1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 15 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ ጥቅምት 15 2014

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ ብርቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። አሰልጣኙን ማን ይተካቸው የሚለው ጥያቄ ተጠናክሯል። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ቫለንሺያ ስፔን ውስጥ በግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ክብረ-ወሰን ሰብራለች፤ ታሪክም ሠርታለች።

https://p.dw.com/p/42A9m
Japan Tokio | Letesenbet Gidey
ምስል Petr David Josek/AP/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ ብርቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። አሰልጣኙን ማን ይተካቸው የሚለው ጥያቄ ተጠናክሯል። ማንቸስተር ዩናይትድ ባለፈው የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታ በላይስተር ሲቲ 4 ለ2 ከተረታ በኋላ ትናንት በሜዳው በሊቨርፑል የ5 ለ0 ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል። ሊቨርፑል ዋትፎርድን ያሸነፈበት የ5 ለ0 ውጤት በዚህ ሳምንቱ ጨዋታም ማንቸስተር ዩናይትድ ላይ ደግሞታል። ዋትፎርድ በበኩሉ በሊቨርፑል ላይ ባይሆንም ቅዳሜ ዕለት 5 ግብ በማስቆጠር የ8ኛ ዙር ጨዋታ ንዴቱን ተወጥቷል።  ቸልሲ ተጋጣሚውን 7 ለ0 አንኮታኩቷል። በቡንደስሊጋው አሰልጣኙ በኮቪድ የተነሳ በሌሉበት የተጋጠመው ባየርን ሙይንሽን ዳግም ድል ቀንቶታል። በደረጃ ሰንጠረዡ ዶርትሙንድ በአንድ ነጥብ ይከተለዋል። ማክስ ፈርሽታፐን በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተንን ዳግም ድል አድርጎታል። ትናንት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ቫለንሺያ ስፔን ውስጥ በግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ክብረ-ወሰን ሰብራለች፤ ታሪክም ሠርታለች። 

አትሌቲክስ

ግማሽ ማራቶን ለተሰንበት ግደይ ክብረወሰን ሰበረች

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ትናንት ቫሌንሺያ ስፔን ውስጥ በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር የዓለም ክብረ-ወሰን በመስበር አሸንፋለች።  በታሪክ ከ63 ደቂቃዎች በታች በመሮጥ ለድል የበቃች የመጀመሪያዋ ሴት አትሌትም ተብላለች። ወጣቷ አትሌት ከዚህ ቀደምም በ5000 እና 10,000 ሜትር የሩጫ ውድድሮችም የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ናት። ለተሰንበት ከስድስት ወራት በፊት በኬንያዊቷ አትሌት ሩት ቼፕንጌቲች ኢስታንቡል ቱርክ ውስጥ ተይዞ የነበረውን የግማሽ ማራቶን ክብረ ወሰን 1 ሰዓት ከ2 ደቂቃ ከ52 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት ከ1 ደቂቃ በላይ ማሻሻል ተሳክቶላታል።  በዚህ ውድድር ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት የዓለምዘርፍ የኋላ ሰው 63 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃ ስታገኝ፤ ኬንያዊቷ ሼይላ ቼፕኪሩይ ከየዓለምዘርፍ 1 ደቂቃ ከ2 ሰከንዶች ዘግይታ በሦስተኛነት አጠናቃለች።

Leichtathletik-Meeting in Valencia I Weltrekord 50000 I Letensebet Gidey
ምስል Manuel Bruque/Agencia EFE/Imago Images

እዛው ቫሌንሺያ ከተማ ውስጥ በተመሳሳይ ርቀት በተደረገው የወንዶች የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ ኬንያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተከታትለው በመግባት ገነው ወጥተዋል። ኢትዮጵያዊው አትሌት ሙክታር ኢድሪስ ስድሰተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል። ኬኒያዊው አትሌት አቤል ኪፕቹምባ የዓመቱ ምርጥ ሰአት በተባለ የ58 ደቂቃ ከ07 ሰከንድ ቆይታ በመግባት ነው ያሸነፈው። የሀገሩ ልጆች ሮኔክስ ኪፕሩቶ እና ዳንኤል ማታይኮ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነው ገብተዋል። ኬኔዲ ኪሙታይ እና ፊሌሞን ኪፕሊሞ ደግሞ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃን ይዘዋል።

