1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋዜጠኞች ፈተና በሶማሊያ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 14 2006

ሶማሊያ ዉስጥ ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ተይዘዉ ከነበሩ ጋዜጠኞች አብዛኞቹ ሲለቀቁ በእስር ላይ የሚገኙት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸዉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ተሟጋች ድርጅት አመለከተ።

https://p.dw.com/p/1CyCn
Symbolbild Zeitungen in Ketten
ምስል Vladimir Voronin - Fotolia.com

የሶማሊያ ጋዜጠኞች የገና ዳቦ ብጤ መሆናቸዉ እየታየ ነዉ። መንግሥት ግጭት የሚያነሳሳ ዘገባ አቀረባችሁ በሚል በአንድ ወገን ይከሳቸዋል፤ ያስራል አለፍ ሲልም ሚስጥር በማዉጣጣት ሰበብ ድብደባ ይፈጽምባቸዋል። ሀገሪቱን በማተራመስ የሚከሰሰዉ ታጣቂ ቡድን አሸባብም በበኩሉ ለባዕዳን ገባሪዎች፤ ለመንግሥት ተብዬዉ አዳሪዎች እያለ በጠራራ ፀሐይ ጎዳና ላይ በጥይት ይደፋቸዋል፤ ከራራም ያግታቸዋል። እንዲህም ሆኖ የሀገሪቱ ጋዜጠኞች ሥራቸዉን ቀጥለዉ ነበር። በተለይ እስካለፈዉ ሳምንት ድረስ በዜጎቹ ተደማጭነት እንዳለዉ የሚነገረዉ ሸበሌ ራዲዮና SKY FM በዚሁ ተግባር ቀጥለዉ ቆይተዋል። ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ ግን በሸበሌ የመገናኛ ብዙሃን ጥላ ሥር ለሚገኙት ለሁለቱ ራዲዮ ጋዜጠኞች ከባድ ነበር። 19 ጋዜጠኞችና ሌሎች ሠራተኞች በሶማሊያ ብሔራዊ የስለላ ተቋም ኃይሎች ተያዙ። ራዲዮዎቹም ተዘጉ። ከታሠሩት አብዛኞቹ ከሁለት ቀናት በኋላ ሲለቀቁ የራዲዮዎቹ ባለቤት አብዲማሊክ ዩሱፍ መሐሙድ፤ የራዲዮ ሸበሌ ዋና አዘጋጅ አህመድ አብዲ ሀሰን እንዲሁም የSKY FM ዳይሬክተር መሐሙድ መሐመድ ዳሂር እስካሁን በእስር ላይ ናቸዉ።

Symbolbild Medienfreiheit
ምስል Fotolia/Serggod

ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች RSF ይፋ ባደረገዉ ዘገባ ጋዜጠኞቹ ከባድ የቁም ስቅል እንደተፈጸመባቸዉ የጸጥታ ኃይሎችን ጨምሮ በርካታ እማኞች፣ መግለጻቸዉን አመልክቷል። የድርጅት የአፍሪቃ ጉዳይ ኃላፊ ክሊያ ካንስራይበር እስካሁን በእስር ላይ የሚገኙት ሶስቱ ጋዜጠኞች ክስም አልተመሠረተባቸም ይላሉ፤

«ሶስቱ ሰዎች እስካሁን ክስ ሳይመሰረትባቸዉ በእስር ላይ ነዉ የሚገኙት። ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የተመለከቷቸዉ እማኞችና የጸጥታ ኃይሎችም ጭምር እንደገለጹት፤ ቁም ስቅል ተፈጽሞባቸዋል። እጅግ ጨካኝና ያልተለመደ ቅጣት፤ በጣም ተደብድበዋል፤ እንደዉም አንደኛዉ በሚደበደቡበት ወቅት ቀልቡን መሳቱም ተሰምቷል። እዚያ ከሚገኙ ምንጮቻችን ጋ የተገናኘዉ አንደኛዉ የፖሊስ መኮንን እንዳለዉም ድብደባዉ የተፈጸመባቸዉም ከሶስቱ ጋዜጠኞች መረጃ ለማዉጣጣት በሚል ነዉ።»

