1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 30 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 30 2013

እድሜያቸው ከ21 በታች የአውሮጳ እግር ኳስ ተጨዋቾች የፍጻሜ ውድድር በጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሸናፊነት ተጠናቋል። ዋናው ብሔራዊ ቡድን የነገ ሳምንት ለአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) የምድብ ግጥሚያ የፈረንሳይ ቡድን ይጠብቀዋል። የቤርሊን ማራቶን ዳግም ሊመለስ ይመስላል።

https://p.dw.com/p/3uYJN
Berlin Marathon 2019
ምስል Imago Images/A. Gora

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

እድሜያቸው ከ21 በታች የአውሮጳ እግር ኳስ የፍጻሜ ውድድር በጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሸናፊነት ተጠናቋል። ዋናው ብሔራዊ ቡድን የነገ ሳምንት ለአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) የምድብ ግጥሚያ የፈረንሳይ ቡድን ይጠብቀዋል። ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፋን ሐሰን በኢትዮጵያዊቷ አትሌት አልማዝ አያና ላለፉት አምስት ዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን መስበር ችላለች። ስለ አትሌቷ እና ቀጣይ ፉክክር የሚያብራራልን የስፖርት ጋዜጠኛ አነጋግረናል። የቤርሊን ማራቶን መስከረም ወር ላይ ሊካኼድ ይችላል ተብሏል።

እግር ኳስ

እድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች ተጨዋቾች በሚሳተፉበት  የአውሮጳ እግር ኳስ የፍጻሜ ውድድር የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዋንጫውን ማንሳት ችሏል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የፖርቹጋል አቻውን ያሸነፈው 1 ለ0 ነው። ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ 49ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ከናይጄሪያዊ አባት እና ከጀርመናዊት እናት ሐምቡርግ ከተማ ውስጥ የተወለደው ሉቃስ ንሜቻ ነው። አጥቂው ሉቃስ በአሁኑ ወቅት የሚጫወተው ቤልጂየም ውስጥ በሚገኘው አር ኤስ ሲ አንደርሌሽት ቡድን ውስጥ ነው። ጀርመን ፖርቹጋልን አሸንፋ ዋንጫ በወሰደችበት የስሎቬኒያ ዋና ከተማ ልዩብሊያና ከተማ ውስጥ በሚገኘው የኤስ አር ሲ ስቶሲች ስታዲየም የፍጻሜውን ግጥሚያ አራት ሺህ ስምንት መቶ ሰማንያ ሦስት ታዳሚያን ተገኝተው ተከታትለዋል።  የጀርመን ቡድን ከሦስት ዓመት በፊትም በፍጻሜ ግጥሚያ ድል አድርጎ ዋንጫ መውሰዱ ይታወሳል።

Fussball I UEFA U21 I Deutschland v Niederlande
ምስል Bernadett Szabo/REUTERS

ለአውሮጳ ሻምፒዮን እግር ኳስ ግጥሚያ የፊታችን ዐርብ ማታ ጣሊያን ከቱርክ ጋር የዙር ግጥሚያቸውን ያደርጋሉ። በበነጋታው ቅዳሜ ስዊዘርላንድ ከዌልስ፣ ዴንማርክ ከፊንላንድ እንዲሁም ቤልጂየም ከሩስያ ጋር ይጋጠማሉ። እሁድ ዕለት በሚደረጉ ግጥሚያዎች እንግሊዝ ከክሮሺያ፣ አውስትሪያ ከሰሜን መቄዶኒያ እንዲሁም ኔዘርላንድ ከዩክሬን ጋር ይፋለማሉ። የዛሬ ሳምንት ደግሞ፦ ስኮትላንድ ከቼክ ሪፐብሊክ፣ ፖላንድ ከስሎቫኒያ እና ስፔን ከስዊድን ጋር ይጫወታሉ። በበነጋታው ማክሰኞ ሐንጋሪ እና ፖርቹጋል ይጋጠማሉ። ከሁለቱ ጨዋታ ቀጥሎ ማክሰኞ ምሽት ፈረንሳይ እና ጀርመን የሚያደርጉት ፍልሚያ በበርካቶች ዘንድ ይጠበቃል።

