1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግሪክ የካሳ ጥያቄ እና ጀርመን

ማክሰኞ፣ መጋቢት 15 2007

በጀርመን እና በግሪክ የገንዘብ ሚኒስትሮች መካከል ንግግሩ ከሯል። ጉዳዩ በሁለት ሚኒስትሮች ብቻ የሚፈታ አይደለም። አዲሱ የግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሲስ ሲፕራስ ሰኞ ወደ ጀርመን መጥተው ከጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋር ስለ ግሪክ የኢኮኖሚ ቀውስ ተወያይተዋል። የሚያስማማ ሀሳብ ላይ ግን አልደረሱም።

https://p.dw.com/p/1Evzu
Berlin Tsipras bei Merkel
ምስል Getty Images/AFP/J. MacDougall

በሚሊዮን ዮሮ እዳ የተዘፈቀችው ግሪክ ፤ ከአውሮፓ ህብረት ተጨማሪ ብድር ለማግኘት ከምትሞክረው ሌላ፤ ከጀርመንም የካሳ ክፍያ ለማግኘት ስትከራከር ሰንብታለች። የዛሬው የአውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅት፤ አከራካሪውን የካሳ ክፍያ ይመለከታል።

አዲሱ የግሪክ መንግሥት በጀርመን ላይ የካሳ ጥያቄ ያነሳው ከ 70 ዓመታት በፊት ለተፈፀመ የጦር ወንጀል ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀርመን ግሪክን በወረረችበት ወቅት በርካታ ግሪካውያን ተገድለዋል፣ መሠረተ ልማቱ ወድሟል፤ ሌላም ሌላም። ጀርመን ለዚህ በተናጠል ካሳ አልከፈለችም። ይሁንና ይህ ርዕስ ለጀርመን ያበቃለት ጉዳይ ነው። የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ ሽቴፋን ዚበርት ከሁለት ሳምንት በፊት በርሊን ላይ እንደተናገሩት፤ « ጀርመን ፤ በናዚ ስርዓት በበርካታ የአውሮጳ ሀገራት ላይ አሳዛኝ ድርጊት መፈፀሙዋን ሁሌም የማትክደው ጉዳይ ነው። ይሁንና የካሳ ክፍያው ነገር ከሕግም ሆነ ከፖለቲካ አንፃር ብንመለከተው ፤ የተዘጋ አጀንዳ ነው።» ነው ያሉት። የጀርመን የገንዘብ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ደግሞ ፤ ለማንም ግራ በማያጋባ መልኩ « ከግሪክ ጋር ምንም አይነት ድርድር አንጀምርም» ሲሉ ነው የተናገሩት። የጀርመን መንግሥት በተደጋጋሚ እንደገለፀው፤ ከበርካታ የአውሮጳ መንግሥታት ጋር በመስማማት እኤአ በ 1960 ዓ ም 115 ሚሊዮን (በወቅቱ ዶይቸ ማርክ)ካሳ ተከፍሏል። ከዚህም በተጨማሪ በቂ፤ ግሪክን የሚጠቅሙ የዕረቀ ሰላም ርምጃዎች ጀርመን መውሰዷን ገልፃለች።

የግሪክ የካሳ ጥያቄ ለተለያዩ የጀርመን የፖለቲካ ፓርቲዎችም ያለቀለት ጉዳይ ነው። የቀድሞ የግሪክ መንግሥታትም በጊዜዉ ካሳ ጠይቀው በጀርመን ተቀባይነት አላገኙም። አሁን ግሪክ በብድር በተዘፈቀችበት ወቅት የካሳ ጥያቄ ማንሳቷ ለጀርመን ፖለቲከኞች ከገባችበት አዘቅት እንዴት አድርጋ እንደምትወጣ መንገድ ማመቻቻ ነዉ።

Deutschland Griechenland Besuch Tsipras in Berlin
ምስል DW/S. Kinkartz

የግሪክ የካሳ ጥያቄ ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረዋል ሲል ዶይቸ ቬለለጀርመናዊው አቃቢ ሕግ ፕሮፌሰር ኡርሊሽ ባቲስ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል።« ግሪኮች ፤ብሔራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፍርድ ቤቶች ቀርበው ጠይቀው ነበር፤ እስካሁን ግን ስኬታማ አልነበሩም። ግሪኮች ስል፤ የአሁኑን መንግሥት ብቻ ሳይሆን የቀድሞ የግሪክ መንግሥታትንም ነው። እና ፍፁም እድል የላቸውም አልልም።»

