የጡት እና የማሕጸን ካንሰር

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
13:01 ደቂቃ
06.11.2018

ቅድመ ምርመራ ማድረጉ ጉዳቱን ይቀንሳል

ሴቶችን ከሚያጠቁ የካንሰር ዓይነቶች የጡት ካንሰር ግንባር ቀደም መሆኑ ይነገራል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በመላው ዓለም በየዓመቱ ሁለት ሚሊየን ገደማ ሴቶች በጡት ካንሰር ይጠቃሉ። ኢትዮጵያ ውስጥም ችግሩ ከፍ ብሎ እንደሚታይ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በመላው ዓለም ሴቶችን እየጎዳ የሚገኘው ካንሰር ሲሆን በአዳጊ ሃገራት ላይ በዚህ በሽታ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እጅግ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። ታማሚዎችም ርዳታ በመፈለግ ወደ ህክምና የሚሄዱት በሽታው ስር ሰድዶ ከበድ ያለ ደረጃ ላይ ሲደርስ መሆኑንም ያመለክታል። ይህንን በዘርፉ ህክምና ላይ የተሰማሩት ዶክተር ማቴዎስ አሰፋም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን በመጥቀስ ያጠናክራሉ።

«አዲስ አበባ ውስጥም ሆነው፣ ለጤና አገልግሎት ቅርበትም ኖሯቸው፣ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት፤ ደረጃው ከፍ ካለ በኋላ፣ ደረጃ ሦስት ወይም ደረጃ አራት ከሆነ በኋላ የሚመጡ ናቸው። ከ50 እስከ 60 በመቶ። ምናልባት ከ20 እስከ 25 በመቶዉ ደረጃ ሁለት ሊሆን ይችላል። ደረጃ አንድ ደግሞ በጣም በጣም ዝቅተኛ ነው።»

በመላው ዓለም የሚያደርሰው የሞት ጉዳት ከፍ እያለ የመጣው የጡት ካንሰር በጎርጎሪዮሳዊው 2011 ዓ.ም. ከ580 ሺህ የሚበልጡ ሴቶችን ሕይወት ቀጥፏል። ለወትሮው ያደጉ ሃገራት የጤና ችግር ብቻ ተደርጎ ይታይ የነበረው ካንሰር አሁን ከአኗኗር ዘይቤ እና አመጋገብ ለውጥ ጋር በተገናኘ በአፍሪቃ ሃገራትም ዋና የጤና ችግር እና የሞት ምክንያት እየሆነ መምጣቱንም የዓለም የጤና ድርጅት ያስረዳል። በየዓመቱ ሁለት ሚሊየን ገደማ ሴቶች በጡት ካንሰር እንደሚጠቁ ያመለከተው የዓለም የጤና ድርጅት ሊሰናበት ከሁለት ወራት ያነሱ ቀናት በሚቀሩት በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2018 ብቻ 627 ሺህ ሴቶች በዚሁ የጤና ችግር ምክንያት መሞታቸውንም ይገልጻል። ይህም ለሴቶች ሞት ምክንያት ከሚሆኑ የጤና እክሎች 15 በመቶዉን ይይዛል።

የጡት ካንሰር አስቀድሞ በሚደረግ ምርመራ እና ክትትል ሊደረስበት የሚችል፤ ለህክምናውም ቢሆን በመጀመሪያ ደረጃ እንደተከሰተ የሚቀል እና የመዳን ዕድሉም ከፍተኛ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜው ይመክራሉ፤ ያሳስባሉ። ዓመት ጠብቆም ቢሆን ጉዳዩ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት እየሳበ የመነጋገሪያ ርዕስ ከሆነ ውሎ አድሯል። እንዲያም ሆኖ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው ግንዛቤ ግን አሁንም ብዙ መሠራት እንደሚኖርበት እና ቅስቀሳውም መጠናከር እንዳለበት አመላካች መሆኑን ነው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ከፍተኛ ስፔሻሊስት ዶክተር ማቴዎስ አሰፋ የገለፁልን።