የባሕር ዳር ስታዲየም ላይ በአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF)የተወሰደው ርምጃ ፖለቲካዊ ነው ሲል የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ጽ/ቤት ዐስታወቀ። ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ወቅታዊ ኹኔታ አንጻርም ግብጻዊው የቡድኖች ፍቃድ ሥራ አስኪያጅ መሐመድ ሲዳት ስታዲየሙ ጨዋታ እንዳያስተናግድ ዝግ ማድረጋቸው ግለሰባዊ ተጽዕኖ ያለበት እንደሆነም ተገልጧል። የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት የስፖርት ግብዓቶች ኃላፊ አቶ ባንተአምላክ ሙላት ዛሬ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በሰጡት መግለጫ፦ ካፍ በባሕር ዳር ስታዲዮም ዙሪያ የሰጣቸው አስተያየቶች አንዳንዶቹ ትክክለኛ ቢሆኑም ብዙዎቹ ግን ከእውነት የራቁ ናቸው፤ አንቀበላቸውም ብለዋል።

በተጫዋቾች የልብስ መቀየሪያና መታጠቢያ ክፍሎች፣ በመጫወቻ ሜዳ ሳርን፣ በመኪና ማቆሚያ ቦታን፣ በእሳት አደጋ መከላከል፣ በደህንነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀትና በመሳሰሉት የቀረቡ ቅሬታዎችንና አስተያየቶችን እንደማይቀበሉ አቶ ባንተ አምላክ አስረድተዋል። ከኢትዮጵያ ወቅታዊ አንፃር ግብፃዊው የክለቦች የፍቃድ ክፍልሥራ አስኪያጅ መሐመድ ሲዳት ስታዲዮሙ ለጨዋታ ዝግ እንዲሆን ማስደረጋቸው ግለሰባዊ ተፅዕኖ ያለው እንደሚመስላቸው ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። ለባሕር ዳር ስታዲየም ቁሳቁስ ማሟያና ያልተስተካከሉ ሥራዎችን ለማከናወን 2 ቢሊዮን ብር ከፌደራል መንግሥት ቢጠየቅም፤ እስካሁን ተግባራዊ ምላሽ እንዳልተገኘም አብራርተዋል። 

Äthiopien Bahir Dar | Amhara Jugend- und Sportbüro
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የአማራ ክልል መንግስት እስካሁን ለስታዲዮሙ ግንባታ 700 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን የባሕር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን የላከልን ዘገባ ይጠቁማል። ባሕር ዳር ስታዲየም በካፍ ከታገደ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን ከሀገር ውጭ ለማድረግ በመገደዱ፤ በአማራጭነት ኬንያ፣ዚምቧቤን እና ደቡብ አፍሪቃን መምረጡ ቀደም ሲል ተዘግቧል። ሦስቱም ሃገራት ጨዋታውን ለማስተናገድ ፈቃደኛነታቸውን ማሳየታቸውን ተዘግቧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ዚምቧቤ ለመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታው ማቅናቱ ስለማይቀር ግን፤ «በአንድ የአውሮፕላን ጉዞ እና መጠነኛ ወጪ ጨዋታውን በደቡብ አፍሪካ ለማድረግ» መወሰኑን ሰሞኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጧል። በመሆኑም ከጋና ጋር ያለውን ጨዋታ ፊፋ በሚያስቀምጠው ቀን በደቡብ አፍሪቃ ኦርላዶ ስታዲየም ለማድረግ ፌዴሬሽኑ ከደቡብ አፍሪቃ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር መስማማቱም ተዘግቧል።

