1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጎሳ ግጭት በደቡባዊ ሱዳን

ቅዳሜ፣ መስከረም 16 2002

በደቡብ ምስራቃዊ ሱዳን ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ በመታየት ላይ ያለው የጎሳ ግጭት ለብዙ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኖዋል። በሉዎ ኑርና በዲንካ ሆል ጎሳ ቡድኖች መካከል የሚካሄደው ውጊያ አሁንም ገና ጨርሶ አላበቃም።

https://p.dw.com/p/JorZ
የደቡብ ሱዳን ፖሊስና ወታደሮችምስል AP

ባለፈው የሳምንት መጨረሻ ሁለቱ ጎሳዎች በጆንግሌይ አካባቢ ባካሄዱት ውጊያ ከእድ መቶ የሚበልጡ ሰዎች ተገድለዋል፤ ሁለት መቶ ስድሳ ጎጆዎች በእሳት ጋይተዋል፤ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችም የሚሊሺያዎቹን ጥቃት ለማምለጥ እያሉ ሸሽተዋል።
ካለፈው ታህሳስ ወር የመጨረሻ ሳምንት ወዲህ በዚሁ አካባቢ በተካሄዱ ተመሳሳይ ጥቃቶች ከሁለት ሺህ የሚበልጥ ሰው ሲገደል፡ ወደ ሀት መቶ ሀምሳ ሺህ ሰው ደግሞ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎዋል። የአፍሪቃ ህብረት በጥብቅ ያወገዘው በሁለቱ ጎሳዎች መካከል በጆንግሌይ አካባቢ ለቀጠሉት ግጭት መንስዔው፡ በእንግሊዝኛ አጠራሩ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የሚባለው ለዓለም አቀፍ ውዝግቦች የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርበው ድርጅት የአፍሪቃ ቀንድ ፕሮዤ ዋና ስራ አስኪያጅ ዚጄ ሆህኑር እንደሚሉት፡ የመሬት ጥያቄ ሊሆን ይችላል።
« እርግጥ ማንም የችግሩን መንስዔ በውል አያውቀውም። ግን በመሬት ሰበብ የተፈጠረ ውዝግብ መሆኑ ይጠረጠራል። ሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች ይገባናል የሚሉዋቸው ለግጦሽ የሚያስፈልጉ ቦታዎችንና ለግብርናው ተግባር የሚያገለግል መሬትን የሚመለከት እንደሆነ ይገመታል። »
እርግጥ፡ በውኃ፡ በቀንድ ከብትና በግጦሽ መሬት ሰበብ በዚሁ አካባቢ ውዝግቡ ከብዙ ጊዜ ወዲህ መኖሩ አዲስ ነገር አይደለም። ነገር ግን፡ ምንም እንኳን አሁን ግጭቱ ጥቂት በረድ ቢልም፡ በየጊዜው በሚነሳው ውጊያ ሰበብ ያካባቢው ሁኔታ ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን ለዓለም አቀፍ ውዝግቦች የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርበው ድርጅት የአፍሪቃ ቀንድ ፕሮዤ ዋና ስራ አስኪያጅ ዚጄ ሆህኑር አስረድተዋል።
« እስከምናውቀው ድረስ፡ ካለፈው እሁድ ወዲህ አዲስ ግጭት አልተፈጠረም። ይሁንና፡ ይህ በጆንግሌይ አካባቢ በተለያዩት ጎሳዎች መካከል የታየው የኃይል ተግባር መቀጠሉ አይቀርም የሚል ስጋት አለን። »
ዚጄ ሆህኑር እንዳመለከቱትም፡ የሰሞኑን ዓይነት ደም አፋሽሳ ግጭት እንዳይደገም የደቡብ ሱዳን መስተዳድር ሁነኛ ርምጃ እንዲወስድ ድርጅታቸው አሳስቦዋል።
