1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠ/ሚ ዐብይ የአንድ ዓመት ሥልጣን

ማክሰኞ፣ መጋቢት 24 2011

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ የማነ ዘርዓይ ዶክተር ዐቢይ ከቀድሞዎቹ የኢህአዴግ መሪዎች በተለየ በድፍረት የወሰዷቸው እርምጃዎች ለታላላቅ ስኬቶች እንዳበቋቸው ገልጸዋል።በርካታ ተስፋ ሰጭ ለውጦች መምጣታቸውን የተናገሩት ዶክተር ሰሚር ዩሱፍ ደግሞ በአቋራጭ ለመጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች የሚወስዷቸው እርምጃዎች ከለውጡ ተግዳሮቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3G7Ha
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Office Of The Prime Minister

የጠ/ሚ ዐብይ የአንድ ዓመት ሥልጣን

 የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአንድ ዓመት የሥልጣን ዘመን ከዚህ ቀደም ይሆናሉ ተብለው ያልታሰቡ ብዙ ስኬቶች የተገኙበት የዚያኑ ያክል ደግሞ ችግሮችና ተግዳሮችም የታዩበት እንደነበር የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ተናገሩ። DW ዶቼቬለ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ዐቢይ ከቀድሞዎቹ የኢህአዴግ መሪዎች በተለየ በድፍረት የወሰዷቸው እርምጃዎች ለታላላቅ ስኬቶች እንዳበቋቸው ገልጸዋል። በርካታ ተስፋ ሰጭ ለውጦች መምጣታቸውን የተናገሩት ሌላው ምሁር  ደግሞ በአቋራጭ ለመጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች የሚወስዷቸው እርምጃዎች ከለውጡ ተግዳሮቶች ውስጥ የሚጠቀስ መሆኑን አስረድተዋል። 
ልክ የዛሬ ዓመት መጋቢት 24 ፣2010 ዓም በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለ መሀላ ፈጽመው ሥልጣኑን የተረከቡት ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባለፈው አንድ ዓመት በወሰዷቸው ያልተጠበቁ እርምጃዎች ታላላቅ የሚባሉ ስኬቶች ማስመዝገብ ችለዋል እንደ አስተያየት ሰጭዎቹ። ዶክተር ሰሚር ዩሱፍ በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ጥናት እና ምርምር በሚያካሂደው በእንግሊዘኛ ምህጻሩ ISS በተባለው ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ የተገኙ ዋና ዋና ሊባሉ የሚችሉ ለውጦችን ጠቅለል አድርገው ገልጸዋቸዋል።  
«የፖለቲካ ምህዳሩ እጅግ አካታች እየሆነ ይገናል የሚዲያ ነጻነት እየተስፋፋ ይገኛል።የፍትህ ተቋማት ተጨባጭ ለውጦችን እያሳዩ ይገኛሉ።በርካታ ዓለም አቀፋዊም ይሁን ቀጣናዊ ለውጦች እየታዩ ነውጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ።»
DW ዶቼቬለ ያነጋገራቸው ሌላው ምሁር ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ዘርዓይ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የለውጡ ስኬቶች ከሚባሉት መካከል ለሁለቱ የተለየ ቦታ ይሰጣሉ።

Äthiopien  - Ministerpräsident Äthiopiens in einer Gesprächsrunde
ምስል Daniel Getachew

«በውጭ የነበሩ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በድፍረት ከፍቶ አምጥቶ እንዲሳተፉ ለማድረግ የተደረገው ሙከራ አንዱ እርሱ ነው። ሁለተኛው በኤርትራ የነበረውን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብም አስጨናቂ ሆኖ የነበረውን ነገር የፈቱበት መንገድ ደግሞ ስኬት ናቸው ብዬ እወስዳለሁ።»   
ሁለቱ ምሁራን እንዳሉት የአንድ ዓመቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉዞ በስኬት ብቻ የተሞላ አልነበረም። ብዙ ተግዳሮቶችም ነበሩት። ግጭቶች፣ የሰዎች ሞት መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት እነዚህ ያስከተሏቸው የደህንነት ስጋቶች እና አረመረጋጋቶች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። ዶክተር ሰሚር ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለተከሰቱ አለመረጋጋቶች መንስኤ ያሏቸውን ምክንያቶች ዘርዝረዋል።

