1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋዜጠኞች ስጋት በመቃዲሾ

ሰኞ፣ ጥቅምት 11 2000

የሶማሊያ መዲና መቃዲሾ ለጋዜጠኞች እጅግ አስጊ ስፍራ እየሆነች መሄዷ ተገለጠ። በመዲናዋ ጠንካራ እንቅስቃሴ ያደርጋል የሚባልለት የሸበሌ ራዲዮ ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ ባለፈዉ ዓርብ በመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደሉም ስጋቱን ከፍ አድርጎታል።

https://p.dw.com/p/E0Y3
ጠብ መንጃና መቃዲሾ
ጠብ መንጃና መቃዲሾምስል AP

በራዲዮ፤ ቴሌቪዥንና ኢንተርኔት መረብ መረጃ የሚያሰራጨዉ የሸበሌ ሚዲያ ባልደረቦች እንደሚናገሩት በተደጋጋሚ የግድያ ዛቻ ይሰነዘርባቸዋል። የመዲናዋ የፀጥታ ሁኔታ በተናጋ ቁጥርም የጥቃት ኢላማ ሆነዋል። በዚህ ሰበብም በርካታ ሶማሊያዉያን ጋዜጠኞች አገር ለቀዉ ለመሰደድ፤ ቢኖሩም ለመሸሸግ ተገደዋል።

በሺር ኑር ጌዲ የራዲዮ ሸበሌ ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ በተለይ በራዲዮዉ ቅፅር ግቢ ሲገኝ እጅግ ደስተኛ ይሆን ነበር ይላሉ ባልደረቦቹ። ጋዜጠኝነት ግን ሰላም በራቃት፤ ሃይ ባይ በሌለባት፤ ወገን ከጠላት ለመለየት ባዳገተባት በመቃዲሾ በደስታ የሚከዉኑት ሙያ መሆኑ ቀርቶ በእሳት ጨዋታ ከሆነ ወራት ተቆጥረዋል።

በሺር ኑር ጌዲ ደስታን በሚያገኝበት የስራ ቦታዉ መመለስ እንደማይችል ሆኖ ነዉ ባለፈዉ ዓርብ ባልታወቀ ታጣቂ ጥይት ህይወቱ ያለፈችዉ። ቀብሩ ትናንት ተፀፈመ። ራዲዮ ሸበሌም ለሶስት ቀናት ሃዘን ስራዉን አቆመ። የሸበሌ ኔት ኢንተርኔት ድረገፅ ሃላፊ ባቡል ኑርና ሌሎች ባልደረቦቸቸዉ ሃዘንና ድንጋጤ ናይ ቢሆኑም አሁን አካባቢዉ ረጭ ብሏል ይላሉ፤


«ሁኔታዉ አሁን የተረጋጋ ነዉ። እንደምታዉቁት ዓርብ ዕለት ያልታወቁ ታጣቂዎች አለቃችንን ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ በሺር ኑር ጌዲን ገድለዉታል። ትናንት በመዲናዋ ቀብረናል። አሁን ሃዘን ላይ ነን። ዋና ሃላፊያችን አብዱልማሊክ ዩሱፍ ማህመድ የመገናኛ ብዙሃኑ ለሶስት ቀናት በሃዘኑ ምክንያት እንዲዘጋ አዞናል። ነገ ስራ እንጀምራለን።»


በጋዜጠኞቹ ላይ ተደጋጋሚ የሚደርሰዉ ዛቻ ባለፈዉ ሳምንት ማለቂያ ሃላፊያቸዉ ላይ ተግባራዊ ሆኗል። ድርጊቱን የኮነነዉ የጋዜጠኞች መብት ተከላካይ ኮሚቴ በምህፃሩ CPJ እንደሚለዉ ሌሎቹ የስራ ባልደረቦቹም ስጋት ተባብሷል። በሺርኑር ጌዲ የተገደለዉ ከስራዉ ወደቤቱ ሲሄድ በመሆኑ በወቅቱ በርካታ የስራ ባልደረቦቹ የራዲዮዉንቅፅር ግቢ ለቀዉ መዉጣት አልቻሉም። አደጋዉ ከፊታቸዉ በተጋረጠበት ሁኔታ ነገ እንደተገመተዉ የራዲዮዉ ዘጋቢዎች ስራ ላይ ይገኛሉ ብሎ መገመት ይቻል ይሆኖ? ባቡል ኑር፣


«በርግጥ ሁኔታዉ ለመስራት የሚደፈርበት አይመስልም። ምክንያቱም ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ዛቻ ይደርሰናል። በየዕለቱ ነዉ የግድያ ማስፈራሪያዉ የሚደርሰን። እናም ነገሩ በርግጥም ለመስራት የሚያመች አይደለም።»


ብሌራዊ የሶማሊያ ጋዜጠኞች ህብረት አባል የሆነዉ አብዱልራሺድ አብዱላሂ ሃይደር እንደገለፀልን በከተማዋ በተለይ ማታ ማታ ከባድ የተኩስ ልዉዉጥ አለ። ጋዜጠኞችም እለት በዕለት ዛቻ እንደሚደርስባቸዉ ለህብረቱ ያመለክታሉ። ሁኔታዉ የተባባሰ በሚመስልበት እንዲህ ባለዉ ወቅት በመዲናይቱ በጋዜጠኝነት ተግባር መግፋት ይቻል ይሆን? ባቡል ኑር


«በርግጥ በመዲናዋ መቃዲሾ ከባድ ዉጥረት መኖሩ ይታወቃል። በርካታ ጋዜጠኞችም ከአገር እየተሰደዱ ነዉ። በተለይ ደግሞ አብዛኛዎቹ ከሆርን አፍሪክና ከሸበሌ ራዲዮ ናቸዉ። አሁንም አንዳንድ ባልደረቦቻችን በዚሁ ችግር ሳቢያ መዲናዋን ለመልቀቅ አስበዋል።»


በሶማሊያ ጋዜጠኞ እሚደርስባቸዉን ጥቃት፤ ወከባና ዛቻ ለጋዜጠኞች መብት የሚቆሙ ዓለም ዓቀፍ ተሰሚነት ያላቸዉ ተቋማት ማዉገዛቸዉን ቀጥለዋል። ስጋቱ ደግሞ የሶማሊያ ጋዜጠኞችን በመዲናዋ አላላዉስ ብሏል። ባቡል ኑር ይህን ማብራሪያ ለዶቼ ቬለ ሲሰጥ ከራዲዮ ጣቢያዉ ህንፃ መዉጣት አለመቻሉን ነዉ የገለፀልን፤


«በመዲናዋ የተረጋጋ ሁኔታ የለንም። እኔ ራሴ አሁን የማዋራሽ በሸበሌ ሚዲያ ማዕከል ህንፃ ዉስጥ ነኝ። ለደህንነታችን ካለዉ ስጋት የተነሳ መዉጣት አይቻልም። አየሽ እኔና የዘጋቢዎች የበላይ እስከ አሁን ህንፃዉ ዉስጥ ነን። መዉጣት አንችልም። ምክንያቱም ለደህንነታችን ያሰጋናል። መቃዲሾ ዉስጥ ከሁለቱም ወገን ጫናዉና ወከባዉ ይሰማናል። በዚህ ሁኔታ መስራት የሚቻል አይመስልም።»


ሁለቱ ከዓርብ ጀምረዉ በራዲዮ ጣቢያዉ ህንፃ ዉስጥ ሲወሰኑ ሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸዉ ደግሞ በየስፍራዉ ቤታቸዉን ጨምሮ ለመደበቅ ተገደዋል።