በሌላ የእግር ኳስ ዜና፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ማክሰኞ ጥቅምት 16 ቀን፣ 2014 ከቀኑ 10 ሰዓት አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ ይደረጋል። በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ ለማለፍ በቅድመ ማጣሪያ ውድድር ኡጋንዳ ካምፓላ ላይ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሉሲዎቹ 2ለ0 በሆነ ውጤት መሸነፋቸው አይዘነጋም። ሉሲዎቹ በነገው ጨዋታ ጥሩ እድል እንዲገጥማቸው እንመኛለን።

Äthiopien - Bahir Dar Stadium
ምስል DW/A. Mekonnen

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች አስደማሚ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ቸልሲ እና ሊቨርፑል ተጋጣሚዎቻቸውን ድባቅ መትተዋል። ችልሲ ቅዳሜ እለት ባደረገው ግጥሚያ ኖርዊች ሲቲን የ7 ለ 0 እጅግ አሸማቃቂ ሽንፈት ነው ያከናነበው። በእለቱ ማሶን ማውንት ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠርቷል።

ቸልሲ ቅድሚያ የሚያሰልፋቸው ሁለት ወሳኝ አጥቂዎቹ ጀርመናዊው ቲሞ ቬርነር እና ቤልጂጋዊው ሮሜሉ ሉካኩ በሌሉበት ነው ኖርዊችን የግብ ጎተራ ያደረገው። ባለፈው ሳምንት ማልሞይን በሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ባሸነፉበት ግጥሚያ ጉዳት ስለደረሰበት ነው ሮሜሉ ሉካኩ ያልተሰለፈው። በሁለቱ ፈንታ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል የሀገራቸው ልጅ ጀርመናዊው ካይ ሐቫርትስ፣ ካሉም ሁድሰን-ኦዶይ እና ማሲን ማውንትን ከፊት አሰልፈው ነው ለድል የበቁት።

በበነጋታው ትናንት ደግሞ ሊቨርፑል ልቆ በታየበት ፍልሚያ ማንቸስተር ዩናይትድን በሜዳው 5 ለ0 ኩም አድርጎታል። ሞሐመድ ሳላህ ኦልትራፎርድ ሜዳ ውስጥ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ከ18 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው ተጨዋች ሆኖ ታሪክ ሠርቷል። ናቪ ኪዬታ ለሊቨርፑል የመጀመሪያውን ግብ ከመረብ እንዲያሳርፍ ያመቻቸውም ሞሐመድ ሳላኅ ነው። ከአምስቱ ግቦች አንዱ የዲዬጎ ጆታ ነው። ሊቨርፑል በኦልትራፎርድ ድሉ የናቢ ኪዬታ እና ጄምስ ሚልነር በጉዳት መውጣት መጠነኛ ቅሬታ ሳይፈጥርበት አልቀረም። ጄምስ ሚልነር ማንም ሳይነካው ሜዳ ላይ እግሩ ተሸማቆ ነው የተቀየረው። ናቢ ኪዬታ ግን ተቀይሮ በገባው ፖል ፖግባ በመጥፎ ሁኔታ ጉዳት ደርሶበት በቃሬዛ ነው የወጣው። ፖል ፖግባም በቀጥታ ቀይ ካርድ ዐይቶ ከሜዳ ተሰናብቷል። በእርግጥ ከሜዳ ሲሰናበት 30 ደቂቃ ቢቀርም ሊቨርፑል አስቀድሞ 4 ግቦችን አስቆጥሮ ነበር። እናም ማንቸስተር ዩናይትድ በ10 ተጨዋቾች ከመከላከል እና 5 ለ0 ከመሸነፍ ውጪ ምንም ማድረግ አልቻለም።

UK Premierleague | Manchester United vs Liverpool
ምስል Oli Scarff/AFP/Getty Images

