1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብጽ ሕዝባዊ ተቃውሞና የኤኮኖሚ ተጽዕኖው

ረቡዕ፣ ጥር 25 2003

በማግሬብ አካባቢ በቱኒዚያ የጀመረው የሕዝብ ዓመጽ አሁን ደግሞ ግብጽን እየናጠ ሲሆን ውጥረቱ በጠቅላላው በአረቡ ዓለም እንዳይስፋፋ በተለይም ገዢዎቹን እያሰጋ ነው።

https://p.dw.com/p/QxfW
ምስል picture alliance/dpa

በአረቡ ዓለም በሕዝብ ብዛት ታላቋ በሆነችው በግብጽ ዓመጹ ከሞላ-ጎደል የአገሪቱን የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ በድን ሲያደርግ በዓለምአቀፍ ደረጃም ተጽዕኖው እያየለ እንዳይሄድ ማሳሰቡ አልቀረም። ውጥረቱ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችን ስጋት እያጠነከረና በዋና ዋና የምንዛሪ ገበዮች ላይ አሻራውን እያሳረፈ ሲሆን ሰሞኑን የነዳጅ ዘይት ዋጋ እንዲንርም አድርጓል። የሕዝቡ ቁጣ በቱኒዚያ የቀድሞውን ገዢ ዚኔ-ቤን-አሊን ለሽሽት ሲዳርግና ሙባራክን ለማንበርከክ ሲቃረብ ስዊዝ ደግሞ አምባገነን ገዢዎች ያሸሹትን ገንዘብ ለመውረስ የሚያስችል አዲስ ሕግ አስፍናለች።

ግብጽ ውስጥ ሰሞኑን ውሏቸውን አደባባይ ያደረጉት የአገሪቱ ዜጎች የሚታገሉት የረጅም ጊዜ ጥም ለሆኑባቸው ለዴሞክራሲና ለፖለቲካ ነጻነት ብቻ አይደለም። በአገሪቱ እያደገ የሚሄደው ኤኮኖሚ ውጤት ተካፋዮች ለመሆንም እንዲሁ ይሻሉ። የግብጽ ኤኮኖሚ ሌላው ቀርቶ በዓለምአቀፉ የቀውስ ዓመት በ 2009 ሳይቀር አምሥት በመቶ ያህል ዕድገት ታይቶበታል። ይሁን እንጂ ሃቁ ሕዝብ በዚሁ ተጠቃሚ ከመሆኑ ይልቅ በኑሮ ውድነትና በሥራ አጥነት መስፋፋት መጠመዱ ነው።
ግብጽ ከ 2004 ዓ.ም. ወዲህ የኤኮኖሚ ፖሊሲዋን ክፍት እያደረገች ስትመጣ ከዚያን ወዲህ ለምሳሌ እስከ ዓለምቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ዋዜማ በያመቱ ሰባት በመቶ ዕድገት አስመዝግባለች። የጀርመኑ የንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቤት ዋና የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ ፎልከር ትራየር እንደሚሉት ግን የኤኮኖሚውን ፖሊሲ ማለዘቡ ይሳካ እንጂ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ የተረፈው የሥራ እጦት ብቻ ነው።

“በኤኮኖሚው የዕድገት ሂደት የሕብረተሰቡ ከፍተኛ መደብ መካበቱና በአንጻሩ ግን ሕዝቡ እንዲሳተፍ አለመደረጉ ከዕውነት የራቀ ነገር አይደለም። ይህንኑም በተለይ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው የትምሕርትና የሥልጠና ይዞታ ግልጽ ያደርገዋል። አዳጊውን ትውልድ ከኤኮኖሚው ለማስተሳሰር እስካሁን ከመንግሥት በኩል በቂ ጥረት አልተደረገም። የኤኮኖሚውን ዕድገት እየጨመረ ከሚሄደው የሕዝብ ቁጥር ጋር በማጣጣሙም ረገድ እንዲሁ!”

የግብጽ ሕዝብ ቁጥር በወቅቱ 84 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጋ ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ግምት በያመቱ ሁለት በመቶ እያደገ የሚቀጥልም ነው። ከዚህ ሌላ በያመቱ ከ 600 እስከ 700 ሺህ ዜጎች በሥራ ገበያው ላይ ተጨማሪ ግፊት ያደርጋሉ። የጀርመኑ የንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቤት ባለሙያ ፎልከር ትራየር እንደሚሉት ታዲያ በየጊዜው ለሚከሰተው የኑሮ ውድነት የነዚሁ ሰዎች በሙያ አለመሰልጠንም አስተዋጽኦ አለው። በወቅቱ የኑሮው ውድነት 11 ከመቶ ይደርሳል።

“ያላንዳች ትምሕርትና ያላንዳች ሥልጠና በምርታማነት ረገድም ዕርምጃ ለማድረግ አይቻልም። እና በራስ ብዙ ማምረት ካልተቻለ ወይም በቂ ምርት ካልተመረተ ለውጭ ዕቃዎች ብዙ መክፈሉ ግድ ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነትን ያስከትላል”

