1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠ/ሚንስትሩ ንግግር፤ ጃዋር እና የቀድሞው ጠ/ሚ

ዓርብ፣ ጥቅምት 14 2012

የጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የምክር ቤት ንግግር፤ የጃዋር የፌስቡክ መልእክቶች እና በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው አመጽ እንዲሁም የቀድሞው ጠቅላይ ሚንሥትር ከዶይቸ ቬለ ጋር ያደረጉት ቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች ትኩረታችን ናቸው።

https://p.dw.com/p/3RtN1
ምስል picture-alliance/dpa/Bildfunk/Kremlin

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ በምክር ቤት ባሰሙት ንግግር የውጭ ሀገር ፓስፖርት ይዘው በሀገሪቱ ሰላም የሚነሱ ያሏቸውን ግለሰቦች ማስጠንቀቃቸው እና ከዚያም ተከትሎ የመጣው የበርካቶች መነጋገሪያ ነበር። ንግግራቸው በተሰማበት እኩለ ሌሊት ላይ ደግሞ የኦሮሞ አክቲቪስት እና የኦሮሞ ሚድያ ኔትወርክ ሥራ አስኪያጅ ጃዋር መሐመድ ደኅንነቱን በተመለከተ የድምጽ እና የጽሑፍ መልእክቶችን አሰራጭቷል። በነጋታው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች  ተቃውሞ፣ ግጭት እና ግድያ ተከስቷል። የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች አንዱን ድርጊት ከሌላው ጋር እያሰናሰሉ አስተያየት፣ ድጋፍ እና ትችቶችን አንጸባርቀዋል። የኢትዮጵያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከዶይቼ ቬለ (DW) ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስም ሌላው መነጋገሪያ ነበር። 

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባሰሙት ንግግር፦ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም የሚነሱ የመገናኛ አውታር ባለቤቶችን በተለይ የውጭ ሀገር ፓስፖርት የያዙትን አስጠንቅቀዋል። በንግግራቸውም፦ «በማንኛውም ሰአት በኢትዮጵጵያ ሰላም እና ኅልውና ላይ ከመጣ አማርኛ ብትናገሩም ኦሮሚኛም ብትናገሩ ርምጃ መውሰዳችን የማይቀር መኾኑን በጥንቃቄ መገንዘብ አስፈላጊ ይኾናል» ብለዋል። 

ይኽ ንግግራቸውን በተመለከተ ሚካኤል ብርሃኑ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «የአንድ ሀገር መሪ ፓርላማ ውስጥ እንዲህ የዛቻ ንግግር መናገር ጠቃሚ አይደለም። ዲፕሎማሲ የሚሠራው በትእግስት እና ውስጥ ለውስጥ በካቢኔው አማካኝነት እንዲሆን ይመረጣል» ብሏል። ጠቅላይ ሚንሥትሩ በምክር ቤቱ ንግግራቸው አጽንዖት ሲሰጡ «በተለይ በተለይ» እያሉ ነበር።

«በተለይ በተለይ የውጭ ሀገር ዜጋ የኾናችሁ የሚዲያ ባለቤቶች የኢትዮጵያ ፓስፖርት የሌላችሁ የሚዲያ ባለቤቶች ስትፈልጉ እና ሰላም ሲኾን እዚህ ተጫውታችሁ እና ችግር ውስጥ ስንገባ ጥላችሁ የምትሄዱበት ሀገር ያላችሁ ሰዎች ትዕግስት እያደረግን ያለነው አውዱን ለማስፋት ነው» ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር፦ «የብሮድካስት ባለሥልጣን የነበረውን የተቀየደ ሚዲያ ነፃ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ሳያደናቅፍ ሕግ የማስከበር ሥራ ግን መሥራት አለበት» ብለዋል። 

Russland | Erster Afrika-Russland-Gipfel
ምስል picture-alliance/dpa/AP Photo/Sputnik/Pool/Tass/A. Druzhinin

ይኽ ንግግራቸው በተሰማበት ዕለትም ጠቅላይ ሚንስትሩ፦ «የሩሲያ አፍሪቃ ጉባኤ» ላይ ለመሳተፍ ወደ ሶቺ ከተማ አቅንተዋል። ሌሊት ላይ ደግሞ የኦሮሞ አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ «የፓርላማው ማስጠንቀቂያ ቤቴ ድረስ መጥቷል» ሲል ፌስቡክ ገጹ ላይ በኦሮሚኛ ጽፏል። ከመኖሪያ ቤቱ ኾኖም የሥልክ ንግግር ቅጂን እና ደኅንነቱን የሚመለከቱ የጽሑፍ መልእክቶችን አሰራጭቷል።  እነዚህ መልእክቶች በውድቅት ለሊት በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በፍጥነት እና በስፋት ነበር የተሠራጩት።

