የጥላቻ ፅሑፎችና ንግግሮችን ለማስቆም የመንግሥት ርምጃ ዘግይቶአል

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:34 ደቂቃ
06.12.2018

ወደ ማኅበረሰቡ የሚሰራጩ ጽሑፎችና ንግሮች የማኅበረሰቡን ሰላም ሊጠብቁ ይገባል

ነፃ ኃሳብ የሚገለፀዉ በዴሞክራሲ መንገድ ነዉ፤ ወደ ማኅበረሰቡ የሚሰራጩ ጽሑፎችና ንግግሮች የማኅበረሰቡን ሰላም ሊጠብቁ ይገባል። መንግሥት የጥላቻን ንግግሮችን ለመግታት የሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ዘግይቶአል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን የጥላቻ ንግግሮችን በመንዛር ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል።

በኢትዮጵያ የጥላቻና ሕዝብን ከሕዝብ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ ንግግሮች እየተበራከተ መምጣቱ በማኅበረሰቡ ዘንድ አሳሳቢነቱ እየተነገረ ነዉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ችግር ያለዉን ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ የጥላቻ ንግግር እና ፅሑፍ ለመከላከል ሕግ ለማዉጣት እየሠራ እንደሆነ አስታዉቋል። በማኅበራዊ መገናኛም ሆነ በሌሎች ሕዝባዊ መገናኛዎች ጥላቻ አዘል ንግግሮችን እንዴት መከላከል ይቻላል? አደገኛ መዘዝ ያለውን የጥላቻ ንግግር ለመገደብ የሚወጣዉ ሕግስ የሰዉን ልጅ የመናገር እና የመጻፍ መብት እንዳይጫን ምን መደረግ ይኖርበታል? አዜብ ታደሰ በጉዳዩ ላይ ዘገባ አጠናቅራለች።

የሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅቶች ባወጡት ዘገባ መሰረት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም ሆነ በኅበረተሰቡ ዘንድ በሚታዩና በሚሰሙ የጥላቻ ንግግሮች ምክንያት በመጠናቀቅ ላይ ባለዉ ጎርጎሮሳዊ ዓመት 2018  የመጀመርያ ግማሽ ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ ከ 1,4  ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ከመኖርያ ቀየዉ ማፈናቀሉን፤ የበርካቶችንም ሕይወት ማሳጣቱን ያመለክታል። ይህን ተከትሎ መንግሥት ወደ ወንጀል የሚከቱ ጥላቻ አዘል ንግግሮችን እና ጽሑፎችን የሚያሰራጩ ዜጎችን ለመግታት ሕግ ለማዉጣት እየሠራ መሆኑን አሳዉቋል።  ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የ «አምነስቲ ኢንተርናሽናል»   የምሥራቅ አፍሪቃ የሰብዓዊ መብት አጥኚ አቶ ፍሰሐ ተክሌ ለ«DW» እንደገለፁት ፤ የጥላቻ ንግግሮች ወይም ጽሑፎች በተመድ ደንብ መሠረትም ሃሳብን ነጻነት በመግለፅ ሕግ ባለመካተቱ ይህ የመንግሥት ርምጃ ትክክል እንደሆነ ያስረዳሉ።hatte speech

ጥላቻን የሚነዙ ንግግሮች ጉዳት ማስከተላቸውን ያመለከተው ሂውማን ራይትስ ዎች እንዲህ ላሉ ችግሮች መፍትሄ ተብሎ የሚደነገገው ሕግ አተገባበር እና አተረጓጎም ላይ ሌላ ችግር እንዳያስከትል ስጋቱን ይገልጻል። የአምነስቲው የምሥራቅ አፍሪቃ የሰብዓዊ መብት አጥኚ አቶ ፍሰሐ ተክሌም በተመሳሳይ ሕጉ ተፈፃሚ ሲሆን አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎች መዉሰድ እንደሚገባ እና ሕጉ ሲረቀቅም አሻሚ ትርጉም እንዳይኖረዉ ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ።

ነፃ ኃሳብ የሚገለፀዉ በዴሞክራሲ መንገድ ነዉ፤ ወደ ማኅበረሰቡ የሚሰራጩ ጽሑፎችና ንግሮች የማኅበረሰቡን ሰላም ሊጠብቁ ይገባል ያለዉ ጋዜጠኛ ዉብሸት ታየ በበኩሉ፤ መንግሥት የጥላቻን ንግግሮችን ለመግታት የሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ዘግይቶአል ይላል።  በ«DW» የፌስቡክና ዋትስኣፕ ገጾች ላይ አስተያየታቸዉን ያስተላለፉልን አብዛኞቹ ተከታታዮች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብሔር ተኮር ጥላቻን የሚነዙ ዜጎችን ለማስቆም መንግሥት ርምጃን እንዲወስድ ያበረታታሉ።

በምዕራቡ ዓለም እንደሚደረገዉ ሁሉ በማኅበራዊ መገናኛ የሚሰራጩ ጥላቻ አዘል ንግግሮችን እና ጽሑፎችን ለተቋሙ በማሳወቅ ማገድ ይቻላል፤ ለማኅበረሰቡም ግንዛቤ መስጠትም ሌላዉ መፍትሄ መሆኑን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል አጥኚ አቶ ፍስሐ ተክሌ አክለዋል። 

ባለፈዉ በኢትዮጵያ በነበረዉ ሥርዓት የመናገርና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተጥሶበታል የተባለዉ የሲቪል ማህበረሰብና የፀረ-ሽብር ሕግ፤ መንግሥት አሻሽሎ ለማዉጣት እየሠራ መሆኑ ተመልክቶአል። አዲስ ይወጣል በተባለዉ ሕግ እንዳለፈዉ ጊዜ ሁሉ ሃሳብን በነፃ የመናገር ነፃነት እንዳይጣስ ጥንቃዌ መወሰድ እንዳለበት ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የ «አምነስቲ ኢንተርናሽናል»  የምሥራቅ አፍሪቃ የሰብዓዊ መብት አጥኚ አሳስበዋል ። 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ተከታተሉን