የቀድሞው የጀርመን መንግስት፤ በ50ዎቹ ዓ ም ከናዚ ጀርመን አንፃር ከተዋጉት ተጓዳኝ መንግሥታት ጋር ፤ባደረገው ስምምነት፤ ጀርመን ለፈፀመችው ወንጀል ካሳ የምትከፍለው የሰላም ስምምነት ከተፈራረመች ብቻ እንደሆን በለንደኑ ስምምነት ጸድቋል። ባቲስ እንደሚሉት ጀርመን መልሳ ስትዋሀድ ሆን ብላ ይህ የሰላም ስምምነት እንዳይፈፀም አድርጋለች። የግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሲስ ሲፕራስ በአቴንስ ፓርላማ ቀርበው ሲናገሩ ተመሳሳይ ነገር አንስተዋል። ጀርመን ህጎችን እያጭበረበረች ካሳውን እንዳትከፍል ሸሽታለች የሚል።« ይህ የጀርመን አቋም ነው። የሰላም ስምምነቱ እስከሌለ ድረስ ፤ገንዘብ አታገኙም የሚል። ነገር ግን የናዚ መንግሥት በግል እና መንግሥት ላይ የጦር ወንጀል መፈጸሙ የማይካድ ነው። በተወሰነ መልኩ የግሪኮቹ ጥያቄ የማይካድ ነው። »

ባቲስ ፤ ግሪክ በተወሰነ መልኩ ካሳ ይገባታል ቢሉም ፤ የጀርመን መንግሥት ህጉን አጭበርብሯል ለማለት አያስደፍርም ባይ ናቸው።« በስምምነቱ ስብሰባ ላይ የተገኙት በሙሉ የፈረሙት እንጂ እኛ አጽፍናቸው አይደለም ስምምነት ላይ የደረሱት፤ በዛ ላይ በሌላ መንገድም ቢሆን ግሪክን ደግፈናታል። ከግሪክ አንፃር ያለውን አጋጣሚ በሙሉ አሁን መሞከር ያለ ነው። ስለዚህ ባለው ሁኔታ የቀድሞ መንግሥታትም ይገባናል ያሉትን የካሳ ጥያቄ ማንሳቱ አይቀሬ ነው።»

ሲፕራስ የካሳውን መጠን በአኃዝ ባይጠሩም አንድ የግሪክ ጋዜጣ እንደዘገበው ፤ 300 ቢሊዮን ዩሮ( የግሪክ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ገንዘብ ሳይጨምር መሆኑ ነው) በካሳ ክፍያ መልክ ደምራለች። የካሳው መጠን በአጋጣሚ ይሁን አይሁን ባይታወቅም ከግሪክ መንግሥት እዳ መጠን ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህ ካሳ ከተከፈለ ደግሞ ግሪክ ባንድ ጊዜ እዳዋን ከላይዋ ታወርዳለች። ዋናው ጥያቄ፤ ግሪክ ካሳውን እንዴት ታገኛለች? የሚለው ነው።

Symbolbild Euroscheine Deutschland Fahne
ምስል picture-alliance/dpa

አቃቢ ሕግ ባቲስ እንደሚሉት ፤ እንደ « ጎተ ኢንስቲትውት» የመሳሰሉ የጀርመን ተቋማትን ግሪክ አቴንስ ውስጥ በእዳ ለመያዝ ሁሉ ሞክራ ነበር። ህጉ ስለማይፈቅድላት ብቻ ነው ፤ ዕውን ያላደረገችው። የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ ዚበርት በዚህ ላይ አስተያየት መስጠት አልፈለጉም።

የካሳ ክፍያው የጀርመን ፖለቲከኞችንም እያነጋገረ ይገኛል። ቀደም ሲል የግራ ፓርቲ የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች የምክር ቤት አባል አኔተ ጎርተ ብቻ ናቸው፤ በይፋ፤ ጀርመን ከግሪክ ጋር አንድ መፍትሄ ላይ መድረስ አለባት» ያሉት። የአረንጓዴው ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት አንቶን ሆፍራይተርም ቢሆኑ ፤ ጀርመን ግሪክ ውስጥ በተጠቀሰዉ ወቅት ስለፈፀመችው ወንጀል አንድ ግልፅ የሆነ ውሳኔ ላይ መድረስ አለባት ሲሉ ተደምጠዋል። ቀስ በቀስ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን በስልጣን ላይ ካሉት ፓርቲዎችም ለግሪክ ድምፅ እየተሰማ ነው። ይሁንና የጀርመኑ የገንዘብ ሚኒስትር ቮልፍጋንግ ሾይብለ በቃላቸው እንደፀኑ ነው። « ይህ ለግሪክ፤ በጀርመን ካሳ የአውሮጳ ህብረትን ብድርን እከፍላለሁ የሚል ተስፋ ብቻ ነው የሚሰጠው ፤ ለህዝቡ ይህን ቃል የሚገባ መንግሥት ደግሞ እውነታውን እየካደ ነው»፤ ነው ሲሉ አስረግጠዉ ተናግረዋል። የግሪክ ማህበረሰብን አስመልክቶ ደግሞ፤« የግሪክ ማህበረሰብ ያለበትን ሁኔታ እስካልተገነዘበ ድረስ፤ ሀገሪቷን የተሻለ ሁኔታ ላይ የሚያደርስ መፍትሄ አያገኝም። »