« የደቡብ ሱዳን መስተዳድር ኃላፊ በጠቅላላ በደቡባዊ ሱዳን የጸጥታ ኃይላት ህልውናን እንዲያጠናክሩ አሳስበናል። እርግጥ፡ ደቡብ ሱዳን ግዙፍ አካባቢ ነው፡ እና የደቡብ ሱዳን መስተዳድርም አስፈላጊ የሆነው የጸጥታ ኃይል የለውም። እንደምታውቁት፡ ባለፈው የሳምንት መጨረሻ የተካሄደው ግጭት የብዙ ፖሊሶችና የሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ እንቅስቃሴ አባላትንም ጭምር ሞት አስከትሎዋል። »
በደቡብ ሱዳን ለሀያ ሁለት ዓመታት የተካሄደው የርስበርስ ጦርነት እአአ በ 2005 ዓም በሰሜን እና በደቡብ ሱዳን መካከል በናይቫሻ ኬንያ በተፈረመ የሰላም ውል ቢያበቃም፡ የወቅቱ የጎሳ ግጭት አካባቢውን እንደገና ወደተመሳሳይ ውዝግብ ማጥ እንዳይመልሰው የአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ ስጋት አድሮበታል፤ እንደ ለዓለም አቀፍ ውዝግቦች የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርበው ድርጅት የአፍሪቃ ቀንድ ፕሮዤ ዋና ስራ አስኪያጅ ዚጄ ሆህኑር ገለጻ።
« አዎ፡ የሰላሙ ውል ባጠቃላይ ሲታይ የተሳካ ውጤት አስገኝቶዋል። እንደምታውቁት፡ ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ ሱዳን ውስጥ ይህ ነው የሚባል መጠነ ሰፊ ውዝግብ አልተካሄደም። ግን ይህ የሰላሙ ውል ትክክለኛ ነው ማለት አይደለም። በሰሜኑና በደቡቡ መካከል በሰላሙ ውል ይዘት ላይ፡ ለምሳሌ የፊታችን ሚያዝያ በሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ እና እአአ በ 2011 ዓም በሚካሄደው ሬፈረንደም ጥያቄ ሰበብ፡ በርካታ ልዩነቶች ተፈጥረዋል። »
አዘውትሮ በግጦሽ መሬት ሰበብ የሚካሄደው ውጊያ ካካባቢው ውጭ ባሉ ወገኖች ነው የሚቀሰቀሰው የሚል ጥርጣሬ ይሰማል። የሱዳም ፕሬዚደንት ኦማር ሀሳን ኧል በሺር የሚመሩት ገዢው የብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲያቸው ያካባቢውን ጸጥታ ለማናጋት እያለ ለጎሳው ጥቃት ተጠያቂ የሚባሉትን ሚሊሺያዎች የጦር መሳሪያ ያስታጥቃል በሚል የደቡብ ሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ እንቅስቃሴ ወቀሳ አሰምተዋል። ይሁንና፡ ለዓለም አቀፍ ውዝግቦች የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርበው ድርጅት የአፍሪቃ ቀንድ ፕሮዤ ዋና ስራ አስኪያጅ ዚጄ ሆህኑር እንዳስታወቁት፡ ይህንኑ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናትን ወቀሳ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አልተገኘም።
« የሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ እንቅስቃሴ ደጋግሞ ወቀሳ መሰንዘሩን በርግጥ እናውቃለን። ይሁንና፡ የተባለውን ወቀሳ የሚያረጋግጥ ሁነኛ ማስረጃ አልቀረበም። ይህ ግን ሚሊሺያዎቹ የጦር መሳሪያ አያገኙም ማለት አይደለም። ግን፡ ጉዳዩ፡ የሱዳን ብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲ በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የተለያዩ ቡድኖችን በርግጥ የጦር መሳሪያ ያስታጥቃል የተባለበትን ወቀሳ የሚደግፍ መረጃ አለመቅረቡ ነው። »