እንደRSF ሁለቱን የሶማሊያ ራዲዮዎች ለሀገሪቱ የስለላ ተቋም ጥቃት ያጋለጠዉ ዘገባ በዩናይትድ ስቴትስና የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ ወቅት የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሀሰን ሼኽ መሐመድ መቅዲሹ ዉስጥ በመንግሥት ኃይሎችና በጦር አበጋዞች መካከል የተካሄደ ዉጊያን አስመልክቶ ከአሜሪካዉ PBS ቴሌቪዥን ጋ ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ የተሰነዘረ ትችት ነዉ። RSF በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸም ድብደባን አጥብቆ እንደሚያወግዝ የገለጹት የድርጅቱ የአፍሪቃ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ ካንስራይበር መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባቸዉ የጣሱት የጋዜጠኝነት መመሪያ ቢኖር እንኳ ሥርዓት የተከተለ ሕግ ማስከበሪያ እያለ አካላዊ ጉዳት ሊፈጸምባቸዉ እንደማይገባ ያመለክታሉ፤

Symbolbild Weltradiotag
ምስል picture-alliance/dpa

«ድርጅታችን በማንኛዉም ጊዜና ዓይነትቁም ስቅል መፈጸምን ያወግዛል። እንዲህ ዓይነቱን የጅምላ እስር አነሳስቷል ከተባለዉ የመገናኛ ብዙሃኑ ዘገባ እንደምረዳዉ፤ እርግጥ ነዉ ማንኛዉም ሀገር ቢሆን 19 ሰዎችን እንዲህ ባለዉ መንገድ የማሠር ሕጋዊ መሠረት አይኖረዉም፤ ምናልባት ዘገባዉ ጥቂት የጋዜጠኝነት መመሪያዎችን ጥሶ ሊሆን ይችላል። በምን መልኩ ግን አካላዊ ቁምስቅል ለማድረስ የሚያስችል ሕጋዊነት አይኖረዉም። በመጠኑም ቢሆን የሆነ ሕጋዊ ሥርዓት ሶማሊያ ዉስጥ ይኖራል ብዬ እገምታለሁ ያነዉ በዚህ ጊዜ ጥቅም ላይ ሊዉል የሚገባዉ እንጂ የዘፈቀደ እስራትና አካልን ማሰቃየት አይደለም።»

ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም ጀምሮ ስምንት ጋዜጠኞች የተገደሉባት ሶማሊያ መገናኛ ብዙሃኑ ላላቋረጠ ወከባ እንደተዳረጉ ነዉ ድንበር የለሽ የጋዜጦች ተሟጋች የሚያመለክተዉ። በጋዜጠኞች አያያዝና በመገናኛ ብዙሃን ይዞታዋም ሶማሊያ ከ180 ሃገራት አሁን 176ኛ ደረጃ ላይ ነዉ የምትገኘዉ። ካንስራይበር ጋዜጠኞቹ ከሁሉም ወገን ለጥቃት የተጋለጡ መሆናቸዉን ነዉ የሚናገሩት፤

Somalische Kämpfer sollen Al Kaida-Ableger im Jemen verstärken
ምስል Fotolia/picsfive

«በሀገሪቱ ካለዉ የጸጥታ ሁኔታ ጋ በተገናኘ የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ የአሸባብ የአጥፍቶ መጥፋት የሽብር ጥቃት ኢላማ እንደሆነ ነዉ። ከ2013ዓ,ም ጀምሮ 8 ጋዜጠኞች ተገድለዋል፤ አንዱ እንደዉም በቅርቡ ከሳምንታት በፊት ነዉ። ሆኖም ግን ከሶማሊያ መንግሥትም ቢሆን ችግሮች እየገጠሙት ነዉ። ያም ማለት መገናኛ ብዙሃኑ ለመንቀሳቀስ የሚያስችላቸዉን ነፃነት ማግኘት አልቻሉም።»

አያይዘዉም የRSF የአፍሪቃ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊዋ ሶማሊያ ዉስጥ የመገናኛ ብዙሃንን ሕግ ለማጽደቅ የተወሰደዉን ተነሳሽነት አድንቀዉ፤ ተሻሽሎ ሕጉ ተግባራዊ የሚሆንበት ሁኔታ ቢፈጠር የተሻለ እንደሚሆንም አመልክተዋል። የሶማሊያ ጋዜጠኞች ብሔራዊ አንድነት በበኩሉ የሶማሊያ መንግሥት ለታሠሩት አባላቱ ፍትህ የሚያገኙበትን ሁኔታ እንዲያረጋግጥ ተማጽኗል። ጋዜጠኞችና ቴክኒሺያኖችን ጨምሮ የራዲዮ ጣቢያዎቹ ስድስት ሠራተኞች፣ የጥበቃ ሠራተኞች ቢለቀቁም ራዲዮዎቹ ግን እስካሁን ሥርጭት አቁመዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