1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 9 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 9 2013

በዓለም ግማሽ ማራቶን በቡድን ኹለተኛ የወጣው የኢትሌቲክስ ቡድን ዛሬ አዲስ አቀባበል ተደርጎለታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሊቨርፑሉ የመሀል ተከላካይ ጂርጂል ቫንጃይክ ጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ለወራት ከውድድር ይርቃል መባሉ አስደንጋጭ ዜና ኾኗል። በጀርመን ቡደስ ሊጋ ኮልን ከተማ እና ሻልከ የመጀመሪያ ነጥባቸውን ትናንት አስመዝግበዋል።

https://p.dw.com/p/3k987
Bundesliga Arminia Bielefeld vs. FC Bayern München | 2. TOR Bayern
ምስል Wolfgang Rattay/Reuters

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ፖላንድ ግዲኒያ ውስጥ በተከናወነው 24ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር በኹለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ቡድን ዛሬ አቀባበል ተደርጎለታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያ የሊቨርፑሉ የመሀል ተከላካይ ጂርጂል ቫንጃይክ ጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ለወራት ከውድድር ሊርቅ መነገሩ ለቡድኑ አስደንጋጭ ዜና ኾኗል። በጀርመን ቡደስ ሊጋ የቦን ከተማ ተጎራባቿ ኮልን ከተማ እና ሻልከ በዘንድሮ የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ነጥባቸውን ትናንት አስመዝግበዋል። የስፔን ላሊጋ ባለድል ሪያል ማድሪድ እና ዋነኛ ተፎካካሪው ባርሴሎና ተመሳሳይ ሽንፈት አስተናግደዋል። 

አትሌቲክስ

ፖላንድ ግዲኒያ ከተማ ውስጥ በተከናወነው 24ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር በቡድን የኹለተኛ ደረጃ ይዞ ወደ ሀገር ለተመለሰው ቡድን ሰኞ፤ ጥቅምት 9 ቀን፣ 2013 ዓ.ም አቀባበል ተደረገለት። ቡድኑ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ክብርት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ እና ሌሎች የፌዴሬሽኑ አመራር በስፍራው ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል። ለአትሌቶቹ «ዛሬ ከቀኑ 10:00 ላይ ደግሞ ፌዴሬሽኑ በለገጣፎ ጥሩነሽ ዲባባ ሆቴል የማበረታቻ ሽልማት ሥነስርአት» ለማድረግ ቀጠሮ መያዙን በይፋዊ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ ቀደም ሲል ዐስታውቋል።

Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በግማሽ ማራቶን ፉክክር ከዓለም በአጠቃላይ ውጤት 2ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። በወንዶችም በሴቶችም በቡድን 1 ወርቅ እና 1 ብር እንዲሁም በአምደወርቅ ዋለልኝ እና የዓለምዘርፍ የኋለው የነሐስ ሜዳሊያዎችም መገኘቱን ፌዴሬሽኑ ዘግቧል።  

በሌላ የአትሌቲክስ ዜና፦ ጣልያን በተከሄደ የ10,000 ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሓጎስ ገ/ሕይወት ክብረ ወሰን ሰብሮ በአንደኛነት አጠናቋል። አትሌት ሓጎስ የቦታውን ክብረወሰን አሻሽሎ ያሸነፈው 29.49 በሆነ ጊዜ መኾኑን፤ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አክሎ ጠቅሷል።

እግር ኳስ

በስፔን ላሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያ ሪያል ማድሪድ ከ14 ዓመታት ቆይታ በኋላ ዘንድሮ ወደ ላሊጋው በተመለሰው ካዲዝ ቡድን 1 ለ0 መሸነፉ ብዙዎችን አስደምሟል። የሪያል ማድሪድ ዋነና ተቀናቃኝ ባርሴሎናም በተመሳሳይ የ1 ለ0 ሽንፈት ቅዳሜ ዕለት በጌታፌ ደርሶበታል።  ባርሴሎና ለሻምፒዮንስ ሊግ ነገ ከሐንጋሪው ፌሬንስባሮሽ ቡዳፔስት ቡድን እንዲሁም ሪያል ማድሪድ ከነገ በስትያ ከዩክሬኑ ሻካቶር ዶኒዬትስክ ጋር ይጋጠማሉ።

