1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግሬስ ሙጋቤ ወደ ፖለቲካው መድረክ መግባት

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 22 2007

በዚምባብዌ ገዢው የዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ የፊታችን ታህሳስ በሚያካሂደው ጉባዔው የሀገሪቱን ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ የፓርቲ መሪነት ሥልጣናቸውን እንደገና እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/1DfWB
Grace Mugabe
የዚምባብዌ ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤምስል J. Njikizana/AFP/Getty Images

ለፓርቲው ማዕከላይ ጽሕፈት ቤት ሥልጣን የተጀመረው ጠንካራ ፉክክር ወደፊት ሙጋቤን የሚተካውን ሰው በመለየቱ ሁኔታ ላይ ወሳኝ ሚና ሊይዝ እንደሚችል ታዛቢዎች ጠቁመዋል። የፕሬዚደንት ሙጋቤ ባልተቤት ግሬስ ሙጋቤ ባለቤታቸውን ለመተካት ዕቅድ እንዳላቸው ነው የተሰማው።
የፕሬዚደንት ሙጋቤ ባልተቤት ግሬስ ሙጋቤ ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ በመላ ዚምባብዌ በመዘዋወር ከሕዝብ ጋር በቅርብ መወያየት ጀምረዋል። እአአ በ2018 ዓም በሀገሪቱ በሚደረገው ቀጣዩ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ በዕጩነት ለመቅረብ ዕቅድ እንዳላቸው ባለፈው ሀሙስ፣ እአአ ጥቅምት 23፣ 2014 ዓም ያስታወቁት ግሬስ ሙጋቤ በዚሁ ድርጊት ራሳቸውን የማስተዋወቅ ዘመቻ እያካሄዱ መሆኑን የፖለቲካ ታዛቢዎች ገልጸዋል። ይሁንና፣ የ49 ዓመቷ ወይዘሮ ግሬስ እስከ ቅርብ ጊዜ በፊት ድረስ በፖለቲካው ዘርፍ ተሳትፎ ያልነበራቸው በመሆኑ፣ ይኸው ዕቅዳቸው የሀገሪቱን ሕዝብ ብዙ እያነጋገረ ይገኛል። ብዙው የዚምባብዌ ሕዝብ የወይዘሮ ግሬስ ዕጩነትን ባይደግፈውም፣ የ91 ዓመቱ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ባልተቤታቸው እንደማንኛውም የዚምባብዌ ዜጋ በዕጩነት የመቅረብ መብት እንዳላቸው ነበር ባለፈው ማክሰኞ የሀገሪቱን ምክር ቤት በከፈቱበት ወቅት ያስታወቁት። በደቡብ አፍሪቃ የተወለዱት የዚምባብዌ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ግሬስ ወደ ፖለቲካው መድረክ መግባት የጀመሩት ከጥቂት ጊዜ በፊት ለገዢው የዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ የሴቶች ማህበር ሊቀ መንበርነት ሥልጣን በዕጩነት በተሠየሙበት ጊዜ ነበር። ይኸው ሥልጣን በፖሊትቢሮው ውስጥ ቁልፍ ቦታ እንዲያገኙ መንገድ ሊከፍትላቸው ይችላል። ለነገሩ ለዚሁ ሥልጣን የታጩበት ሂደት ራሱ በጣም አጠያያቂ ነው። በፓርቲው ደንብ መሠረት፣ ለከፍተኛ የፓርቲው ሥልጣን የሚታጭ ግለሰብ የ15 ዓመት የፓርቲ አባል እና በነፃነቱ ትግል ውስጥ የሚደነቅ ስራ የሰራ መሆን እንዳለበት ነው ። በዚህ አኳያ ሲታይ ታድያ፣ ይላሉ የኦንላይን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ዊልፍ ምባንጋ፣ ወይዘሮ ግሬስ በፖለቲካው አንድም ተሞክሮ የላቸውም።
« ግሬስ ፖለቲከኛ አይደሉም። ግሬስ በፖለቲካው መድረክ አዲስ ጀማሪ ናቸው። ግሬስ በዛኑ ፒ ኤፍ ጉዳይም ሆነ ባጠቃላይ በፖለቲካው ዘርፍ አንድም ተሞክሮ የላቸውም። »