የጎሳው ግጭትና የደቡብ ሱዳን መስተዳድር ባለስልጣናት ወቀሳ ከአራት ዓመት በፊት የተፈረመውንና አሁንም እክል ያላጣውን በሰላም ውል ላይ የሚታየውን ውጥረት እያካረረው ተገኝቶዋል። እንደሚታወሰው፡ በሰላሙ ውል መሰረት፡ በደቡብ ሱዳን ስድስት ዓመት የሚቆይ ሰፊ ራስ ገዝ አስተዳደር የተመሰረተ ሲሆን፡ የዚሁ አካባቢ ህዝብ እአአ በ 2011 ዓም የራሱን ዕጣ ፈንታ ፡ ማለትም፡ አንድም ከሱዳን ጋር ተጠቃሎ ለመኖር ወይም ተገንጥሎ ነጻ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለው ሬፈረንደም እንዲያካሂድ፡ እንዲሁም፡ በአስር ዋነኛ ጉዳዮች፡ ብሎም፡ ለምሳሌ ፡ የፊታችን ሚያዝያ በሚካሄደው አጠቃላይ ምክር ቤታዊ ምርጫ፡ በዳርፉር ሰላም በማውረዱ ጥረት፡ የሰሜንና የደቡብ የሀገሪቱን ድንበር በማካለሉና በስልጣን ክፍፍሉ ጥያቄዎች ላይ ተባብረው ለመስራትም ሁለቱ ወገኖች ተስማምተዋል። ይሁንና፡ በዓለም አቀፍ ደረካ ለሚነሱ ውዝግቦች የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርበው ድርጅት የአፍሪቃ ቀንድ ፕሮዤ ዋና ስራ አስኪያጅ ዚጄ ሆህኑር እንዳስረዱት፡ በሬፈረንደሙ ሂደት እና በህዝብ ቆጠራው ጥያቄዎች ላይ አሁንም በሰሜኑና በደቡቡ መካከል ትልቅ ልዩነት ተፈጥሮ ሁለቱን ወገኖች እንዳከራከረ ይገኛል።
« እንደጠቀስሽው ደቡቡ የህዝብ ቆጠራውን ሂደት ትክክለኛነት እያጠያየቀ ነው። ይህ ጥያቄ፡ በብሄራዊው ኮንግረስ ፓርቲ እና በሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ እንቅስቃሴ መካከል በተለይ በብሄራዊው አጠቃላይ ምርጫ ዝግጅት ሂደት ላይ ስምምነት እንዳይኖር ምክንያት ሆኖዋል። በውነቱ ይህ ጉዳይ እንዴት መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚችል ገና አላወቅንም። አሁን ባለን መረጃ መሰረት የህዝብ ቆጠራው ውጤት በትክክለኛ ዘዴ ተካሂደዋል በሚል የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እውቅና አግኝቶዋል። ግን፡ እንደምታውቁት፡ በወቅቱ የወጣው የህዝብ ቆጠራ ውጤት በቀጣዩ ምርጫ ላይ ሰሜኑን የሚጠቅም ሆኖ ነው የታየው።»
በገዚው ብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲ አስተሳሰብ ደቡብ ሱዳን ነጻ መንግስት መመስረት የሚችለው በሬፈረንደሙ ሰባ አምስት ከመቶ የመራጩን ድምጽ ካገኘ ነው። ይሁንና፡፡የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ነጻ መንግስት ለመመስረት የአብዝኃኑ መራጭ ድምጽ በቂ ነው ባይ ናቸው።
ግጭቱን ለማብረድና በተቀናቃኙ ወገኖች መካከል ዕርቀ ሰላም ለማውረድ የሚቻልበትን ድርድር ለማካሄድ ለፊታችን ረቡኵ ተይዞ የነበረው ቀጠሮ በሁኔታው መክፋት ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፎዋል።
AA/MM

Salva Kiir als Vizepräsident Sudans vereidigt Omar al-Bashir
የደቡብ ሱዳን መስተዳድር መሪ ሳልቫ ኪር ከሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን ኧል በሺር ጋርምስል picture-alliance/dpa/dpaweb