Fußball Champions League I Juventus vs Olympique Lyonnais
ምስል Imago Images/Gribaudi/ImagePhoto

አራተኛው ዙር የቡንደስሊጋ ግጥሚያ

የሣምንቱ መጨረሻ ከባየር ሙይንሽን ውጪ ብዙ ግብ ያልተቆጠረበት ነበር። አብዛኛዎቹ ቡድኖች አቻ አለያም በጣም በጠበበ የግብ ልዩነት ነው የተለያዩት። ፍራይቡርግ ከብሬመን፤ ቮልፍስቡርግ ከቦሩሽያ ሞይንሽንግላድባኅ፤ ኮሎን ከአይንትራህት ፍራንክፉርት እንዲሁም ሻልከ ከዑኒዮን ቤርሊን በአጠቃላይ አንድ እኩል በኾነ ውጤት ነው ጨዋታቸውን ያጠናቀቊት።

ኮሎን ከአይንትራህት ፍራንክፉርት

ኮልን ትናንት አንድ እኩል ወጥቶ ነጥብ ከመጋራቱ በፊት ለ13 ጊዜያት ማሸነፍ ተስኖት ቆይቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል የኮልን ተከላካይ ሠባስቲያን ቦርኖው ዲያቺ ካማዳ ላይ ጥፋት በመፈጸሙ የቅጣት ምት ተሰጥቷል። ፍጹም ቅጣት ምቱንም አንድሬ ሲልቫ በግሩም ኹኔታ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ይኽ ጥፋት ባይፈጸም ኖሮ ኮልን የመጀመሪያ ድሉን ያስመዘግብ ነበር። ጥፋቱን የፈጸመው ተከላካይ ስለ ጨዋታው ቀጣዩን ብሏል።  

«እንደሚመስለኝ ይኼ ለእኛ ወሳኝ የኾነ ነጥብ ነው። በእርግጥ ለሦስት ነጥብ ነበር ያለምነው፤ ግን ለዚህ ጨዋታ አንድ ነጥብ ምንም አይደለም። ከእረፍት መልስ የመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን የእኛ ምርጡ እንቅስቃሴ የነበረ ይመስለኛል። በሚቀጥሉት ጨዋታዎችም ከመጀመሪያው አንስቶ ልክ እንደዛ ነው መጫወት ያለብን።»

ኮሎን በኦንድሬ ዱዳ ብቸኛ ግብ ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር አቻ በመውጣቱ በዚህ የጨዋታ ዘመን እንደ ሻልከ ኹሉ አንድ ብቸኛ ነጥቡን ማግኘት ችሏል። ባየርን ሌቨርኩሰን ማይንትስን እንዲሁም ቦሩስያ ዶርትሙንድ በመከራ ሆፈንሃይምን ያሸነፉት 1 ለዜሮ ነበር። ላይፕሲሽ አውግስቡርግን፤ ሽቱትጋርት ሔርታ ቤርሊንን 2 ለ0 ማሸነፍ ችለዋል። ሰፊ የግብ ልዩነት የነበረው፦ ባየር ሙይንሽን አርሜኒያ ቢሌፌልድን 4 ለ1 ያሸነፈበት ግጥሚያ ነበር።

