1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግሪክ ክስረትና ተጽዕኖው

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 27 2002

የኤውሮ ምንዛሪ ተገልጋይ ሃገራት በበጀት ኪሣራ የተወጠረችውን ዓባል ሃገር ግሪክን ከለየለት ውድቀት ለማትረፍ ከዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ጋር በመሆን የ 110 ሚሊያርድ ኤውሮ ዕርዳታ ለመስጠት ወስነዋል።

https://p.dw.com/p/NF6Z
ምስል DW

መንግሥታቱ ዕርምጃውን የሚወስዱት በተለይም አደጋ ላይ የወደቀውን የጋራ ምንዛሪ የኤውሮን እርጋታም ለማረጋገጥ ነው። ግሪክ ዕርዳታውን ለማግኘት ጠበቅ ያለ የቁጠባ ዕርምጃ መውሰድ ሲኖርባት ይህም ገና ከአሁኑ አገሪቱን በሥራ ማቆም ዓድማና በሕዝብ ቁጣ ማሽመድመዱ አልቀረም። የሌሎቹ የኤውሮ ምንዛሪ ዓባል ሃገራት የፖርቱጋል፣ የስፓኝ ወይም የኢጣሊያ በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የመውደቅ አደጋም እንዲሁ የስጋት መንስዔ ሲሆን የግሪክ ተጎራባች የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ አገሮችም የቀውሱ ተጽዕኖ እየተሰማቸውና እያሳሰባቸው ነው። አደጋው ተገትቷል፤ ወይስ ገና የሚያስከትለው መዘዝ ይኖረዋል? ይህ በወቅቱ ብዙ እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው።

የግሪክ መንግሥት አገሪቱን ከለየለት ክስረት ለመሰወር በሚቀጥሉት ሶሥት ዓመታት ውስጥ ሰላሣ ሚሊያርድ ኤውሮ መቆጠብ አለበት። ዕርዳታው የሚሰጠው በዚህ ቅድመ-ግዴታ በመስማማቱ ነው። እርግጥ ይህን ግዙፍ ገንዘብ ለመቆጠብ የመንግሥት ተቀጣሪዎችን ደሞዝ እስከመቀነስ ድረስ በሕዝብ ኑሮ ላይ ከባድ ተጽዕኖ የሚኖራቸው ዕርምጃዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል። ታዲያ የቁጠባው ፖሊሲ በወቅቱ አገሪቱን በጠቅላላ የሥራ ማቆም ዓድማ ሲወጥር መርሁ እንደታቀደው ገቢር ሆኖ መቀጠሉን መናገሩ ለጊዜው በጣሙን ነው የሚያዳግተው።

የሆነው ሆኖ የግሪክ መንግሥት የቁጠባ ዕርምጃውን ባይወስድ ዕርዳታው ዕውን ሊሆን ባልቻለ ነበር። የአውሮፓው ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ሆሴ-ማኑዌል-ባሮሶ ባለፈው ሰንበት እንደገለጹት ለዕርዳታው የሚያስፈልገው ሁኔታም የተሟላ መሆኑ ተረጋግጧል።

“የአውሮፓ ኮሚሢዮን ለግሪክ የሚሰጠውን የፊናንስ ዕርዳታ ለማንቀሳቀስ ሁኔታዎች ተሟልተዋል ባይ ነው። መላው የግሪክ ፍላጎትም በጊዜው እንደሚሟላ ለማስረገጥ እንወዳለን”

የኤውሮው ቡድን ፕሬዚደንት ዣን-ክላውድ-ዩንከር ከዚሁ ከተል ብለው እንዳስረዱት ደግሞ በተለይ የዓባል መንግሥታቱ አመለካከት ይበልጡን ወሣኝ ነበር።

“16ቱ የኤውሮ-ዞን አገሮች ዕርዳታውን ለማንቀሳቀስ ዛሬ ወስነዋል። ለዚሁ መሠረት የሆነው የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክና ኮሚሢዮን የመላው የኤውሮ-ዞር እርጋታ አደጋ ላይ ከወደቀ በኋላ ያቀረቡት ዘገባ ነው”