እስከቅርብ ጊዜ በፊት ድረስ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው የፍትሕ ሚንስትር ኤሜርሰን ምናንጋግዋ እና ምክትል ፕሬዚደንት ወይዘሮ ጆይስ ሙጁሩ ሮበርት ሙጋቤን የመተካት ጥሩ ዕድል እንዳላቸው ሲባል ነበር የቆየው። በዚምባብዌ የነፃነት ትግል ንቅናቄ ውስጥ ዋና አዛዥ የነበሩ የአንድ ሟች አርበኛ ባልተቤት ጆይስ ሙጁሩ በተለይ ነፃነት ታጋይ አርበኞች ዘንድ ትልቅ ድጋፍ አላቸው።
ወይዘሮ ግሬስ አሁን በሀገሪቱ በመዘዋወር ከሕዝብ ጋር በሚያደርጉት ውይይት ወቅት ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ በዕጩነት ሊቀርቡ በሚችሉት ተፎካካሪዎችቸው ላይ ግልጹን ዛቻ ሲሰነዝሩ እና ምክትል ፕሬዚደንት ጆይስ ሙጁሩን የመሳሰሉት ተፎካካሪዎቻቸው ለዚሁ ሥልጣን የሚያበቃቸው ስራ አልሰሩም በሚል በአንድ የፓርቲው ዝግጅት ላይ ሲወቅሱ ተሰምተዋል።
« ወይዘሮ ሙጁሩ ሥልጣናቸውን መልቀቅ አለባቸው። የፕሬዚደንትነቱን ሥልጣን ከመመኘት አልፈው ለዚች ሀገር የሰሩት አንድም ነገር የለም። ዚምባብዌን ለመምራት የሚያበቃ ችሎታ አላቸው ብየ አላስብም። በገንዘብ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤን ከሥልጣን ለማስወገድ ነው የሚፈልጉት። »
እክል የገጠመውን የሀገራቸውን ኤኮኖሚያዊ ልማት ለማሻሻል መስራት ያለባቸው የዚምባብዌ ባለሥልጣናት አሁን በገዢው የዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ውስጥ የሚያካሂዱት የሥልጣን ሽኩቻ የሀገሪቱን ሕዝብ እንደሚጎዳ ተንታኞች በማስጠንቀቅ፣ ባለሥልጣናቱ ትኩረታቸውን ወደ ሀገር ልማት ግንባታ እንዲያዞሩ አሳስበዋል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ የዚምባብዌ ተቃዋሚ ፓርቲ፣ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ፣ በምሕፃሩ ኤም ዲ ሲ ትናንት በከፈተው የሁለት ቀናት ጉባዔ በቀጣዩ ምርጫ የ34 ዓመቱን የፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ አገዛዝ ማብቃት የሚያስችለው ዕቅድ እንደሚያወጣ አስታውቋል። የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚገምቱት፣ ፓርቲው ከዛኑ ፒኤፍ ጋ በብሔራዊው አንድነት መንግሥት ውስጥ ተጣምሮ በሰራበት ጊዜ ያን ያህል የሚሞገስ ውጤት አለማስመዝገቡ ገፅታውን በመጉዳት በሕዝብ ዘንድ የነበረውን ድጋፍ ቀንሶበታል፤ ይሁንና፣ የፓርቲው መሪ ሞርገን ቻንጊራይ ይህ አባባል የተሳሳተ ነው ይላሉ።
« ይህ ፈፅሞ ጥያቄ ውስጥ የገባ አይመስለኝም። ከዚምባብዌ ሕዝብ መካከል 85% ኤም ዲ ሲ ወሳኝ አስተዋፅዖ አድርጓል ብሎ ያምናል። እንዲያውም፣ ቀውስ በሚታይበት ባሁኑ ጊዜ ለምን እንደገና የብሔራዊ አንድነት መንግሥት አይመሠረትም በማለት እስከመጠየቅ ርቆ ሄዷል። ምክንያቱም ያኔ ኤም ዲ ሲ የመንግሥቱ አካል ስለነበረ፣ ሁኔታዎች በጉልህ ተሻሽለው ነበር። »
እና ዛሬ የሚጠናቀቀው ጉባዔ ኤም ዲ ሲ የአባላቱን ተሳትፎ እንደገና እንዲያነቃቃ እና ራሱንም እንደገና፣ እንደ መንግሥት ሳይሆን እንደ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ በማዋቀር ለቀጣዩ ምርጫ እንዲዘጋጅ ጥሩ መንገድ ይከፍታል።

Morgan Tsvangirai
ሞርገን ቻንጊራይ- የዚምባብዌ ተቃዋሚ ፓርቲ- የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ መሪምስል Alexander Joe/AFP/Getty Images
Simbabwe simbabwischer Cartoonist
በዚምባብዌ ሰዓሊ የተሰራና ንግሥት ግሪስ የሚል መጠርያ የተሰጠዉ ሥዕልምስል Konrad-Adenauer-Stiftung, Simbabwe


አርያም ተክሌ
አዜብ ታደሰ