1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብፅ አውሮፕላን ስብርባሪዎች እና የመንገደኞች አካላት ተገኙ

ዓርብ፣ ግንቦት 12 2008

ሐሙስ ዕለት ከፓሪስ ወደ ካይሮ ሲበር እየተመዝገዘገ የሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ የተከሰከሰው የግብጽ አውሮፕላን የአብራሪ ክፍል ውስጥ ጭስ ተከስቶ እንደነበር የፈረንሳይ የበረራ አደጋ ባለሙያዎች ቅዳሜ አስታወቁ። ኤር ባስ 320 አውሮፕላን 66 ሰዎችን ጭኖ እንዴት ሊከሰከስ እንደቻለ ግን መርማሪዎች አሁንም ፍንጭ አላገኙም።

https://p.dw.com/p/1Is5A
EgyptAir MS804 Wrackteil
ምስል picture-alliance/abaca

ምናልባት ግን የሽብር ጥቃት ተሰንዝሮበት ሊሆን ይችላል የሚለው መላ ምት ማመዘኑ ተጠቅሷል። ከራዳር ውጪ ተሰውሮ የተከሰከሰው ኤርባስ አውሮፕላን ዐሥር የበረራ ሠራተኞችን እንዲሁም 56 መንገደኞችን አሣፍሮ ነበር። በአውሮፕላኑ ውስጥ ሁለት ጨቅላዎች እና አንድ ህፃንን ጨምሮ፤ 30 ግብፃውያን፣ 15 ፈረንሣውያን፣ ሁለት ኢራቃውያን፣ ሁለት ካናዳውያን እንዲሁም አንድ አልጀሪያዊ፣ ቤልጂጋዊ፣ የብሪታንያ ዜጋ፣ ቻዳዊ፣ የፑርቹጋል ዜጋ፣ ሥዑዲ ዐረቢያዊ እና ሱዳናዊ መንገደኞች ይገኙ ነበር። 66 ሰዎችን እንዳሳፈረ የተከሰከሰው አውሮፕላን 150 ሰዎችን የማሣፈር አቅም ነበረው። አውሮፕላኑ ወደ ፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ከመድረሱ በፊት ከግብጽ መዲና ካይሮ በመነሳት ቱኒዝያ እና ኤርትራ የነበረውን የበረራ ጉዞ ማከናወኑም ተዘግቧል።

የግብፅ ጦር ቃል አቀባይ፣ ብርጋዴር ጀነራል ሞሀመድ ሳሚር ዛሬ ጠዋት በፌስቡክ ገጻቸው እንዳስነበቡት የግብጽ አየር ኃይል እና ባህር ኃይል ባልደረቦች የአውሮፕላኑን ስብርባሪዎች እና የመንገደኞችን ንብረቶች ከወደብ ከተማዋ ከአሌክሳንድሪያ በስተሰሜን 290 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አግኝተዋል። የግብፅ የፈረንሳይ እና የብሪታንያ መርማሪዎች እንዲሁም የኤር ባስ ባልደረባ፣ ስብርባሪዎቹን በጋራ እንደሚመረምሩ የግብፅ ባለስልጣናት አስታውቀዋል። የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ዛሬ ባወጡት መግለጫ በአደጋው ለሞቱት 66 ሰዎች ቤተሰቦች የተሰማቸዉን ጥልቅ ሐዘን ገልፀዋል። ይህ የፕሬዝዳንቱ መግለጫ የግብፅ መንግሥት አውሮፕላኑ መከስከሱን ያረጋገጠበት የመጀመሪያ ይፋ መግለጫ ተደርጎ ተወስዷል። እስካሁን አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ምክንያት በግልፅ አልታወቀም። ሆኖም የግሪክ መከላከያ ሚኒሥትር ፓኖስ ካሜኖስ አውሮፕላኑ ቀርጤስ በተባለው የግሪክ ደሴት የአየር ክልል ውስጥ ወደ ግራና ወደቀኝ ሲዞር መታየቱን ተናግረው ነበር።
«አውሮፕላኑ መጀመሪያ 90 ዲግሪ ወደ ግራ ከዞረ በኋላ ወደ ቀኝ 360 ዲግሪ ዞሮ ከ11 ሺህ ወደ 4500 ሜትር ከወረደ በኋላ ከራዳር እይታ ተሰውሯል ።»

Ägypten Flugzeug A320 der EgyptAir
ምስል Reuters/C. Hartmann


የግብጽ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ከአብራሪው በኩል ምንም አይነት የአደጋ ጥሪ ባለመሰማቱ አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በአሸባሪዎች ጥቃት ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬያቸዉን ተናግረዋል። የግብጽ የአየር ትራንስፖርት ሚኒስትር ሸሪፍ ማቲ፤
«ሁኔታው በአግባቡ ሲተነተን ከቴክኒክ ችግር ይልቅ የተለየ እንቅስቃሴ ወይም ደግሞ የሽብር ጥቃት ደርሶ ሊሆን የመቻሉ ዕድል ከፍተኛ ነው። »

አሁንም በቀጠለው ፍለጋ ፈረንሳይ፣ ግሪክ፣ ኢጣልያ፣ ቆጵሮስ እና ብሪታኒያ፤ ከግብጽ ጋር በትብብር እየሠሩ ነው። 66 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረው ይኽው አውሮፕላን ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ፣ ከለሊቱ 8 ሰአት ከ45 ላይ በሜዲቴራንያ ባህር ላይ በመብረር ላይ ሳለ ነበር ከራዳር ዕይታ የሰወረው።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