አንድ ነገር ግን የሚቻል ይመስላል። ተደጋጋሚ ሽንፈት ያስተናገዱት የ48 ዓመቱ አሰልጣኝ ኦሌ ጉናር ሶልስካዬር የመሰናበታቸው ጉዳይ። ለብዙዎች ያ ሳይታለም የተፈታ ነው። ግን አሰልጣኙን ማን ይተካቸው? የበርካቶች ጥያቄ ነው። የሊቨርፑል የቀድሞ ዕውቅ ተከላካይ ጃሚ ካራጌር በስካይ ስፖርት ትንታኔው ወቅት፦ «ኦሌ ጉናር ሶልስካዬር ለማንቸስተር ዩናይትድ ትክክለኛው አሰልጣኝ አይደሉም» ብሏል። «ሶልስካዬር እንደ ዬርገን ክሎፕ፣ ፔፕ ጓርዲዮላ ወይንም ቶማስ ቱኹል ሊሆኑም አይችሉም» ሲል የማንቸስተር ዩናይትዱን አሰልጣኝ ተችቷቸዋል።  ትችቱ ከጃሚ ካራጌር ብቻ ሳይሆን፤ አሰልጣኝ ኦሌ ጉናር ሶልስካዬር ይሰናበቱ የሚለው ድምፅ እያስተጋባ ነው። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ያ መሆኑ የማይቀር ነው።

ከወዲሁ ታዲያ እሳቸውን ማን ይተካ ለሚለው የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። ከዚነዲን ዚዳን፤ እስከ አንቶኒዮ ኮንቴ፤ ከማውሪሲዮ ፖቺቲኖ እስከ ኤሪክ ቴን ሐግ፤ ብሎም ብሬንዳን ሮጀርስ ወደ ኦልትራፎርድ ቢመጡ የሚሉ መላ ምቶች እየተሰሙ ነው። ሪያል ማድሪድን በሻምፒዮንስ ሊግ ለሦስት ጊዜያት ዋንጫ ለማንሳት ያበቃው የ49 ዓመቱ አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ግን ውጥረት እና ጭንቀት ባለበት ሁኔታ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ እንደማያቀና የፈረንሳይ መገናኛ አውታሮች ዘግበዋል። በዚያ ላይ ዚነዲን ዚዳን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንን ወደፊት ሊያሰለጥን ነው እየተባለም ነው። የሌሎቹም አሰልጣኞች ጉዳይ ገና ያለቀለት አይደለም።  ሆኖም ማንቸስተር ዩናይትድ አዲስ አሰልጣኝ እንዲያመጣ ግፊቱ አይሏል።