አትሌቲክስ

በዜግነት ኔዘርላንዳዊቷ ትውልደ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሲፋን ሐሰን በ 10,000 ሜትር የሴቶች የሩጫ ውድድር አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገበች። ሲፋን ትናንት ኔዘርላንድስ ሄንገሎ ከተማ ውስጥ በተተካሄደው ውድድር ያሸነፈችው 29 ደቂቃ ከ06 ነጥብ 82 ሰከንድ በመሮጥ ነው። ተወልዳ ከአደገችበት ኢትዮጵያ በ15 ዓመቷ ወደ ኔዘርላንድስ የሄደቸው ሲፋን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 ዓ.ም የኔዘርላንድስ ዜግነት አግኝታለች።  ሲፋን ከውድድሩ በኋላ ያስመዘገበችውን ውጤት አስመልክቶ በተደረገላት ቃለ መጠይቅ  የደች ደጋፊዎቿ በተገኙበት በመሆኑ ይበልጥ እንዳስደሰታት ተናግራለች። ሲፋን ትናንት በ11 ሰከንድ ገደማ ያሻሻለችው ክብረ ወሰን በኢትዮጵያዊቷ አልማዝ አያና እጎአ በ 2016 ዓ ም ሪዮ ላይ የተመዘገበው ነው።  ሲፋን የትናንትናውን ክብረ ወሰን ጨምሮ በጠቅላላው አራት ክብረ ወሰን አስመዝግባለች።

Leichtathletik-WM Doha 2019 Frauen Finale 1500 Meter Sifan Hassan
ምስል Reuters/D. Martinez

የቤርሊን ማራቶን

በኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ምክንያት ተስተጓጉሎ የነበረው የቤርሊን ማራቶን ዳግም ሊመለስ ይመስላል። የቤርሊን ማራቶን አዘጋጆች መስከረም ወር ውስጥ የሩጫ ውድድሩ ዳግም ጀምሮ 35,000 ሰዎች ይፎካከራሉ የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።  አዘጋጆቹ እና የቤርሊን ከተማ ሴኔት በጋራ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ዕንዳስታወቁት፦ ከቤርሊን ማራቶን አስቀድሞ ለሙከራ ሁለት ውድድሮች ይከናወናሉ። በሐምሌ ወር ውስጥ የዐሥር ሺህ ሜርትር የሩጫ ፉክክር፤ ከዚያም ነሐሴ ወር ውስጥ ደግሞ የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድሮች ይከናወናሉ ተብሏል።

የቤርሊን ማራቶን አዘጋጆች ውድድሩን ዕውን ለማድረግ የሩጫው ተሳታፊዎች በአጠቃላይ ሙሉ ለሙሉ ጸረ ኮሮና ተሐዋሲ ክትባት የተከተቡ አለያም ከተሐዋሲው ነጻ ለመሆናቸው ምርመራ ያደረጉ መኾን ይገባቸዋል ብለዋል። እንዲያም ኾኖ የቤርሊን ከተማ ውድድሩ ስለመከናወኑ ሙሉ ማረጋገጫ ገና አልሰጠም። የከተማዋ የሴኔት አባል አንድሪያስ ጋይዘ፦ «የቤርሊን ማራቶን በእርግጠኝነት ይካኼዳል ብሎ መናገር አይቻልም፤ ኾኖም ሊካኼድ የሚችልበት አጋጣሚ አለ» ብለዋል። በአጠቃላይ የቤርሊን ማራቶን ዕቅድ የሚሳካ ከሆነ ውድድሩ መስከረም 16 ቀን፣ 2014 ዓም ነው የሚከናወነው።  የቤርሊን ማራቶን ይፋዊ ክብረወሰን የተያዘው በኬንያዊው ሯጭ ኤሊውድ ኪፕቾጌ ነው። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 ኬኒያዊው አትሌት ክብረወሰን የሰበረው ሁለት ሰአት ከአንድ ደቂቃ ከ39 ሰከንድ በመሮጥ ነው። በወንዶች የማራቶን የፉክክር ታሪክ ሦስቱ ፈጣን ሰአቶች የተመዘገቡትም በዚሁ የቤርሊን ማራቶን ፉክክር እንደኾነ ይታወቃል።

Tennis | Australian Open | Daniil Medvedev - Novak Djokovic
ምስል William West/AFP/Getty Images

የሜዳ ቴኒስ

ፈረንሳይ ውስጥ በተከናወነው የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ሠርቢያዊው የዓለማችን ድንቅ ተጫዋች ኖቫክ ጄኮቪች የጣሊያኑ ተፎካካሪ ሎሬንትሶ ሙሴቲን አሸንፏል። ዛሬ በተከናወነው ውድድር ኖቫክ ጄኮቪች የ19 ዓመቱ ተፎካካሪውን ያሸነፈው 6 ለ1 እና 6 ለ0 ነው። በአራት ዙር በተከናወነው ግጥሚያ ሎሬንትሶ ሙሴቲ የመጀመሪያ ሁለቱን ግጥሚያዎች በተከታታይ 7 ለ6 አሸንፎ ነበር። በኋላ ላይ ግን የ34 ዓመቱ ኖቫክ ጄኮቪች ብርቱ ኾኖ በመቅረብ ሁለቱን ዙር ግጥሚያዎች በሰፋ የነጥብ ልዩነት ማሸነፍ ችሏል። ኖቫክ ጄኮቪች እስካሁን ድረስ ለ18 ጊዜያት የዓለም የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያዎች ፍጻሜ ላይ ድል የተቀዳጀ ብርቱ ተጋጣሚ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