1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግሪክ ቀውስና የዕዳ ምሕረቱ

ረቡዕ፣ መጋቢት 5 2004

በዕዳ ቀውስ ተወጥራ የምትገኘው ግሪክ አብዛኞቹ የግል አበዳሪዎች የአገሪቱን ዕዳ ለመቀነስ ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ላይ በወሰዱት ታሪካዊ ዕርምጃ በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ ከለየለት መንግሥታዊ ክስረት ልትተርፍ በቅታለች።

https://p.dw.com/p/14K9k
ምስል Reuters

በዕዳ ቀውስ ተወጥራ የምትገኘው ግሪክ አብዛኞቹ የግል አበዳሪዎች የአገሪቱን ዕዳ ለመቀነስ ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ላይ በወሰዱት ታሪካዊ ዕርምጃ በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ ከለየለት መንግሥታዊ ክስረት ልትተርፍ በቅታለች። 86 በመቶው ባንኮችና መሰል ባለሃብቶች ዕዳውን ለመቀነስ ሲስማሙ ይሄም ከመቶ ሚሊያርድ ኤውሮ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል። የግሪኩ ፊናንስ ሚኒስትር ኤቫንጌሎስ ቬኒዜሎስ ዕርምጃውን ታሪካዊ ሲሉት አገራቸው በዚሁ እስክ 2020 ድረስ መንግሥታዊ ዕዳዋን ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ አንጻር እስክ 120 ከመቶ ወይም ከዚያ በታች ለመቀነስ ጭብጥ እድል እንዳገኘች ነው የተናገሩት።

«ዕርምጃው ባለሃብቶቹ በግሪክ ኤኮኖሚ፤ እንዲሁም በኤውሮ-ዞን የኤኮኖሚ ማስተካከያ ፖሊሲ ላይ ዓመኔታ እንዳላቸው የሚያሳይ ምልክት ነው። ባለሃብቶቹ የነገሩን ጥቅምና ጉዳት በሙሉ ከመዘኑ በኋላ በመጨረሻ ከውሣኔ ላይ ለመድረስ ችለዋል። ገበያ ደግሞ የበጎ አድራጎት ነገር ባለመሆኑ ውሣኔው ለነርሱ ለራሳቸውም እንደሚጠቅማቸው ግልጽ ነው»

ግሪክ እስካሁን ተጭኖባት የሚገኘው የዕዳ ክምር 350 ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ ይጠጋል። ከዚሁ 206 ሚሊያርዱም የግል ባለሃብቶቹ ነበር። እነዚህ ደግሞ ባንኮች፣ ኢንሹራንስ ወይም መድሕን ድርጅቶች፣ ሌሎች የገንዘብ ተቋማትና የግል ባለ ገንዘቦች ናቸው። አሁን ከባለሃብቶቹ ከዘጠና በመቶ የሚበልጡት ከግሪክ ይደርሳቸው የነበረውን ገንዘብ ከ 53 በመቶ በሚበልጥ መጠን ቀንሰዋል።

ግን ይህን ያደረጉት ደግሞ ያለ ምክንያት አይደለም። ግሪክ ከለየለት መንግሥታዊ ክስረት ላይ ብትወድቅ ጠቅላላ ገንዘባቸውን እንዳያጡ ባደረባቸው ስጋት ነው። የሆነው ሆኖ ከግሉ ዘርፍ የዕዳ ቅነሣ በኋላ ውሣኔ የአውሮፓ ሕብረትም ለግሪክ ሊያቀርብ ካቀደው የ 130 ሚሊያርድ ኤውሮ የዕርዳታ ፓኬት 35,5 ሚሊያርዱን ከወዲሁ ነጻ አድርጓል። ይህም በአውሮፓ ዕፎይታን ማስከተሉ አልቀረም። የኤውሮ-ቡድን ሃላፊ ዣን-ክላውድ-ዩንከር ግሪክ የመክሰሯ አደጋ እንደተወገደ ነው የተናገሩት።

«ግሪክ ክስረትን ማወጇ ወይም ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንግድ ቀውሱን ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሃገራት የማስተላለፏ አደጋ የለም ለማለት ይቻላል»