ይህ በተለይም የምግብ ዋጋ እንዳሁኑ በጣሙን በሚንርባቸው ጊዜያት ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው። ግብጽ ዛሬ ከውጭ ከምታስገባቸው ዕቃዎች 14 በመቶው የምግብ ምርቶች ናቸው። የምግብ ዋጋ መናር ደግሞ ይበልጡን የሚያጠቃው ገቢያቸው አነስተኛ የሆነውን ወይም ጨርሶ ሥራ የሌላቸውን ድሆቹን የሕብረተሰብ ዓባላት ነው።

“እርግጥ እነዚህን ሥራ በመስጠት ከአደባባይ ለማንሣት ቢያንስ በያመቱ ስድሥት በመቶ ዕድገት ያስፈልጋል። ይህ የአውሮፓው የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት የ OECD ስሌት ነው። ይሁንና በአሁኑ የቀውስ ሁኔታ ከዚህ ግብ መድረሱ ደግሞ በጣሙን ያዳግታል”
ይህን የሚሉት የጀርመኑ የመካከለኛ ምሥራቅ የንግድና የመዋዕለ-ነዋይ አዋቂ ማርቲን ካልሁፈር ሲሆኑ እንደርሳቸው ዕምነት የወቅቱ ዓመጽ በአገሪቱ የቱሪዝም ንግድ፣ በስዌዝ ካናል መተላለፊያና ግብጻውያን ከውጭ በሚልኩት ገንዘብ ላይም ጎጂ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በዓመጹ የተነሣ ቀጥተኛው የውጭ መዋዕለ-ነዋይ እንዳይተጓጎል ይሰጋሉ። እርግጥ ይህ የባለሙያው ፍርሃቻ ከወዲሁ ዕውን እየሆነ መሄድ መጀመሩም አልቀረም። ለምሳሌ ያህል ታላላቆቹ የጀርመን ,ኩባንያዎች ቢ.አ.ኤስ.ፍ.፣ ዳይምለርና ቢ.ኤም.ደብልዩ. ከወዲሁ ግብጽ ውስጥ ያካሂዱ የነበረውን የምርት ተግባር አቋርጠዋል። እርግጥ ፎልከር ትራየር እንደሚሉት የጀርመን ኩባንያዎች ውሣኔ ጊዜያዊ ነው።

“የጀርመን ኩባንያዎች ይዞታቸውን ጨርሰው እንደማይለቁ እናውቃለን። ግብጽ ውስጥ ሲበዛ ስር የሰደዱ፣ አገሪቱን ጠቃሚና ስልታዊ ገበያ አድርገውም የሚመለከቱ ናቸው። አሁን በወቅቱ ግን መጪውን ከመጠባበቅ ሌላ ምርጫ የለም”

እንግዲህ የአገሪቱ ሁኔታ መልሶ እስከሚረጋጋ ድረስ ተጨማሪ መዋዕለ-ነዋይ እንቅስቃሴ አይኖርም ማለት ነው። አዳዲስ ባለሃብቶችም ቢሆኑ ግብጽ ከወደቀችበት አዘቅት ወጥታ መንገዷ እስኪለይለት ድረስ መጠበቁን እንደሚመርጡ አንድና ሁለት የለውም። በሌላ በኩል አገሪቱ በዴሞክራሲ አቅጣጫ ለማምራት ከቻለች፣ ሕዝቡም ለበለጠ የሙያ ስልጠናና የኤኮኖሚ ተሳትፎ ከበቃ መዋዕለ-ነዋይን መልሳ እንደምትማርክ የአረቡ ዓለም ሁኔታ አዋቂ የካልሁፈር ተሥፋ ነው።

“በወቅቱ ግብጽ በዚህ ገንቢ አቅጣጫ ማምራት መጀመሯን ለመለየት ጊዜው ገና ትኩስ ነው። መንግሥት በወቅቱ ወደፊት ከመራመድ ይልቅ በኋልዮሽ አቅጣጫ የሚሄድ ነው የሚመስለው። እንግዲህ የሚቀረው የዴሞክራሲ መቆናጠጥ ተሥፋ ብቻ ነው። ይህ ከተሳካ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ተመልሰው ይመጣሉ”