«መንግሥት መራሽ ለውጥ ነው ይሄ በራሱ አንድ ተግዳሮት ነው። ምክንያቱም ለውጥ በመንግሥት መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሲሆን የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያመጣ ይችላል ብዬ አስባለሁ።በአሁኑ ሰዓት ያለው መንግሥት ወጥነት በተወሰነ መንገድ የሚያንሰው ደከም ያለ መስሉ የሚታይ መንግሥት ይመስላል።ይሄ ደግሞ ለተለያዩ ያለመረጋጋት ሁኔታዎች እንዲከሰቱ መንስኤ ወይም ሰበብ ሆኗል ብለን መውሰድ እንችላለን በተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ራሳቸውን ተቃዋሚ አድርገው በሚቆጥሩ ቡድኖች መካከል ያለው ሽኩቻ ንትርክ ሰጣ ገባ ትልቁ የሩቁን ጊዜ ፖለቲካዊ ሽግግር ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚባለውን ዓላማ ከማሳካት ይልቅ አቋራጭ መንገዶችን በመጠቀም የቡድን እና የግል ፍላጎቶችን ለማሳካት የሚደረገው ጥረት ትልቁን የሩቁን ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚባለውን ግብ ሊያደናቅፈው የሚችል ዓይነት አዝማሚያ የምናይበት አጋጣሚዎች እናስተውላለን።»

Äthiopien President Somalia Mohammed Abdulahi, Eritreas Präsident Isayas Afeworki, Äthiopiens Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

ዶክተር ዐቢይ ሥልጣን እንደያዙ የወሰዷቸው ያልተጠበቁ እርምጃዎች በርካታ ደጋፊዎች አስገኝቶላቸዋል። ይሁን እና እንደ አቶ የማነ ይህ እንደ መጀመሪያው ሊቀጥል አልቻለም። ህዝቡ ስኬቶቹን አጣጥሞ ሳይጨርስ ከየአቅጣጫው ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት ልዩ ልዩ ችግሮች ጥርጣሪ ውስጥ እንዲገባ  አድርጎታል።

«የለውጥ ፕሮግራሙ ምንድን ነው የሚመስለው የሚለውን አለማስኬድ እና ተቋማዊ በሆነ በህግ መልኩ ለማስኬድ የተደረገው ጥረት አነስተና መሆኑ መተማመን እና ጥርጣሪ ውስጥ እንዲገባ አንዳንዱም በዚህ ምክንያት ወደ ኋላ እንዲሄድ አድርጓል የሚል ነው።»

አስቀድሞ በተያዘው እቅድ መሠረት ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ ታኪሂዳለች ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ዓመት ሊካሄድ የነበረው የህዝብ እና የቤቶች ቆጠራ ተሰርዟል። ምርጫውም ይዘግይ የሚሉ ወገኖች አሉ። አብዛኛዎቹ ከሚሰጡት ምክንያት አንዱ ሰላምና ጸጥታ አልሠፈነም የሚል ነው። ዶክተር ሰሚር ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ ማካሄድ ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ። ሆኖም ከዚያ በፊት ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራት አሉ ይላሉ።

Deutschland Besuch Abiy Ahmed äthiopischer Premierminister
ምስል DW/T. W. Erago

«በተለይ ኢትዮጵያን የመሰሉ የብሄር ቀውስ ያለባቸው ሀገሮች የምርጫ ፖለቲካ አንዳንድ ጊዜ ወደ ባሰ ቀውስ እና ግጭት የሚያመራባቸው ሁኔታዎች አሉ።ስለዚህ ምርጫ ማከናውወን በራሱ ግብ ተደርጎ መወሰድ ያለበት አይመስለኝም።እዛ ከመድረስ በፊት መሟላት ካለባቸው ሥራዎች አንደኛው መንግሥትን አገረ መንግሥትን ማጠናከር ነው።እነዚህ ነገሮች ባልተሟሉበት ወደ ምርጫ መግባት ምናልባት የሚቀጣጠል የሚፈነዳ ዓይነት የፖለቲካ ዐውድ ከተፈጠረ ሀገረ መንግሥቱ ያንን ነገር የማስቆም ብቃትም ወይ ደግሞ ፍላጎት ከሌለው አሁን ከምናየው የባሰ ቀውስ ውስጥ ልንገባ እንችላለን።» 
አቶ የማነ በበኩላቸው ምርጫው ይካሄዳል የሚል እምነት የላቸውም። ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን ያነሳሉ። 

«አንደኛ ምርጫውን ለማካሄድ የህዝብ ቆጠራ አስፈላጊ ነበር። ሁለተኛው በጣም ብዙ የኢትዮጵያ ክፍል ላይ የመንግሥት መዋቅሮች የክልል መዋቅሮች ላይ በጣም ብዙ ችግሮች አሉ። መንቀሳቀስም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ነው ያሉት። ስለዚህ ያስቸግራል የሚል እምነት ነው ያለኝ።  
ሁለቱ ምሁራን ሀገሪቱን ከባሰ ጥፋት ለመታደግ ለውጡን ተቋማዊ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። 

ኂሩት መለሰ 

ሸዋዬ ለገሠ