1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ አንሽ - አሮን ስሜነህ

ዓርብ፣ መጋቢት 6 2011

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ስልጣን ከያዙ በኋላ ፅህፈት ቤታቸው እንደ ፌስቡክ ባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ይፋ ከሚያደርጋቸው ፎቶዎች በስተጀርባ አንድ ወጣት ባለሙያ ይገኛል። አሮን ስሜነህ ። ካለፉት አምስት ወራት አንስቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ አንሺ ነው።

https://p.dw.com/p/3F1uA
Aron Simeneh
ምስል Aron Simeneh

ወጣት አሮን ስሜነህ ላለፉት አምስት አመታት የፖርትሬት ፣ የዘገባ እና የንግድ ፎቶዎችን የሚያነሳ የፎቶግራፍ ባለሙያ ነው። ከጥቂት ወራት አንስቶ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፎቶ አንሺ ሆኗል። አሮን የአንድ ሀገር መሪ ፎቶ አንሽ እሆናለሁ ብሎ የጠበቀው አልነበረም። በመሆኑ ግን እጅግ ይኮራል።« እንደዚህ አይነት ፎቶዎች ልዩ ልምዶችን የሚጠይቅ ነው። ለኔ ትልቅ እድል ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከሚያደርጉት ስራ አንፃር ትልቅ ታሪካዊ እድል ነው። የዚህ አንድ አካል መሆን ለኔ ትልቅ ነገር ነው።»
አሮን ካለፉት አምስት ወራት አንስቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ቢሮ ሙሉ ሰዓት ይሰራል። ወጣቱ፤  አሮን ስሜ በሚለው የግሉ የኢንስታግራም ገፁ ስር ከጥቂት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶዎች ሌላ የተለያዩ የፎቶ ስራዎቹ ይታያሉ። ከነዚህም መካከል የበርካታ አርቲስቶች ፎቶ ይታያሉ። « ሙዚቃ በጣም እወዳለሁ። ወደ ፎቶአንሽነት የገባሁበትም ምክንያት ሙዚቃ ነበር። ለረጅም ጊዜ ላይፍ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን በመዘገብ ሰርቻለሁ።»  


ዛሬ ላይ አብዛኛው ሰው ባለ ካሜራ ነው። ቢያንስ ስልኩ ላይ ካሜራ አይጠፋም። ፎቶ ያነሳል። ያነሳውንም ፎቶ ፤ ፎቶ ቤት ወስዶ አሳጥቦ ሳይሆን ወድያው የመመልከት እድል አለው። ነገር ግን አንድን ሰው እንደ አሮን የፎቶ ባለሙያ የሚያስብለው ምን ምን ነገሮችን ማሟላት ሲችል ነው?« እቃው ብቻ አይደለም ፎቶውን ፎቶ የሚያደርገው። ማስተላለፍ የምንፈልገውን መልዕክት በምስል ማቅረብ ስንችል ነው።» ይላል አሮን። 
አሮን ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ በረራ የተጀመረ ጊዜ የመጀመሪያውን በረራ ከወሰዱ ሰዎች አንዱ ነው። « ከኤርትራ ጋር በቤተሰብም ይሁን በሌላ አጋጣሚ ምንም ግንኙነት የለኝም። ግን የዚህ የሰላም ግንኙነት ደስተኛ ከሆንኩባቸው እና በፊት ከማዝንባቸው ነገሮች አንዱ ነበር። ታድያ እድሉ ሲመጣ በግሌ ብዘግበው ትልቅ ታሪክ ነው ብዬ ስላመንኩኝ ለዛ ነበር የሄድኩት። ነገር ግን በጣም ከጠበኩት በላይ ሆኖ ነው ያገኘሁት።»

Italien Abiy Ahmed, Premierminister Äthiiopien & Giuseppe Conte in Rom
አሮን የተለያዩ የሀገር መሪዎች እና ባለስልጣናት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር ሲገናኙ አንስቷልምስል Office of the Prime Minister of Ethiopia


ሌላው አሮን ተፈጥሮ ላይ ያተኩራል። ኢትዮጵያን፣ ህዝቧን፣ አኗኗራቸውን ለማሳየት ይሞክራል። « በተቻለኝ መጠን የተለመዱ እና የታዩ ነገሮችን ላለማሳየት ነው የምጥረው። ከሰዎች ጋር የማደርጋቸውን ግንኙነቶች ነው በፎቶዎች ማሳየት የምሞክረው።» የ 23 ዓመቱ አሮን የፎቶ ስራዎቹን ሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ እንደ ማሊ፣ ደቡብ አፍሪቃ ፣ ዮናይትድ ስቴትስ በመሳሰሉ ሀገሮች ዓውደ ርዕይ ላይ የማሳየት እድሉንም አግኝቷል።

Deutschland Bundespräsident Steinmeier zu Staatsbesuch in Äthiopien
የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታየንማየር ኢትዮጵያን በጎነኙበት ወቅት ምስል Office of the Prime Minister Ethiopia 


አሮን ፎቶ ሊያነሳ ሲሄድ ቀድሞ ይዘጋጃል ወይስ ቦታው ሲደርስ ነው የሚወስነው?«  እንደ ፕሮጀክቱ ይለያያል። የግል ፕሮጀክት ሲሆን በብዛት ቀደም ብዬ እዘጋጃለሁ። አንዳንዴ ደግሞ የጉዞ ተሞክሮ ሲሆን ዝግጅትን ሳይሆን እይታን ነው የሚጠይቀው። » ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሲጓዝስ?
« በጣም ፈታኝ ነው። ቀድሞ ለመዘጋጀት በተለያዩ ምክንያቶች እድል የማይገኝበት አጋጣሚዎች አሉ።  ዋናው ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሆኑም የሚካሄደውን ፣ አካባቢው ላይ ያሉትንም ነገሮች በፎቶ መዘገብ እና ሙሉ ታሪኩን መግለፅ መቻል ያስፈልጋል። ይህ ነው በዚህ ስራ ላይ ፈታኝ የሚያደርገው።»


እንደ አሮንም ባይሆን በርካታ ወጣቶች ለግላቸው ፎቶዎች ያነሳሉ። እነዚህንም ፎቶዎች ለሌሎች እንደ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ባሉ ገፆች ለሌሎች ያካፍላሉ። አሮን የፎቶ ማንሳት ፍቅር ያላቸው ሰዎች ሊበረታቱ ይገባል ይላል። « ሀገራችን ላይ ብዙ ያልተነሱ እና ያልተነገሩ ነገሮች አሉ። ነገር ግን ፎቶግራፊ ትልቅ ልምምድ፣ ትምህርት እና ጊዜ መስጠትን የሚፈልግ ነገር ነው። በየቀኑ ፎቶ ማንሳትን፣ እይታን ማዳበር ይጠይቃል። »ይላል። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፎቶ አንሽ አሮን ስሜነህ።

የበለጠ የአሮንን ፎቶዎች ለማየት ይኸን ይጫኑ  ።


ልደት አበበ 
እሸቴ በቀለ