1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግሪክ ሕዝበ ውሳኔ

እሑድ፣ ሰኔ 28 2007

ግሪክ በአውሮጳ መዓከላዊ ባንክና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የቀረበላትን የቁጠባና ተሐድሶ መርሐ-ግብር ላለመቀበል በሕዝበ ዉሳኔ አሳለፈች። በግሪክ እሁድ ጠዋት የጀመረው ሕዝበ-ውሳኔ ያለምንም እንከን መከናወኑም ተዘግቦአል።

https://p.dw.com/p/1Ft4I
Bildergalerie Griechenland Fünf-Euro-Banknote
ምስል Getty Images/AFP/L. Gouliamaki

በግሪክ ሠዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ አንድ ሰዓት በጀመረው ሕዝበ-ውሳኔ ወደ 10 ሚሊዮን መራጮች ድምፅ መስጠት እንደሚችሉም ተመልክቶ ነበር። መራጮች እጅግ በዕዳ የተዘፈቀችው አውሮጳዊቷ ሀገራቸው በአውሮጳ ኮሚሽን፣ በአውሮጳ መዓከላዊ ባንክ እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የቀረበላትን የቁጠባና ተሐድሶ መርሐ-ግብር መቀበል አለመቀበሏን በድምፅ በመስጠት ነዉ የወሰኑት። በርካታ ግሪካውያን የእሁዱን ምርጫ ሀገራቸው በዩሮ ዞን የንግድ ሸርፍ አባል ሀገርነት ስለመቀጠሏ የሚወሰንበት ምርጫ አድርገው ወስደውታል። በጠቅላይ ሚንስትር አሌክሲስ ሲፕራስ የግራ ክንፍ ፖለቲካ የሚመራው የግሪክ መንግሥት ሀገሪቱ ከአበዳሪዎች ጋር ጠንከር ያለ ድርድር ወደ ማድረጉ ለመመለስ ያስችላት ዘንድ ሕዝቡ በድምፁ «እምቢ» ማለት እንዳለበት ማሳሰባቸዉ ተመልክቶአል። የቅድመ መጠይቅ መዘርዝሮች እንዳመላከቱት ከሆነ የመራጩ ሕዝብ ፉክክር ጠንካራ ነው። የእሁዱ የግሪክ ሕዝበ-ውሳኔ ተቀባይነት የሚኖረው ከመራጮች 40 በመቶው ድምፅ መስጠቱ ከተረጋገጠ በኋላ እንደሆነም ተጠቅሶ ነበር።

Griechenland Referendum Auszählung
ምስል GettyImages/AFP/L. Gouliamaki


በሌላ በኩል የጀርመኑ የኤኮኖሚ ሚኒስትር ዎልፍጋንግ ሾይብለ ግሪክ ከይሮ ሸርፍ ተጠቃሚ አባልነት አትወጣም የሚል ድምዳሜ እንደሌላቸዉ ቢልድ ለተሰኘዉ የጀርመን ጋዜጣ ቅዳሜ ዕለት ገልፀዉ ነበር። ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ግሪክ ሕዝበ ዉሳኔ ለማድረግ በዝግጅት ካለችበት አንድ ቀን ቀደም ብለዉ ነበር። ዎልፍጋንግ ሾይብለ ግሪክ በይሮ ሸርፍ ተጠቃሚ ሃገራት አባልነት መቆየት አልያም ለግዜዉ የመዉጣት ዉሳኔ በግሪካዉያን እጅ መሆኑን ሳይገልፁ አላለፉም። ጀርመንና ፈረንሳይ በጎርጎረሳዉያኑ 2003 ዓ,ም የሸርፉ ተጠቃሚ ሃገራት ሕግን የጣሱ የመጀመርያዎቹ ሃገራት ነበሩ ያሉት የጀርመኑ የኤኮኖሚ ሚኒስትር የግሪክን ህዝብ ግን ችላ ብለን አንተዉም ማለታቸዉ ተዘግቧል። ግሪክ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማቱ ያስቀመጡላትን የተሃድሶ መረሃ-ግብር ተግባራዊ ማድረግ አለማድረግ በሚለዉ ጥያቄ እሁድ ዕለት ሕዝበ ዉሳኔ ከመድረጓ በፊት ቅዳሜ በታየዉ የቅድመ-መጠይቅ መዘርዝር ሁለቱም ወገኖች እኩሌታ ቁጥር ላይ ሆነዉ ታይተዉ ነበር።

Griechenland Demonstration Nein Referendum
ምስል picture alliance/ZUMA Press/M. Debets


አዜብ ታደሰ


ማንተጋፍቶት ስለሺ