1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመንግሥት ኃላፊነት

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ መስከረም 14 2011

የፌደራል ይሁን የክልል፤ የወረዳ ይባል የቀበሌ ባለሥልጣን ወይም  የፀጥታ አስከባሪ የሕዝብን ሠላም እና ደሕንነት ማስጠበቅ እንጂ ሕዝብ ከተገደለ፤ከተሰደደ በኋላ «ለቅሶ ደራሽ»፤ አስከሬን ቆጣሪ ፖለቲከኛ አያስፈልገዉም።

https://p.dw.com/p/35Q3d
Äthiopien Proteste in Addis Abeba
ምስል picture-alliance/AA/M.W. Hailu

ለጎሳ ዛር ገበር፤ ሕይወት፤ ደም፤ አካል፤ ሐብት ንብረት

ኢትዮጵያ የሠላም፤የዴሞክራሲ፤የፍትሕ ነፃነት ጅምር ተስፋዋ ባይጠፋ በጎሳ ግጭት፤ግድያ፤ ደብዝዟል።የኢትዮጵያዊዉ አንድነት፤የመቻቻል፤መደጋገፍ ነባር ወግ ጨርሶ ባይሰበር ግራ ቀኝ እየታላጋ ነዉ። የአዲስ መሪዋ የመፈቃቀር፤የይቅርታ፤ መደመር መርሕ ባይቀጭ እየተዉገረገረ ነዉ።ባለፉት ሰባት-ስምንት ወራት ሶማሌ፤ሐረርጌ፤ ቦረና፤ ኮንሶ፤ አሶሳ፤ አዋሳ፤ ወልቂጤ፤ ጌዲዮ፤ወይም ጉጂ ላይ ኢትዮጵያዉን ጎሳ ለይተዉ ሲተላለቁ ለአዲስ አበቦች «የሩቅ ሐገር» ጥፋት፤ ወይም ያለፍ አገደም አጋጣሚ መስሎ ነበር።አዲሱ ዓመት ካዲስ ተስፋ ጋር በበረቀ ማግሥት ግን አዲሱ ተስፋ ባዲስ ደም ይበከል ገባ።አዲስ አበባ፤ ቡራዩ፤አሸዋ ሜዳ፤ከታ የነዋሪዎቻቸዉን ሕይወት፤ደም፤አካል፤ ሐብት ንብረት ለጎሳ ዛር ገበሩ።

የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ባለፈዉ ሳምንት እንዳስታወቀዉ አዲስ አበባ ዉስጥ በተደረገ ሰልፍ መሐል የፀጥታ አስከባሪዎችን የተተናኮሉ አምስት ሰዎች በፖሊስ ተገድለዋል።የአዲስ አበባ ፖሊስ ግን በሚጠብቃት ከተማ የሆነ እና ያደረገዉን ለሕዝብ ለማሳወቅ ከአንድ ሳምንት በላይ ፈጀበት።ዛሬ አረዳን።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲ።አዲስ አበባ አካባቢ በተለይ ቡራዩ፤አሸዋ ሜዳ፤ከታ እና በአካባቢያቸዉ ነዋሪዎች ላይ በጅምላ የዘመተዉ ወጣት በትንሽ ግምት 58 ሰዉ መግደሉን ባለፈዉ ሳምንት ሰምተናል።አስራ አምስት ሺሕ የሚሆን ሕዝብ ተፈናቅሏል።

አዲስ አበባ፤ ቡራዩ ይሁን ከዚያ በፊት በየስፍራዉ የተከሰተዉ ጎሳ ጎሳን ለይቶ የመግደል፤ ማሰደድ የመዝረፍ አባዜ የሕግ ባለሙያ እና ደራሲ ሙሉጌታ አረጋዊ እንደሚሉት 27 ዘመን ሲሰበክ የኖረዉ  የዘር አስተሳሰብ እና ስሜት ዉጤት ነዉ።

የሕግ መምሕር ሙሉ ጌታ አረጋዊ፤ የጎሳ ልዩነት እፍቅረኞች መሐል ድረስ ዘልቆ  ፍቅርን ወይም ትዳርን ማመሰቃቀሉን የሚተርክ ልቦለድ መፅሐፍ በቅርቡ አሳትመዋል።አቶ ሙሉ ጌታ እንደሚያምኑት አሁን በየስፍራዉ በጎሰኝነት አስተሳሰብ እየተገፉ የሌላ ጎሳ አባልን የሚገድሉ፤ ወይም ለአስገዳዮች መሳሪያ የሚሆኑት አብዛኞቹ በዘመነ-ኢሕአዴግ የተወለዱ እና ያደጉ ወጣቶች ናቸዉ።

አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ታፍኖ ጎሳኝነት፤ ክልላዊነት ወይም ብሔረሰባዊነት መንገሱ የሕዝብን አድነት ሸርሽሮ የገዢዎቹን እድሜ ማራዘም እስከቻለበት ጊዜ ድረስ ለማራዘም ጠቅሟቸዋል።የገዢዉ ፓርቲ መሪዎች በሕዝብ ግፊት ተቀያይረዉ አዲሶቹ መሪዎች ባጭር ጊዜ መመለስ የነበረበትን የሕዝብ ጥያቄ መመለሳቸዉ አላነጋገረም።

