል ሲሉ በኩራት ይናገራሉ።
« ምርጫ ስናካሂድ የመጀመሪያችን አይደለም። ከአምስት የሚበልጡ ምርጫዎች ተካሂደዋል። እና፡ በርግጥ፡ ይህም ምርጫ ይሳካል፤ ። »
የትናንቱ አጠቃላይ ምርጫ አሸናፊ የሚታወቅበት ይፋ ውጤት በነገው ዕለት ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። ማሃማኒ እና አዶ የምርጫውን ውጤት በፀጋ እንደሚቀበሉ ከወዲሁ አስታውቀዋል። በምርጫው አንዱም ዕጩ 50% ካላገኘ እአአ የፊታችን ታህሳስ 28 የመለያው ምርጫ ይካሄዳል።
ዳንየል ፔልስ/አርያም ተክሌ
መሥፍን መኮንን