በሌላ በኩል ይሁንና የኤኮኖሚ ጠበብት በዕዳው ቅነሣ የተነሣ የተጋነነ ውጤት እንዳይጠበቅ አስጠንቅቀዋል። ግሪክ በዕዳ ቅነሣው 107 ሚሊያርድ ኤውሮ ከትከሻዋ ስለተነሳላት የግሪክ የዕዳ ቀውስ በአንዴ መፍትሄ አገኘ ማለት አይደለም፤ በአቴን የኒቨርሲቲ የኤኮኖሚ ሣይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ማኖስ ማትሳጋኒስ እንደሚያስረዱት ዕዳው ባይቀነስ እርግጥ ለግሪክ የሚቀረው አማራጭ፤ መንግሥታዊ ክስረት፤ ማሕበራዊ ቀውስና አስከፊ የአደባባይ ዓመጽ በሆነ ነበር።

ለማንኛውም አሁን ከዕዳው ቀነሣ በኋላም ግሪክ በኤኮኖሚ መልሳ በሁለት እግሮቿ እስክትቆም መንገዱ ገና ረጅም መሆኑ የሚቀር አይመስልም። ቢሆንም እስክዚያ ደግሞ የኤውሮ-ዞን አዲስ የስፓኝ ችግር ተደቅኖበታል። ስፓኝ ባለፈው ዓመት ከባድ ከሆነ የበጀት ክስረት ላይ ስትወድቅ ይሄውም ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ አንጻር 8,5 ከመቶ አንጻር ደርሶ ነበር።

ታዲያ የአውሮፓ ኮሚሢዮን ለዚህ ለያዝነው ዓመት 4,4 ከመቶ የበጀት ኪሣራ ጣራ ቢያስቀምጥም የማድሪድ መንግሥት በበኩሉ የሚጠብቀው አሃዙ 5,8 ገደማ የሚጠጋ እንደሚሆን ነው። ግን የሕብረቱ ዓባል ሃገራትም ሆኑ የብራስልሱ ኮሚሢዮን ይህን አይቀበሉትም። የአውሮፓው ሕብረት የምንዛሪ ኮሜሣር ኦሊ ሬህንም በሣምንቱ መጀመሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይህንኑ ነው ያንጸባረቁት።

«ኮሚሢዮኑ በሙሉ እንዳለ የሚቀበለው የኤውሮ-ቡድን አቋም እንደሚለው የስፓኝ መንግሥት ታርሞ ከቀረበው የበጀት ኪሣራ መጠን ከ 0,5 በመቶ በላይ ማለፍ የለበትም»

እርግጥ እንዲህም ሆኖ በስፓኝ ላይ የተጣለው ግዴታ ልዝብ ሆኖ የሚታይ ነው። የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ቮልፍጋንግ ሾይብለ ለምሳሌ ስፓኝ ሌላዋ ግሪክ አትሆንም ወደ ማለቱ ነው ያዘነበሉት በትናንቱ የብራስልስ የገንዘብ ሚኒስትሮች ስብሰባ እንዳመለከቱት።

«ግሪክ እንድ ዕውነቱ ራሷን የቻለች ታሪክ ናት። ይህን ባለፉት ሁለት ዓመታት አዘውትረን ተመልክተናል። ስፓኝ በበኩሏ ትልቅ ዕርምጃ አድርጋለች። ይህ የፊናንስ ገበዮች አመለካከትም ነው። እርግጥ ሁላችንም ገና አስቸጋሪ ጎዳና ላይ ነን። ሆኖም ያለፉት ሣምንታትና ወራት ልምዶች፤ እንዲሁም ዕርምጃዎች እንደሚያሳዩት በትክክለኛው መንገድ ላይ ነው ያለነው። እናም በዚሁ አቅጣጫ በስኬት ለመቀጠል ቁርጠኞች ነን»

ይህ እርግጥ ሁሉም የሚጋሩት አመለካከት አይደለም። የአውስትሪያ የፊናንስ ሚኒስትር ማሪያ ፌክተር ለምሳሌ ጠበቅ ብሎ የሰፈነው አዲሱ የሕብረቱ የበጀት ቁጥጥር ውል አሁኑኑ መልሶ እንዳይላላ ነው የሚያስጠነቅቁት። እንደርሳቸው ከሆነ ስፓኝ ቢቀር ለመጪው 2013 አስተያየት ልትጠብቅ አይገባም። አገሪቱ የበጀት ኪሣራዋን ለማለዘብ በጣሙን መጣር ይኖርባታል። ሚኒስትሯ እንዳስገነዘቡት ሁሉም እንዲያውቀው አዲሱን ደምብ ጠንክሮ ገቢር ማድረጉ አስፈላጊ ነገር ነው።