ስዊዝና የአምባገነኖች ገንዘብ ሕግ

የአንድ ፓርቲና ግለሰብ አገዛዝ ለዓመታት በሰፈነባቸው አገሮች ሙስና፣ የጥቂቶች መካበትና የብዙሃኑ መራቆት ትናንትም ዛሬም የስርዓቱ መለያ ነበሩ፤ ናቸውም፤ እንደሆኑም ቀጥለዋል። ለምሳሌ ሟቹን የዴሞክራቲክ ሬፑብሊክክ ኮንጎ አምባገነን ገዢ ሞቡቱ-ሤሤ-ሤኮን ወይም የሃኢቲ መሰላቸውን ዱቫልዬን ለመጥቀስ፤ እነዚህና መሰሎቻቸው ከሕዝቦቻቸው የዘረፉትን ሃብት በስዊስ ባንክ ያከማቹ ነበር፤ ዛሬም ያከማቻሉ።
ይሄው ገንዘብ በትክክል ምን ያህል እንደሚሆን በውል አይታወቅም። በጥቅሉ የሚገመተው ግን ከ 150 ሚሊያርድ ዶላር እንደሚበልጥ ነው። ለአምባገነኑ ወሮበላ ገዢዎች ይህን አመቺ የዝርፊያ ሁኔታ የፈጠረው ደግሞ የስዊስ ባንኮች የሚስጥር አያያዝ የአሠራር ዘይቤ ነበር። አገሪቱ አሁን አንድ አዲስ ሕግን በማስፈን ይህን የአሠራር ዘይቤ ለማብቃትና የተዘረፈው ገነዘብ ለባለቤቶቹ እንዲመለስ ለማድረግ ተነስታለች።

ማለት ስዊዝ በአዲሱ ሕግ አማካይነት ገንዘቡን በፍጥነት በመውረስ ለሕጋዊ ባለቤቱ ለማስረከብ ነው የምትፈልገው። እስካሁን በነበረው አሠራር የስዊትዘርላንድ መንግሥት በጉዳዩ የሚያተኩረው የአገሪቱ የሕግ ዘርፍ ባልደረባ ቫሌንቲን ሤልቬገር እንደሚያስረዱት የሚመለለከተው አገር በቀድሞ አምባገነን ገዢው ላይ የወንጀል ምርመራ ሲከፍት ብቻ ነበር።

“ባለፉት ጊዜያት እንደታዘብነው የሚያሳዝን ሆኖ ይህን መሰሉን የወንጀል ምርመራ ችሎት ለመክፈት የማይችሉት ሃገራት ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። በዚሁ የተነሣም ገንዘቡ ያላግባብ መልሶ ከዘራፊው ወይም ከቤተሰቡ ዕጅ እንዳይገባ አዲስ ሕግ እናቀርባለን። ይህም ስዊዝ ራሷ ጭብጥ ሆኖ በተደነገገ ሁኔታ ገንዘቡን እንድትወርስና ለተዘረፈው ሕዝቡ እንድታስረክብ የሚያስችል ይሆናል”

በቀድሞው ሕግ መሠረት ስዊዝ አምባገነኑን ለመውረስ ገንዘቡን በሕገ ወጥ-መንገድ ለማግኘቱ መረጃ ማቅረብ ነበረባት። ይህ ደግሞ እጅግ አድካሚና የማይቻል ነገር ነበር። በዚሁ የተነሣም ስዊዝ ስምንት ሚሊዮን ፍራንክ የሚጠጋ የዛኢርን ሕዝብ ገንዘብ ለሞቡቱ ቤተሰብ ማስተላለፍ ተገዳለች። አሁን በአዲሱ ሕግ መሠረት ገንዘቡ በተገቢ መንገድ የተገኘ መሆኑን ማረጋገጥ የሚኖርበት ራሱ አስቀማጩ ነው። ይህም ሤልቬገር እንደሚያምኑት ገንዘቡ ለሕዝብ እንዲደርስ ሕጋዊ ሁኔታን የሚያመቻች ይሆናል።

“ገንዘቡ በእርግጥም ለሕዝብ ጥቅም እንዲውልና ከአንድ ስውር ቀዳዳ ገብቶ እንዳይቀር ለማድረግ አስፈላጊውን ማረጋገጫ ዘዴ እንፈጥራለን”

ስዊትዘርላንድ በአምባገነኖች የተዘረፈ ገንዘብን ለመመለስ ለረጅም ጊዜ ስትጥር ቆይታለች። በአንዳንድ ሁኔታም ስኬት መታየቱ አልቀረም። ለምሳሌ ፊሊፒንስ ፈርዲናንድ ማርቆስ ካከማቹት ሃብት የተወሰነውን ሚሊዮን ስታገኝ ለናይጄሪያ ደግሞ ሣኒ አባቻ የዘረፉት 700 ሚሊዮን ዶላር ተመልሷል። የሃኢቲው የቀድሞ አምባገነን ገዢ ዣን-ክላውድ-ዱባልዬር ያካበቱትን ሃብት በተመለከተ ግን የአስካሁኑ ሕግጋት ለውሣኔ የሚያበቁ አልሆኑም። እርግጥ በአዲሱ ሕግ ዱቫልዬም ሊወረሱ ይችላሉ። የቱኒዚያም ሕዝብ ዕድል አሻለ ነው የሚሆነው።

እርግጥ የተባለው አዲስ ሕግ በተግባራዊ አተረጓጎሙ ረገድ ምን ያህል ፍቱን እንደሚሆንና ለውጥ እንደሚያሳይ ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው። ይሁን እንጂ የሕዝብን ገንዘብ እየዘረፉ ወደ ውጭ ባንኮች ለሚያሸሹት የዓለማችን አምባገነን ገዢዎች ከወዲሁ አስደንጋጭ መልዕክት ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