የእስረኞች መለቀቅ፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የመሳሰሉ አፋኝ ደንቦች መሻር፤ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ነፃነት ማግኘታቸዉ፤ ከኤርትራ ጋር ሠላም መስፈኑ፤ አማፂያን እና ስደተኛ ፖለቲከኞች ለሰላማዊ ትግል ወደ ሐገር መመለሳቸዉ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ መንግሥት ከወሰዳቸዉ እርምጃዎች ጥቂቶቹ ናቸዉ።

Äthiopien Addis Abeba, Unruhen
ምስል DW/B. ze Hailu

እርምጃዎቹ የአብዛኛዉን ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ማግኘታቸዉ አያጠያይቅም። ከገዢዉ ፓርቲ እስከ ቀድሞ አማፂያን መሪዎች፤ ከፖለቲካ አቀንቃኞ እስከ ደጋፊዎች፤ ከፀጥታ አስከባሪዎች እስከ መንግስት ሠራተኞች ያሉት የአብዛኞቹ አመለካከት ባሮጌዉ የዘር አስተሳሰብ የተቃኘ መሆኑ እንጂ ክፋቱ።

ክፉዉ አስተሳሰብ አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት ብልጭ ያለዉን የተስፋ ጮራ ከማደብዘዝ፤ ከግጭትም አልፎ የየሰዉን የዕለት ከዕለት ኑሮ ያዉከዉ ገባ።                                           

የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መንግስት ባጭር ጊዜ ሊመለሱ የሚችሉ የህዝብ ጥያቄዎችን መመለሱን፤ የይቅርታ እና የመደመር አስተሳሰብን ለማሥረፅ መጣሩን፤ ከሁሉም በላይ ዴሞክራሲ፤ፍትሕ እና እኩልነትን ለማስፈን ቃል መግባቱን ያልደገፈ፤ያላደነቀ፤ ወይም ያልተቀበለ ኢትዮጵያዊ ካለ እሱ በርግጥ በለዉጡ ጥቅም ያጣ ነዉ።ይሁንና መንግሥት የሕዝብ ድጋፍ ሞልቶ የተረፈዉን ያክል የህዝብን ምርጫ፤ ሰላም እና ደሕንነትን ማስከበር ግን አንድም አልቻለም ወይም ዳተኛ ነዉ።የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት ቢያንስ የቡራዩ ሕዝብ አደጋ እንደሚጣልበት ሲዛትበት ለፀጥታ አስከባሪዎች የድረሱል ጥሪ አሰምቶ ነበር።የደረሰለት የለም።

አዲስ አበባ ዉስጥ  28 ሰዎችን ከመገደል ለማዳን ያልፈየደዉ ፖሊስ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲ ዛሬ እንዳሉት አሁን ወጣቶችን በጅምላ እያፈሰ በየጦር ሠፈሩ እያጎረ ነዉ።የሕግ ባለሙያ ሙሉ ጌታ አረጋዊ የፖሊስን እርምጃ ፍትሐዊነት ይጠይቃሉ።

የአዲስ መሪዎቹን ርዕይ እና እርምጃ በመደገፍ በየአደባባዩ የሚሰለፈዉ አንዳዴም የቦምብ ማብረጃ የሆነዉ ሕዝብ የጎሳ ዛር በሚያሰደልቃቸዉ እብሪተኞች በካራ መታረዱ፣ ብዙዎች እንዳሉት ዘግናኝ፤ አሳዛኝ፤ አሳሳቢ፤ አስጊም ነዉ።የፌደራል ይሁን የክልል፤ የወረዳ ይባል የቀበሌ ባለሥልጣን ወይም የፀጥታ አስከባሪ የሕዝብን ሠላም እና ደሕንነት ማስጠበቅ እንጂ ሕዝብ ከተገደለ፤ከተሰደደ በኋላ «ለቅሶ ደራሽ»፤ አስከሬን ቆጣሪ ፖለቲከኛ አያስፈልገዉም።

Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

አቶ ሙሉ ጌታ እንደሚሉት ደግሞ የትኛዉም መንግስት የመጀመሪያ ኃላፊነት የዜጎቹን ደሕንነት መጠበቅ ነዉ።

ሶማሌ፤ ምሥራቅ ሐረርጌ መቶዎች ሰዎች ሲገደሉ-የሶማሌ ክልል መሪዎች ተጠያቂ ሆነዉ ታሰሩ።ልዩ ፖሊስ ተወገዘ።ደቡብ ኢትዮጵያ ከአዋሳ እስከ ወልቂጤ ለሞተ-ለተፈናቀለዉ ተጠያቂ የተባሉ የየአካባቢዉ ባለሥልጣናት ከስልጣን መነሳታቸዉ ተግሯል።አሶሳም እንዲሁ።የጌዲዮ-ጉጂስ? የአዲስ አበባስ? ምናልባትም ከአሸዋ ሜዳ በተጫነ አሸዋ እና ድጋይ በተሰራ ቤት ተቀምጠዉ የእዚያዉ የአዲስ አበባ፤ የቡራዩ እና የአካቢዉን ግድያ፤ ዘረፋ እና ቃጠሎ ለማስቆም ያልፈለጉ፤ ቸል ያሉ ወይም ያልቻሉ ባለሥልጣናት ለፍትሕ እስኪቀርቡ ምን ያሕል ጊዜ ይፈጅ ሆን?

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