1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጎርፍ ስጋት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች

ሐሙስ፣ ግንቦት 16 2010

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ በሆነ ዝናብ ድንገተኛ ጎርፍ ሊያጋጥም እንደሚችል የኢትዮጵያ የብሄራዊ ሜትርዮሎጅ አገልግሎት ድርጅት አመለከተ። የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ የሚመጣዉን አደጋ ለመከላከል ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። 

https://p.dw.com/p/2yDDb
Flutkatastrophe in Malawi Januar 2015
ምስል picture-alliance/dpa/E. Waga

Flood catastrophe in Ethiopia - MP3-Stereo

 አደጋዉ ይከሰትባቸዋል በተባሉ ቦታዎችም  ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠቱንም ገልጿል። ከህንድ ዉቅያኖስና ከኤደን ባህረሰላጤ በሚነሳ ሙቀት ያዘለ ማዕበል ሳቢያ የምሥራቅ አፍሪቃ አገሮች ላለፉት 3 ዓመታት አጋጥሞ ከነበረዉ የድርቅ አደጋ በተጨማሪ በዘንድሮዉ ዓመት በከባድ ጎርፍ ሊመቱ እንደሚችሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የአየር ትንበያዎች  ሲያስጠነቅቁ  ቆይተዋል።  ከዚህ የተነሳም በግንቦት ወር ብቻ  «ሳጋር» የተባለው ማዕበል ባስከተለዉ ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ በሶማሊያ፣ በጅቡቲ በኬንያና በዩጋንዳ  በርካታ ሰዎች ሲሞቱ በመቶ ሽህ የሚቆጠሩት ደግሞ ከቤት ንብረታቸዉ መፈናቀላቸዉን ዘገባዎች ያሳያሉ።   በኢትዮጵያም  እንደገለፀዉ የዘንድሮዉ የበልግ ወቅት ካላፉት 10 ዓመታት ጋር ሲነጻጸር  በጣም የተስፋፋ ዝናብ የነበረዉ በመሆኑ በሶማሌ ክልልና በሌሎች  የሀገሪቱ አንዳንድ ደቡብና ደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች ቅፅበታዊ ጎርፍ አጋጥሞ እንደነበር የኢትዮጵያ የብሄራዊ ሜትሮሎጅ  ድርጅት ገልጿል።
ሰሞኑን ከኤደን ባህረ ሰላጤ ዝቅተኛ የአየር ግፊት ጋር ተያይዞ ከተከሰተዉ  «ሳጋር» ከተሰኜ ማዕበል  ጋር በተገናኘ ግን እስካሁን በኢትዮጵያ ሁለት ቦታዎች ብቻ ከፍተኛ ዝናብ ከመመዝገቡ ዉጭ  የጎርፍ አደጋ አላስከተለም ሲል ድርጅቱ ጠቅሷል ። ያም ሆኖ ግን  እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ባለዉ ጊዜ ከመደበኛ በላይ በሆነ ዝናብ ሳቢያ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል የድርጅቱ የሜትሪዮሎጅ ትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሳምነዉ ተሾመ ለዶይቼ ቬለ ገልፀዋል። «ይህ ወር ግንቦት ማለት የበልግ የመጨረሻዉ ወር ነዉ።በልግ ማለት ከየካቲት እስከ ግንቦት ያሉትን ወራት ያጠቃልላል ማለት ነዉ።ስለዚህ አሁንም ከግንቦት መጨረሻዎቹ  ድረስ አብዛኛዉ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገራችን ቦታዎች ላይ የተስፋፋ  የደመና ክምችት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ስፍራዎች ከፍ ያለ ዝናብ የሚጠበቅ ይሆናል። ከባድ መጠን ያለዉ ዝናብ ድግግሞሹ በሚበዛበት ጊዜ ቅፅበታዊ ጎርፍ የማስከተል ዓቅም ሊኖረዉ ይችላል ማለት ነዉ።ስለዚህ በዚያ ላይ ትንበያዎችን በማዘጋጀት ለሚመለከታቸዉ ባለ ድርሻ አካላት እየሰጠን እንገኛለን።»ነበር ያሉት።

Flutkatastrophe in Malawi Januar 2015
ምስል AFP/Getty Images/A. Gumulira


የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንም ከብሄራዊ ሜትሪዮሎጅ፣ ከዉኃና መስኖ ልማት ድርጅት አገኘሁት ባለዉ መረጃና ኮሚሽኑ በራሱ ባደረገዉ ጥናት  መሠረት ከመደበኛ በላይ በሆነ ዝናብ በመጭዎቹ የክረምት ወራት የጎርፍ አደጋ ያጋጥማቸዋል ለተባሉ ቦታዎች ቅድመ ማስጠንቀቂያ እየሰጠ መሆኑን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘዉዴ አብራርተዋል።

« በግንቦት ወር ዝናብ የተለመደ አይደለም።ግን እየዘነበ ነዉ።ይህ ዝናብ ደግሞ ከመደበኛዉ በላይ ስለሚዘንብ በተለይም «ሳይክሎ» ተብሎ በሚጠራዉ ማዕበል ባመጣዉ ተፅዕኖ ምክንያት በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል  በተለይም በፋፈንና ሽኪ ዞን እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል።»ካሉ በኋላ በድሬደዋም ቅድመ ማስጠንቀቂያዉ መሰጠቱን አክለዋል።
ኅብረተሰቡ ስለአደጋዉ እንዲያውቅም የማኅበረሰብ ሬዲዮዎችና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም በተለያዩ ቋንቋዎች የቅድመ ጥንቃቄ መልዕክቶች እንዲተላለፉ እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊዉ ተናግረዋል። ጎርፍ ከቆሻሻ ጋር ተደባልቆ የጤና ጠንቅ እንዳያስከትልም ኅብረተሰቡ በዉኃ መውረጃ ቦዮች ላይ ቆሻሻ ከመጣል እንዲቆጠብ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ አቶ ደበበ ገለፃ ኮሚሽኑ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባለፈ የግብርና፣ የጤና ጥበቃ፣ የዉኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስትሮችንና  ሌሎች የሚመለከታቸዉ አካላትን ባካተተ ግብረ ኃይል አማካኝነት አደጋዉ በሰውና በንብረት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል እየሠራ ነዉ።
በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሶማሌ ክልል 163 ሺህ ሰዎች በጎርፍ የተጠቁ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ 98 ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ መፈናቀላቸዉን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ሰሞኑን አመልክቷል። ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ፤ በባሌ፤ በቦረና፤ በምሥራቅና ሞዕራብ ሐረርጌ እንዲሁም በጉጅ ዞኖችም ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ እንደነበር የድርጅቱ ዘገባ ያሳያል።
በኢትዮጵያ በድርቅ፣ በጎርፍ አደጋ እንዲሁም በየቦታዉ በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታ ፈላጊ መሆናቸዉንም የተለያዩ ዘገባዎች ያሳያሉ።

Ägypten Flutkatastrophe
ምስል picture-alliance/dpa/I. Sayed

ፀሐይ ጫኔ
ሸዋዬ ለገሰ