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ በምክር ቤቱ ያሰሙት ማስጠንቀቂያ የሚከተለው ነበር። «በማንኛውም ሰአት በኢትዮጵያ ሰላም እና ኅልውና ላይ ከመጣ አማርኛ ብትናገሩም፤ ኦሮሚኛ ብትናገሩም ርምጃ መውሰዳችን የማይቀር መኾኑን በጥንቃቄ መገንዘብ አስፈላጊ ይኾናል። ሁለት ቤት መጫወት አይቻልም ማለት ነው። እኛ የምንሄድበት ሀገር የለንም፤ ሀገራችን ይኼ ስለኾነ ሠላም እንፈልጋለን። ስኮርት ያላችሁ ሰዎች በነፃነት ልማታችን፣ ሠላማችን፣ ዲሞክራሲ ካገዛችሁ እሰየው በደስታ። ከዚያ ውጪ ግን ለመነገጂያ የምትጠቀሙበት ከኾነ በዚህ ኹኔታ በነፃነት እና በዲሞክራሲ ስም የሚቀለድ ነገር እንዳልኾነ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል እንደዚህ አይነት ችግሮች አሉ።»

የምክር ቤቱ ንግግር በተሰማ በነጋታው ረቡዕ ዕለት የጀዋር መሐመድ መኖሪያ ቤትም ጽሑፎቹን ካሰራጨበት ሌሊት አንስቶ እስከ በነጋታው እኩለ ቀነ በኋላ ድረስ በወጣት ደጋፊዎቹ ተከቦ ውሎዋል። ጠዋት በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ እንዲሁም በኦሮሚያ የተለያዩ ስፍራዎች የሰው ሕይወትን የቀጠፉ ተቃውሞዎች እና ብጥብጦች ተስተውለዋል። ጃዋር በመኖሪያ አካባቢው «በቁጥር በርካታ ታጣቂ እየተሰማራ እንደኾነ» ማስተዋሉን በመጥቀስ «ወደኋላ እንዲመለስ በአጽንኦት» ጠይቋል። 

Repräsentantenhaus in Äthiopien
ምስል DW/Y. Gebreegiziabher

«የሄድነው ሴኩሪቲ ለመቀየር ነው እያሉ ነው አይደል? የተላኩ ፖሊሶች ለዚህ ጋዜጠኛ የተናገሩትን እዩ» ሲልም ወደ አራት ሺህ ግድም ሰዎች የተቀባበሉትን የፌስቡክ መልእክት በኦሮሚኛ አስፍሯል። ከፌስቡክ መልእክቱ ጋርም በእንግሊዝኛ የተጻፈ የጋዜጠኛ ሣሙኤል ጌታቸው የትዊተር መልእክትን አያይዟል። አንድ የፖሊስ አባል እንደነገሩት የጠቀሰው ሣሙኤል ፖሊሱ ጃዋርን በቁጥጥር ስር ለማዋል እና ለፍርድ ለማቅረብ መምጣታቸውን እንደነገሩት ጽፏል። አብርሃም ኤቢ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «እዚህ ያለነው ልናስረው ነው? » ሲል ለሣሙኤል ጥያቄ በማቅረብ፦ «በትዊተርህ የጠቀስከው የፖሊስ ባልደረባ ማን እንደኾነ ትገልጥልን? »  ሲል አክሎ ጠይቋል።

የፌዴራል ፖሊስ ለመንገድ መዘጋት ሰበቡ «አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ለተከታዮቹ እና ለደጋፊዎቻቸው ያስተላለፉት መልእክት ስለነበረ ነው» ብሏል በመግለጫው። መግለጫውን የሰጡት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጀነራል እንደሻው ጣሰው የተናገሩት የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ይገኛል። «በፖሊስ ርምጃ ተወሰደብን ብለው ያስተላለፉት መልእክት ስህተት ነው። በየትኛውም ፖሊስ የተወሰደ ርምጃ የለም። በየትኛውም የመንግሥት አካል የተወሰደ ርምጃ የለም። ይኼ ኅብረተሰቡ በአግባቡ እንዲያውቀው ስለፈለግን መልእክቱን በአግባቡ ለማስተላለፍ ነው ዛሬ ይኼን መድረክ የጠራነው።» 

