1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃውሞ በጎንደር

Eshete Bekeleሰኞ፣ ሐምሌ 25 2008

የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የወልቃይትን የድንበር አከላለል በመቃወም የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ የወልቃይትጠገዴን የማንነት እና የድንበር ጥያቄ ለመንግስት ለማቅረብ የተቋቋመው ኮሚቴ አባላት ከእስር እንዲፈቱ የሚጠይቁ መፈክሮችን ማሰማታቸውን የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/1JZN4
Fasil Schloss Gonder Äthiopien
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn

የከተማው ነዋሪዎች «በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች» በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ተሳትፈዋል ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በሰላማዊ መንገድ መከናወኑንም የአይን እማኞች አክለው ገልጸዋል። «ወልቃይት የአማራ ነው። ኮሎኔል ደመቀ ይፈቱ፤የትግራይ ህዝብ የእኛ ጠላት አይደለም። ጠላታችን ወያኔ ነው።» የሚሉ መፈክሮች መመልከታቸውን የተናገሩት የሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊ በተቃውሞው የአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ መወቀሱንም ተናግረዋል። የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ ማለዳ ሲጀመር የጸጥታ አስከባሪዎች ክልከላ ለማድረግ መሞከራቸውንም ጨምረው ገልጠዋል።

«የሰላማዊ ሰልፉን ተሳታፊዎች ብዛት መገመት አልችልም» ያሉ ሌላ የአይን እማኝ ማለዳ የተጀመረው ሰልፉ ያለ ምንም እንከን መከናወኑን ተናግረዋል። የተቃውሞው ዋና መነሻ የወልቃይት ጉዳይ መሆኑን የተናገሩ ሌላ የሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊ የዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር እጦት ጥያቄዎችም መነሳታቸውን ገልጠዋል። «በኦሮሚያ ያሉ ወንድሞቻችን ደም እኛንም ያስቆጨናል።» የሚለው በጎንደር ከተማ የዕለተ እሁድ ተቃውሞ ከተሰሙ መፈክሮች መካከል እንደሚገኝበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በተቃውሞ ሰልፉ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም። ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያለው ራዲዮ ፋና ዓርብ የተቃውሞ ሰልፉ «ከክልሉ መንግስት እና ከከተማ አስተዳደሩ ህጋዊ እውቅና ያልተሰጠው»ነበር ሲል ዘግቧል። «ከትናንት ጀምሮ ሰላማዊ ሰልፉ እንዳይካሄድ እጅግ በጣም ብዙ ወታደሮች ነበሩ።» ያሉት ተሳታፊ ወታደሮቹ ከአካቢው መልቀቃቸውን እና በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የጎንደር የተቃውሞ ሰልፍ እና በጎንደር ከተማ የተደመጡ መፈክሮች በማህበራዊ ድረ-ገጾች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ስበዋል። የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች በጎንደሩ ተቃውሞ የተደመጡ የአጋርነት መልዕክቶችን አወድሰዋል።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