ዕርዳታው 80 ሚሊያርዱ በኤውሮ-ዞን አገሮች የተቀረው 30 ሚሊያርድ ኤውሮ ደግሞ በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በአይ.ኤም.ኤፍ የሚቀርብ ሲሆን ግሪክ ብድሯን መልሳ መክፈል ,ለመቻሏ ዋስትና ለመስጠት የሚደፍር ማንም የለም። የዓባል ሃገራቱ ግብር ከፋይ ሕዝብ ገንዘብ ባዶ ቦጣ ላይ ፈሶ የመቅረቱም ሁኔታ ብዙዎችን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል። እርግጥ የአውሮፓ ሕብረት ዋና ስጋት ደግሞ የማዳኑ ተግባር በግሪክ ብቻ ተወስኖ ይቀራል ወይስ ተከታይ አገር ብቅ ይላል ነው።
በአስጊነት የሚታዩት ፖርቱጋልን ወይም ስፓኝን የመሳሰሉት ሌሎች የኤውሮው ምንዛሪ አገሮችም እንደ ግሪክ ሁሉ ከበድ ባለ የበጀት ኪሣራ ተጠምደዋል። አያምጣው ነው እንጂ የአውሮፓ ሕብረት እነዚህን ሁሉ ማዳን ቢኖርበት ታዲያ ጉዳዩ ከአቅም በላይ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። እርግጥ እንደ ፈረንሣይዋ የፊናንስ ሚኒስትር እንደ ክሪስቲን ላጋርድ ሁሉ የግሪክን ጉዳይ ከሌሎቹ ለይተው የሚመለከቱት የሕብረቱ ባለሥልጣናትም አልታጡም።

“ግሪክ፣ ፖርቱጋል፣ ስፓኝ፣ ኢጣሊያና ሌላ ማንም ይሁን በተናጠል የሚታዩ ናቸው። የግሪኩ እጅግ የተለየ ሁኔታ ነው። ባለፉት ዓመታት ይቀርቡልን የነበሩት መረጃ አሃዞች ዕውነተኛ አልነበሩም። ይህም አመኔታን የሚያጓድል ሁኔታን ነው ያስከተለው”

የወቅቱ የግሪክ ቀውስ ያስተማረው ነገር ቢኖር የኤውሮ አገሮች የመረጃ ልውውጥ በየጊዜው ብቅ የሚሉ ቀውሶችን መቋቋም ይቻል ዘንድ ወደፊት መሻሻል እንዳለበት ነው። ከዚሁ ሌላ የጋራ ምንዛሪው ዓባል መንግሥታት የኤኮኖሚ ፖሊሲያቸውን ሊያጣጥሙ ይገባል። ለጊዜው በጋራና በቁርጠኝነት ተገቢውን ዕርምጃ በመውሰድ የፊናንሱን ቀውስ የመጀመሪያ ግፊት ለመቋቋም ችለዋል። ይህም ደግሞ ለመጪው ትምሕርታዊነት አለው።

Griechenland Ausschreitungen in Athen Mittwoch 5.5.2010
ዓመጽና ተቃውሞው አይሏልምስል AP

የኤውሮው ዞን ሁኔታ አስተማማኝ ሆኖ መረጋጋቱ እያደር የሚታይ ጉዳይ ሲሆን በሌላ በኩል የግሪክ ቀውስ ተጽዕኖ በጎረቤቶቹ የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ አገሮችም ለስጋት መንስዔ መሆኑ አልቀረም። በዚህ አካባቢ በማቄዶኒያ ወይም በአልባኒያ ለምሳሌ የግሪክ ኤኮኖሚ እስካሁን በአርያነት ይታይ ነበር። ዛሬ ግን የኤውሮ ዞን ግሪክን ለማዳን ቢነሣም የአካባቢው ነዋሪዎች ችግሩን ለመጋተር ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው ማሰር ሳይኖርባቸው እንደማይቀር ነው የሚያምኑት። መዘዙ ለኛም ይተርፋል ባዮች ናቸው።

የግሪክ ባንኮች በማቄዶኒያ ወይም በአልባኒያና በሌሎች የደብብ ምሥራቅ አውሮፓ አገሮች በአብዛኛው ገበዮችን ሲቆጣጠሩ ቆይተዋል። እስካሁን በመላው አካባቢ የዕድገት ሞተር ነበሩ። ግን ወደፊት ከግሪክ ወደዚያ የሚፈሰው ብድርና መዋዕለ-ነዋይ ከቀነሰስ ምንድነው የሚሆነው? ቡልጋሪያ ውስጥ ብቻ በተለይም በግንቢያው ዘርፍ 100 ሺህ የሥራ ቦታዎች በግሪክ መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎች ላይ ጥገኞች ናቸው። የዓለም ባንክ ይህንኑ በማጤን እነዚሁ ሃገራት በኤኮኖሚ ዕድገት መገታትና በከፍተኛ የመንግሥት በጀት ኪሣራ ፈታኝ በሆነ የምጣኔ-ሐብት ችግር እንዳይጠመዱ ያስጠነቅቃል።

በደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ አካባቢ በአጠቃላይ የፊናንስ ገበያውና የንግዱ ግንኙነት በግሪክ ላይ ጥገኛ ሆኖ ነው የሚገኘው። በመሆኑም የማቄዶኒያው የፊናንስ ሚኒስትር ዞራን ስታቭሬቭስኪ ለምሳሌ ጎረቤቲቱን ግሪክን ለማዳን በኤውሮ አገሮች በተደረገው ውሣኔ መደሰታቸውን አልሸሸጉም። ሆኖም ግን በግሪክ ላይ የተጣለው ጠንካራ የቁጠባ ፕሮግራም ለጎረቤቶቹ አገሮችም መትረፉ የማይቀር ነውና ችግር ሊያስከትል መቻሉን አያይዘው ማስጠንቀቃቸው አልቀረም።

“በግሪክ የሚፈጠር ዓመጽና ዓድማዎች በአካባቢው ንግድ ላይ ከባድ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል። እና ድንበሮች ሊዘጉ ይችላሉ ማለት ነው። እርግጥ የግሪክ ኩባንያዎች ማቄዶኒያንና ሌሎቹን ጎረቤት አገሮች ለቀው ይወጣሉ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ማቄዶኒያ በዝቅተኛ የሥራ ዋጋ የተነሣ ማራኪ አገር ናት። አንዲት በየቀኑ አሥር ሰዓት የምትሰራ የማቄዶኒያ ልብስ-ሰፊ በወር ምናልባት ከ 100 እስከ 120 ኤውሮ ደሞዝ ብታገኝ ነው። ግሪክ ውስጥ ግን ሁኔታው ከዚህ ይለያል”

እንግዲህ እስካሁን ይሄው ዝቅተኛ ደሞዝ የግሪኩን ቀውስ ተጽዕኖ ለመቋቋም በጅቷል ለማለት ይቻላል። ግን እስከመቼ? አይታወቅም። የግሪክ ቀውስ የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ሕዝብ አንጀቱን ጠበቅ አድርጎ ማሰር ሊገደድ እንደሚችል ሲያመለክት የአውሮፓ ሕብረት ወይም የምንዛሪው ማሕበር ዓባል ለመሆን የሚደረገውን ጥረትም እንደሚያከብድ በግልጽ እየታየ ነው። ለምሳሌ ሕብረቱን በተቻለ ፍጥነት ለመቀላቀል በምትሻው በክሮኤሺያ ጠቅላይ ሚኒስትር ያድራንካ ኮዞር ጥብቅ የበጀት ቁጠባ ዲሢፕሊን እንደሚያስፍኑ በማያሻማ ሁኔታ ተናግረዋል።

“ምንም፤ ማንም የማይደፈር ነገር የለም። በራሳችን እንጀምራለን። በመንግሥቱ በጀት ተጠቃሚዎች! ለእንግዶቻችን ውሃ ብቻ እየጋበዝን፤ ከቡና ጋር ወይም ካለ ቡና ይህን ጊዜ እናልፈዋለን ባይ ነኝ”

የኤውሮን ምንዛሪ ክልል በፍጥነት ለመቀላቀል የሚፈልጉት ሁለቱ የአካባቢው የአውሮፓ ሕብረት ዓባል ሃገራት ቡልጋሪያና ሩሜኒያም መስፈርቱን ሁሉ ለማሟላት ሲጥሩ ቢቆዩም በግሪክ ጥፋት ተቀጪ እንዳይሆኑ በጣሙን እየሰጉ ነው። በመሆኑም የቡልጋሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪሶቭ ከአሁኑ ፍትሃዊነት ተጓድሏል ማለታቸው አልቀረም። ለማንኛውም ቡልጋሪያና ሩሜኒያ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የኤውሮ ዞንን በመቀላቀል ከብሄራዊ ምንዛሪያቸው ለመሰናበት የነበራቸው ዕቅድ አሁን ለጊዜው የጨለመበት ነገር ነው የሚመስለው።
የግሪክ ቀውስ በጠቅላላው ለደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ አካባቢ የበረዶ ውርጂብኝን ያህል ነው የሆነው። የፖለቲካው አለማስተማመን ሲጨምር የኤኮኖሚው ስጋት ደግሞ ቀድሞ ለአካባቢው አርአያ ለነበረችው ለግሪክ በተደረገው የዕርዳታ ውሣኔ ገና አልተወገደም። መጪው ጊዜ ፈታኝና የሚሆነውም በትክክ ሊተነብዩት የሚያዳግት ነው። ለግሪክ ግን ከመንግሥታዊ ክስረት ለመዳን ከቁጠባው ጉዞ ሌላ መንገድ የለም።
መስፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