የግሪክ ፓርላማ በሳምንቱ መጨረሻ አዲስ እና ብዙ ግብር እሰበስብበታለሁ ያለውን ሕግ አፅድቋል። በዚህም መሠረት 3,7 ሚሊዮን የሚሆነው የግሪክ ዜጋ እና 450 000 ድርጅቶች የግብር ባለእዳ ናቸው። ይህ ግብር ከሀገሪቷን ባጀት 76 ቢሊዮን ዩሮ መሆኑ ነው። ከዚህ ገንዘብ 9 ቢሊዮን የሚሆነውን ግሪክ በቶሎ አሰባስባለሁ፤ የሚል እምነት አላት። ይህም በቀጣይ ቀናት ውስጥ በአፋጣኝ ግብር ለሚከፍሉ ግሪካውያን፤ ቅጣት እና ወለዱን በመሰረዝ ነው።

ግብር የሚለው ቃል ለግሪካውያን ፤ በአሁኑ ወቅት አስጨናቂ ቃል ነው። ወይ ለግብር የሚከፍሉት ገንዘቡ የላቸውም፤ ወይም እንዴት አድርገው ከግብር ማምለጥ እንደሚችሉ ያፈላልጋሉ። ሀብታሞች ግብር ሲቀነስላቸው፤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ከ 2010 ዓም አንስቶ እስከ 300 በመቶ ገንዘብ ለመንግሥት ሲከፍሉ፤ ባለ ሀብቶች ደግሞ በ9 ከመቶ ግብር ክፍያ ተገላግለዋል። ከዚህም ሌላ ባለፉት አምስት ዓመታት 370 000 የሥራ ቦታዎች ግሪክ ውስጥ ተዘግተዋል። የጡረተኞች ገንዘብ በ40 ከመቶ ተቀንሷል። የግሪክ ወቅታዊ ችግር ተቆጥሮ አያልቅም። የጀርመን ወግ አጥባቂ ጥምር ፓርቲዎች ተጠሪ ሚሻኤል ግሮሰ- ብሮመር፤ ችግሩ ግሪክ ከመበደር በቀር ማሟላት የሚገባትን መስፈርቶች ባለማሟላቷ ነው ይላሉ።«አውሮጳ ግሪክን በሚገባ ሁኔታ ረድታለች፤ ልትረዳም ትፈልጋለች። ነገር ግን በየቀኑ ከግሪክ ወደ ጀርመን ምክንያት እየተፈለገ አይደለም። አሁን ያለው ጉዳይ ሁለተኛ እና የመጨረሻውን የማሻሻያ ድጋፍ የሚመለከት ነው። ግሪክ ብዙ ቃል ገብታለች፤ በተግባር ግን ያዋለችው የለም። ይህንን እንደማናወድሰው እና ለግሪክም ቢሆን ጥሩ እንዳልሆነ መግለፁ የሚያስወቅስ አይደለም። »

Brauchitsch auf Akropolis
ምስል picture-alliance/akg-images

ሲፕራስ ትናንት ጀርመንን ሲጎበኙ፤ እንደወትሮው በጀርመን መንግሥት ላይ ኃይለ ቃል አልሰነመዘሩም፤ ይልቁንም ግሪክ አሁን ላለችበት ቀውስ ያበቃት ጀርመን ሳትሆን የቁጠባ መርሃ ግብሩ ነው፤ ሲሉ ነዉ የተደመጠዉ። ያም ሆነ ይህ ጀርመን ብቻዋን ግሪክ የምትሻውን ብድር ልታፀድቅ አትችልም። የጦር ወንጀል የካሳ ክፍያውም ቢሆን በትናንቱ ጉብኝት ዋና ርዕስ አልነበረም።

ክርስቶፍ ሀስልባህ

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