England Manchester United Jadon Sancho
ምስል Martin Rickett/imago images/PA Images

ሌላው ቀርቶ የ36 ዓመቱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ከማንቸስተር ዩናይትድ አጥቂነት ወደ አሰልጣኝነት እንዲሸጋገር የሚጠይቁ ደጋፊዎች ተበራክተዋል። በእርግጥ ሮናልዶ የአሰልጣኝነት ልምድ የለውም። እናም ምናልባት መጀመሪያ በሌላ አሰልጣኝ ስር ሆኖ ልምምድ በማድረግ ወደፊት የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎችን ፍላጎት ያሟላ ይችል ይሆናል። ለዚያም ነው የቶትንሀም ሆትስፐር የቀድሞ አሰልጣኝ ቲም ሼርዉድ ስለ ክርስቲያኖ ሮናልዶ አስቀድመው የተነበዩት። «ይህ ወጣት አሰልጣኝ እንደሚሆን መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ»ም ብለዋል። «እወራረዳለሁ፤ ከአመት ከመንፈቅ በኋላ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ይሆናል» ሲሉ ስለ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ተናግረዋል። ቡድኑ በሜዳው የ5 ለ0 ሽንፈት ሲከናነብ ከመቆዘም ውጪ ምንም ማድረግ ያልቻለው ፖርቹጋላዊ አጥቂ ምናልባት ወደፊት አሰልጣኝ ሆኖ የማንቸስተር ዩናይትድ ሰጋፊዎችን ሕልም ዕውን ያደርግም ይሆናል። ያም ቢሆን ግን የጊዜ ጉዳይ ነው።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች፦ ባየርን ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት ሆፈንሀይምን 4 ለ0 በማሸነፍ በደረጃ ሰንጠረዡ መሪነቱን አስጠብቋል። ለሁለት ጊዜያት ጸረ ኮሮና ክትባት ተከትበው በኮቪድ መያዛቸው የተገለጠው ጀርመናዊ አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማን በሌሉበት ነው ባየርን ሙይንሽን ለሁለተኛ ጊዜ ለድል የበቃው። ቀደም ሲል በሻምፒዮንስ ሊግ ቤኔፊካን 4 ለ0 ባሸነፉበት ጨዋታም አሰልጣኙ በኮሮና የተነሳ ሊዛቦን ሜዳ ውስጥ የተወከሉት በረዳቶቻቸው ነበር። 21 ነጥብ ይዞ ከባየርን ሙይንሽን በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ አርሜኒያ ቢሌፌልድን በሜዳው 3 ለ1 አሸንፎታል። ዘንድሮ ወደ ቡንደስሊጋው ያደገው አርሜኒያ ቢሌፌልድ በመጣበት እግሩ ሊመለስ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ከግሬውተር ፊዩርት ብቻ በልጦ በ5 ነጥቡ 17ኛ ደረጃ ላይ ተዘርግቷል። ከበታቹ ያለው ግሬውተር ፊዩርት 1 ነጥብ ብቻ አለው። ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች፦ ኮሎኝ ከባየር ሌቨርኩሰን ሁለት እኩል ሲወጣ፤ ሽቱትጋርት እና ዑኒዬን ቤርሊን አንድ እኩል አቻ ተለያይተዋል። ፍራንክፉርት በቦኹም የ2 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል።

Deutschland Bundesliga VfB Stuttgart vs Union Berlin
ምስል Matthias Koch/imago images

በስፔን ላሊጋ ትናንት ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ የተጋራው ሳንሰባስቲያን በ21 ነጥብ በአንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባርሴሎናን ትናት 2 ለ1 ያሸነፈው ሪያል ማድሪድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በሳንሰባስቲያን በአንድ ነጥብ ይበልጣል። ትናንት ሌቫንቴን 5 ለ3 ያሸነፈው ሴቪያ ነጥቡን ከሪያል ማድሪድ እኩል 20 አድርሷል። ሪያል ማድሪድም እንደ አትሌቲኮ ማድሪድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ቤቲስ እና ኦሳሱና 18 ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ ከ4ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ዛሬ ማታ፦ ጌታፌ ከሴልታ ቪጎ ጋር ጨዋታ አለው።

ፎርሙላ አንድ

USA | Formel 1 I US Grand Prix - Austin Texas | Max Verstappen ist der Sieger
ምስል Antonin Vincent/imago images/PanoramiC

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ዳግም ሽንፈት ገጥሞታል። በትናንቱ የዩኤስ ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም መሪነቱን የጨበጠው የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን ነው። የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ሐሚልተን በትናንቱ ውድድር የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። በአጠቃላይ ነጥብም ማክስ ፈርሽታፐን በአነስተኛ ልዩነትም ቢሆን መሪነቱን ጨብጧል። 275.5 ነጥብ ያለው ሌዊስ ሐሚልተን በማክስ ፈርሽታፐን በ12 ነጥብ ይበለጣል።  በፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም 12 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላገኘው ተወዳዳሪ የሚሰጥ ነው። በአንድ ውድድር ላይ አንደኛ ደረጃ የሚያገኝ አሽከርካሪ 25 ነጥብ ያገኛል። 2ኛ የሚወጣ 18 ነጥብ፤ 3ኛ ደግሞ 15 ነጥብ ይሰጠዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