የማሞግራፊ ምርመራ

የካንሰር ከፍተኛ ሃኪሙ እንደሚገልፁት በሽታውን ከከፍተኛ ስቃይ ጋር ብቻ የማገናኘቱ የተሳሳተ ግንዛቤ ሰዎች በሽታው ገና በዝቅተኛ ደረጃ ሳለ ወይም ሲጀምር ወደ ህክምና እንዳይሄዱ ያዘናጋ ይመስላል። ያም ሆኖ ግን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የጡት ካንሰር አብዛኛውን ሴቶች በመጉዳት ላይ ያለ ህመም እየሆነ መምጣቱን ሃኪሞቹ እያስተዋሉት ነው።

የጡት ካንሰር በቀላሉ በቤት ውስጥ በራስ ፍተሻ ጀምሮ ወደ ከፍተኛው የቴክኖሎጂ ድጋፍ ወደሚያሻው ምርመራ መሄድ የሚቻል የጤና ችግር ነው። ይህንኑ ነው የካንሰር ስፔሻሊስቱ የሚናገሩት።

በነገራችን ላይ የጡት ካንሰር የሴቶች ብቻ የጤና ችግር አድርገው የሚመለከቱ ጥቂት አይደሉም። እውነቱ ግን በጡት ካንሰር ቁጥሩ ይቀንስ እንጂ ወንዶችም ተጠቂዎች ናቸው። ዶክተር ማቴዎስም ይህን ያረጋግጣሉ።

ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላው ሴቶችን የሚያጠቃው የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ነው። ለበሽታው መንስኤ የሆነው ሂውማን ፓፒሎማ የተሰኘው ቫይረስ ለበርካታ ዓመታት ሳይታወቅ ሰውነት ተደብቆ ሊኖር እንደሚችል ነው የሚነገረው። የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመጪው ኅዳር ወር በመላ ሀገሪቱ ዕድሜያቸው 14 ዓመት የሆኑ አዳጊ ሴት ልጆችን የማህጸን ካንሰር ክትባት እንደሚሰጥ በፌስቡክ ባሰራጨው መረጃ ጠቁሟል።

የካንሰር ሴል ገጽታ

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የእናቶች እና ሕጻናት ጤና ባለሙያ በቂ መረጃ እንደሌላቸው በመግለፅ በሌላ ጊዜ እንድንደውልላቸው በመጠየቃቸው ዝርዝሩን ለመረዳት አልቻልንም። ሆኖም ግን ከካንሰር ከፍተኛ ሀኪሙ ከዶክተር ማቴዎስ አሰፋ ገለፃ የተረዳነው የማሕፀን ጫፍ ካንሰር አዲስ አበባ ውስጥ ሴቶችን በግንባር ቀደምትነት ከሚያጠቃው የካንሰር ዓይነት ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ነው።

ቅድመ ምርመራ በማድረግ የጡት ካንሰርም ሆነ የማሕጸን ጫፍ ካንሰር ተባብሰው የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ በሕክምና መርዳት እንደሚቻል የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያ ሀኪም አፅንኦት ይሰጣሉ። የዳበረ የህክምና ታሪክ ባላቸው እና በዘመናዊ መሳሪያዎች የሚታገዝ ህክምና በሚሰጥባቸው ሃገራት ሴቶች እነዚህን ምርመራዎች በየዓመቱ እንዲያደርጉ ሁኔታዎች የተመቻቹ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም እንኳን በገጠሩ አካባቢ ይህን የማድረግ የአቅም ውሱንነት ቢኖርም በከተማ አካባቢ የሚኖሩ ወገኖች ታሞ ከመማቀቅ እንዲሉ አስቀድመው ምርመራ የማድረጉን ልማድ ለማዳበር ቢሞክሩ፤ ሌሎችንም ቢያበረታቱ የሰው ሕይወት ሊያድኑ በሚችሉ የጤና እክሎች ከመቀጠፍ የማዳን ዕድሉ እንደሚሰፋ ይታመናል። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ዶክተር ማቴዎስ አሰፋን በእናንተ ስም እናመሰግናለን። እንደ ዶክተር ማቴዎስ ያሉ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎች እንዲያብራሩላችሁ የምትፈልጓቸውን ጥያቄዎቻችሁን መላክ ትችላላችሁ። ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን። 

ሸዋዬ ለገሠ

ተስፋለም ወልደየስ

ተዛማጅ ዘገባዎች

ተከታተሉን