ፖሊስ ከውጭ ሀገር ለተመለሱ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች «የጥበቃ ከለላ ሲያደርግ» መቆየቱንም ገልጠዋል። እናት እናትዬ የተባለች የፌስቡክ ተጠቃሚ፦«ጃዋር ምን ስለሆነ ነው በሕዝብ ገንዘብ ጠባቂ የተቀጠረለት? » የሚል ጥያቄ አስፍራለች። 

Hailemariam Desalegn, ehemaliger äthiopischer Ministerpräsident
ምስል DW

የቀድሞ ብቸኛው የምክር ቤት አባል ግርማ ሠይፉ፦«ለማንኛውም ትናንት በፓርላማ በተሰጠ ማሰጠንቀቂያ፣ የውጭ ፓሰፖርት ባለቤት ጃዋር ቅር ብሎታል፣ ለጠብ እንዲመቸው ጥበቃ ተነሳብኝ ብሎ ፖስት አድርጓል። እንዳሰበውም እዚህም እዚያም ጠብ ተጀምሯል፣ እርሱም አሁን በደንብ አየተጠበቀ ነው። ቤቱም ተከቧል። ግድ የለም ሊነጋ ነው መሰለኝ ደንገዝገዝ ማለቱ ታወቆኛል» ሲሉ ፌስቡክ ላይ ጽፈዋል።  «የሚያኮራ ደጋፊ አለህ መታደል ነው» ያለው ደግሞ አሚሎን ፈርስት የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ነው።

በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የአንድ ትንሽ ልጅ ፎቶግራፍ በስፋት ተሰራጭቷል። ቁንጣ ያደረገው፤ የትምህርት ቤት ቦርሳ ያነገበው ይኽ ህጻን ልጅ በአውራ ጎዳና እዚህም እዚያም በተጣሉ ድንጋዮች መሀከል ፊቱ እንደተከፋ አንገቱን ዘንበል አድርጎ ሲጓዝ ይታያል። በርካቶች የዚህን ህጻን ልጅ ፎቶግራፍ አያይዘው ስለ ሀገሪቱ የፀጥታ ኹኔታ ብዙ ጽፈዋል። ታሪኩ ሐብታሙ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «ብሩህ ተስፋ አይቼ ማልጄ ስነሳ፤ የነጋልኝ ሌሊት ወርሶታል አበሳ» ሲል የህጻኑ ልጅ ፎቶግራፍ ላይ ጽፏል። 

ሌላው በሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች መነጋገሪያ ከነበሩት ጉዳዮች የኢትዮጵያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በእንግሊዝኛው «ኮንፍሊክት ዞን» ከተባለው የዶይቼ ቬለ (DW) ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ነበር። 26 ደቂቃ በፈጀው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ቃለ መጠይቅ በሥልጣን ዘመናቸው ለደረሰው በደል ምን እንደሚሰማቸው፤ አምባገነን እንደነበሩ፤ ይቅርታ ይጠይቁ እንደሆነም ጋዜጠኛው ይጠይቃል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚንሥትር በዘመናቸው የተሠራው በደል ከዕውቅናቸው ውጪ እንደኾነ፤ የጸጥታ ኃይሉ መረጃ እንዳልሰጣቸው፤ የነበረው አስተዳደርም ብዙ እንዳላሠራቸው፤ እሳቸውን አምባገነን ብሎ መጥቀስ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጥ ይሞግታሉ። በቃለ መጠይቁ፦ «ባለፈው አንድ ዓመት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር በእኔ 6 ዓመት የስልጣን ጊዜ ከነበረው ይልቃል» ሲሉም ተደምጠዋል። 

DW Conflict Zone (Podcastcover)

በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ትችት እና ነቀፌታን ሰንዝረዋል። በዛው መጠን ድጋፋቸውንም የገለጡ አሉ። ዜድ የተዋሕዶ ልጅ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው ጽሑፍ፦ «ሊደነቁ የሚገቡ ትሁት መሪ ናቸው 'ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባበታል' እንዲሉ በጀመሩት መንገድ የገባው ዶ/ር አብይ ስሙን ቀምቷቸዋል እሳቸው በአስፈሪው ፓርቲ ውስጥ በጣም ተጨቁነው እና ታፍነው የነበሩ ምርጥ መሪያችን ነበሩ» ይላል። ግርማ ሹሚ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦«እባክዎትን አይዋሹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንሥትር። ሁሉንም ነገር ያውቁ ነበር፤ ለመቆጣጠርም በራስ መተማመን እና ድፍረቱ ስላልነበረዎት እንጂ» በማለት በእንግሊዝኛ ጽፏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተስፋለም ወልደየስ