1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥሬ ሃብት ፍላጎትና እጥረት

ሐሙስ፣ ኅዳር 16 2003

የጀርመን ኢንዱስትሪዎች የጥሬ ሃብት እጥረት ስለመኖሩ መናገር ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

https://p.dw.com/p/QIDP
...ጥሬ ሃብት አሰሳ...ምስል Deutsche Rohstoff AG

በሌላዉ አካባቢ እንደልብ የማይገኘዉ ለኢንዱስትሪ ምርቶች ግብዓት ከሚዉለዉ ጥሬ ሃብት ዘጠና በመቶ የሚሆነዉን ለዓለም ገበያ ታቀርብ የነበረችዉ ቻይናም ሳይታሰብ ሽያጭ አቁማለች። ይህም የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያሻቅብ አስተዋፅኦ ማድረጉ እየተነገረ ነዉ። የጀርመን የኤኮኖሚ ሚኒስትር ራይነር ብሩደርለ ለዚህ ችግር መፍትሄ ያሉት፤ ጥሬ ሃብት ፈላጊዎቹ ኢንዱስትሪዎች ማዕድን የማዉጣት መብትን ከግምት ያስገባ ኅብረት መመሥረትን ነዉ። ከጀርመን ኢንዱስትሪዎች ገሚሶቹ ለዚህ ጥሪ ፈጣን ምላሽ ሰጥተዋል። ትልቁ የአገሪቱ የብረት ኩባንያ ታሰን ክሩፕም «አፍሪቃን ለቻይና አንተዉም» የሚል መፈክር መሰል መመሪያ አወጣ። ዓላማዉ የጀርመን ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን ጥሬ ሃብት በጋራ ከያለበት መግዛት እንዲችሉ ማስተባበር ነዉ። ይህም እየተሟጠጡ በመሄድ ላይ ያሉትን እንደየከበሩ ድንጋዮችና የብረት ማዕድናት የሚገኙበትን መንገድ ያመቻቻል። የበርካቶችን ትኩረት የሳበዉ ይህ በኅብረት ወደገበያዉ የመዝለቅ ሃሳብ ግን ኩባንያዎቹ ወትሮ ከገበያዉ ያገኙት የነበረዉን ድርሻ አይጨምረዉም። የፌደራል የዋጋ መዳቢ ሚኒስትር አንድሪያስ ሙንድ፤

«ይህ የሚገናኘዉ ከዓለም ገበያ ጋ ነዉ፤ እኔም እደሚመስለኝ የጀርመን ኩባንያዎች በጋራ ተሰባስበዉ ቢሆን ኖሮ ያላቸዉ ገበያ ድርሻ አነስተኛ በሆነ ነበር። ሆኖም ያንን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ምርመራ ማካሄድ ያሻል።»

Deutsche Rohstoff AG Vorbereitung Testförderung Öl im Allgäu
ምስል Deutsche Rohstoff AG

ጥሬ ሃብትን እንደልብ ለማግኘት በጋራ ለመገብየት ከመተባበሩ ባሻገር የተዘረጉት እቅዶች በአጭር ጊዜ ወደተግባር የሚለወጡ ዓይነቶች አይመስሉም። በኢንዱስትሪዉ አካባቢ፤ አንዳንድ ኩባንያዎች ለዘለቄታዉ ጥሬ ሃብትን ለማግኘት ከአዳጊ አገራት ጋ የቴክኒክ እዉቀት ልዉዉጥ ማድረግ እንደሚበጅ ያስባሉ። ይህ በርግጥ አዲስ ስልት አይደለም። በተማከለዉ የዉጭ ፖሊሲዋ አማካኝነት ቻይና ጥሬ ሃብትን በለዉጡ እየሰበሰበት በምትኩ የመሠረተ ልማት ፕሮዤዎችን በተለይ በአፍሪቃ እየተረከበች ትሰራለች። ጀርመናዉያን ኩባንያዎችም ሃሳባቸዉ ተቀባይነት ካገኘ ምናልባት በመንግስት ድጋፍ እየተረዱ ሊገቡበት ይሻሉ። ቀደም ሲል ግን የኤኮኖሚ ሚኒስትሩ መንግስት በቀጥታ በዚህ ጉዳይ እንደማይገባ ጠቁመዋል። የልማት ሚኒስቴር በበኩሉ የጀርመን መንግስትን የልማት ፖሊሲና ለኩባንያዎቿ የሚያስፈልገዉን ጥሬ ሃብትን የማግኘት ሁኔታ በማጣመር ዉጤታማ ተግባር ማከናወን እንደሚቻል ያስረዳል። የፌደራል ልማት ሚኒስትር ድሪክ ኒብል የጀርመን ኢንዱስትሪ ማኅበር ጥሬ ሃብትን አስመልክቶ ባካሄደዉ ጉባኤ ላይ ይህን ጠቅሰዋል፤

«የልማትና የጥሬ ሃብት ፖሊሲ መቃረን አይኖርባቸዉም። የምንጋራዉ በርካታ የጋራ ፍላጎትና ጥቅም አለ። እናንተ የልማት ፖሊሲ ልምዳችንን እኛ ደግሞ የእናንተን ገንዘብ እንጠቀማለን። እናም ሁለታችንም ከአንድ ግብ ለመድረስ የጋራ ፍላጎት ካለን፤ ሁሉም ባለድርሻ ትርፋማ የሚሆንበትን መንገድ እናበጃለን።»

የጀርመን የተቃዉሞ ፖለቲካዉ ወገን ግን ምንም እንኳን የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች በዉጭ ተባብረዉ መንቀሳቀሳቸዉን ቢቀበለዉም፤ ተግባራቸዉን ያለ ሽሚያና የመንግስት ድጋፍ እንዲያከናዉኑ ይፈልጋል። የኤኮኖሚ ምሁር የሆኑት የአረንጓዴዉ ፓርቲ ቃል አቀባይ ካርሽቲን አንድሪያስ አካሄዱ ጥንቃቄ ያሻዋል ባይ ናቸዉ፤

«መንግስት ጥሬ ሃብት ፈላጊ ኢንዱስትሪዎች በተሰባሰቡበት ቡድን ዉስጥ ባለድርሻ እንዲሆን አልመክርም። ያንንም በኤኮኖሚ ኮሚቴ ዉስጥ ተነጋግረንበታል፤ ምክንያቱም በዚህ ረገድ እጅግ የሚያሳስበን ጉዳይ አለ፤ የፌደራል መንግስቱ ስልት ምን እንደሚመስል ማየት እንፈልጋለን። በቀጣይም ጉዳዩን በቅርበት እንከታተላለን። ትብብሩ የልማት ርዳታን በለዉጡ ሰጥቶ ጥሬ ሃብትን ለመሰብሰብ ከሆነ የልማት ርዳታን ፅንሰ ሃሳብ በትክክል ያለመገንዘብ ዉጤት ነዉ። ያ ደግሞ ከሰብዓዊ አካሄዳችን ጋ አይገናኝም።»

የጀርመን ኢንዱስትሪዎች የጥሬ ሃብት እጥረት እንዳይገጥማቸዉ፤ በተወዳዳሪያቸዉ የቻይና ኩባንያዎችም እንዳይበለጡ ቢታሰብም፤ የጀርመን የጥሬ ሃብት ተጠቃሚ በሚል ኮሚቴም ሆነ ሌላ ዓይነት ድርጅት ይመስረት፤ ከመንግስትስ ምን ያህልና እንዴት ያለ ድጋፍ ያግኝ የሚለዉ ምላሽ አላገኘም።

ኒኮላስ ማርቲን

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