የስፓን መንግሥትም ለነገሩ በኤውሮ-ቡድን ስብሰባ ላይ በጀቱን እስከ 2013 መልሶ በሚፈቀደው መጠን ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቱ አንጻር ከሶሥት በመቶ ጣራ በታች ለማድረግ ግዴታ ገብቷል። እርግጥ ይህ አስቸጋሪ ነገር የሚሆን ነው የሚመስለው።

ወደ ግሪክ መለስ እንበልና ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው የግሉ ዘርፍ 107 ሚሊያርድ ኤውሮ ዕዳ ለመቀነስ በመወሰኑ የአውሮፖ ሕብረትም 130 ሚሊያርድ መድሕን ፓኬቱን ለማቅረብ ከእንግዲህ የሚያቅማማበት ነገር የለውም። ስለዚህም ገንዘቡን ለማቅረብ ወስኗል። ግን ይህ የጀርመን ባንኮች ፌደራል ማሕበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚሻኤል ኬመር እንደሚሉት ብቻውን ገሪክ ዳነች፤ የግሪክ ችግር ተፈታ፤ አለቀለት ማለት አይደለም።

«እርግጥ ደስታው ተገቢ ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ግሪክ ጊዜ አገኘች እንጂ ከችግሯ ተላቀቀች ማለት እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ገና የቤት ሥራዋን ማከናወን ይኖርባታል። የበጀት ሁኔታዋን ማረጋጋቱ፣ የቁጠባ ፖሊሲዋን ገቢር ማድረጉና መንግሥታዊ ንብረትን ወደ ግል ዕጅ ማዛወሩ ሊታለፍ የሚችል ነገር አይደለም። ይህ እጅግ ጠቃሚ ነገር ሲሆን በወቅቱ የደስታ ስሜት ሊዘነጋ አይገባውም»

የግሪክ ዕርምጃ እያደር የሚታይ ሲሆን በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ቀውሱን ለመታገል እንዲበጅ በባንኮች ላይ የገንዝብ ሽግግር ግብር ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ደግሞ አከራካሪ እንደሆነ ቅጥሏል። ጀርመንና ፈረንሣይ ብራስልስ ላይ የግብሩን መስፈን ደግፈው ሲቀሰቅሱ በአንጻሩ ብሪታኒያ፣ ሉክሰምቡርግና ስዊድን እየተቃወሙት ነው። እነዚሁ በግብሩ የተነሣ በተለይ የአውሮፓ የፊናንስ ገበዮች የፉክክር ብቃት እንዳይጠፋ ይሰጋሉ።

የጀርመኑ ፊናንስ ሚኒስትር ቮልፍጋንግ ቮይብለ ስጋቱ ተገቢ አለመሆኑን ሲናገሩ በሌላ በኩል የሉክስምቡርጉ የሥልጣን አቻቸው ሉክ ፍሪድን ጉዳዩን አሳሳቢ አድርገው ነው የሚመለከቱት።

«ይህ የምንለው የገንዘብ ሽግግር ሁሌም አገር አቋራጭ ባሕርይ የሚኖረው ነው። ግብሩ በትንሽ የሃገራት ቡድን ውስጥ በሥራ ላይ ቢውል እንኳ ወደ ሌሎች አገሮችም በቀላሉ ሊዛመት ይችላል»

ከስዊድን በኩልም ተመሳሳይ ቁጥብነት መኖሩ ነው የሚነገረው። በአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር በአንደርስ ቦርግ ዕምነት የፊናንስ ሽግግሩ ግብር ከመንግሥትና ከኩባንያዎች ተጨማሪ ወጪን የሚጠይቅ ነው የሚሆነው። እርግጥ ይህን መሰሉ ግብር የመላውን የሕብረቱን ዓባል ሃገራት ፈቃድ የሚጠይቅ በመሆኑ በወቅቱ የፊናንሱ ገበዮች ለጊዜውም ቢሆን ዕፎይ ሊሉ ይችላሉ።

በሌላ በኩል የአውሮፓው የፊናንስ ሽግግር ግብር የንግድ ተቋማት ይህን ግብር ወደማትጠይቀው ወደ ብሪታኒያ እንዲሸሹ ሊያደርግ ይችላል የሚል አስተያየት በአንዳንድ ባለሙያዎች መሰንዘሩም አልቀረም። እነዚሁ በአንጻሩ ከባንኮች ይልቅ የምንዛሪ ገበየች ግብር ይስፈን ባዮች ናቸው። ክርክሩ በመጨረሻ ምን መልክ ሊይዝ እንደሚችል ከወዲሁ መተንበዩ ለጊዜው ያዳግታል።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