አርሜኒያ ቢሌፌልድ ከባየር ሙይንሽን

ቅዳሜ ማታ በተደረገው ግጥሚያ፦የሦስት ዋንጫዎች ባለድሉ ባየር ሙይንሽን ከታችኛው የቡንደስሊጋ ምድብ የመጣው ቢሌፌልድን አንዳችም ዕድል አልሰጠውም። ቶማስ ሙይለር በስምንተኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ የጀመረው ባየርን በሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ኹለት ግቦች (25 እና 45+1) ነበር ረፍት የወጣው። ከረፍት መልስም ሙይንሽኖች ማጥቃታቸው ላይ አልቦዘኑም። 51ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ አመቻችቶለት አራተኛዋን ግብ ቶማስ ሙይለር ሲያስቆጥር ለአርሜኒያ ቢሌፌልዶች ተስፋ አስቆራጭ ነበረች። ግን እልህ እና ወኔ የተሞሉት ቢሌፌልዶች ወደ ባየር ሙይንሽን ግብ ክልል ደርሰው ያገኙት ፍጹም ቅጣት ምትን 59ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ በማሳረፍ በዜሮ ከመውጣት ድነዋል። 76ኛው ደቂቃ ላይ ኮሬንቲን ቶሊሶ ፋቢያን ክሎስ ላይ ጥፋት በመሥራቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ቢሰናበትም በጨዋታው ውጤት ላይ የቀየረው ነገር ግን አልነበረም።

Bundesliga Arminia Bielefeld vs. FC Bayern München
ምስል Sascha Steinbach/Getty Images

የአርሜኒያ ቢሌፌልድ ግብ ጠባቂ ሽቴፋን ኦርቴጋ ግብ ሊኾኑ የሚችሉ ኳሶችን ባያመክን ኖሮ ባየር ሙይንሽን እጅግ በሰፋ የግብ ልዩነት ማሸነፍ በቻለም ነበር።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሆፈንሃይምን

ለቲ ኤስ ጂ ሆፈንሃይም ጨዋታው ከመጀመሩም በፊት አስደሳች አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ ባለፈው የጨዋታ ዘመን፤ በ34ኛው ዙር ግጥሚያ ቦሩስያ ዶርትሙንድን 4 ለ0 ባሸነፉበት ጨዋታ አራቱንም ከመረብ ያሳረፈው አንድሬ ክራማሪች በቅዳሚው ጨዋታ ሊሰለፍ ያለመቻሉ ነበር። አንድሬ ክራማሪች በኮሮና ተሐዋሲ በመጠቃቱ መሰለፍ ባልቻለበት ግጥሚያ፦ 75ኛው ደቂቃ ላይ ጋቺዮኖቪች የግብ ዕድል አምልጦታል። ኧርሊንግ ሃላንድ በ76ኛው ደቂቃ ላይ ለአምበሉ ማርኮ ሮይስ ያሻገረውን ኳስ አምበሉ ከመረብ አሳርፎ በዛችው ግብ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ማሸነፍ ችሏል። በዚያም ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል። ላይፕሲሽ በ10 ነጥብ ደረጃውን ሲመራ፣ ባየር ሙይንሽን እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ በተመሳሳይ 9 ነጥብ ግን በግብ ክፍያ ልዩነት ኹለተኛ እና ሦስተኛ ናቸው።

ሻልከ ከዑኒዮን ቤርሊን

ጎንቻሎ ፓሰንሲያ 69ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተላከውን ኳስ በጭንቅላት ገጭቶ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ሻልከ በጨዋታ ዘመኑ የመጀመሪያ ግቡን ትናንት አስመዝግቦ ከቅዠቱ ለጊዜውም ቢኾን ባኗል። ሻልከ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ብቸኛ ግብ ብቻ ይዞ ያለምንም ነጥብ ነበር ያሳለፈው። በቡንደስሊጋው ታሪክ ለ7 ጊዜያት ዋንጫ ማንሳት ችሎ ለነበረው የንጉሥ ሰማያዊዎቹ የቀድሞ ኃያል ቡድን ሻልከ ተደጋጋሚ ሽንፈት ማስተናገድ የጀመረው ካለፈው ጥር ወር አንስቶ ነው። አሰልጣኝ ማኑዌል ባውም በሜዳቸው አቻ ከወጡ እና ብቸኛዋን ነጥብ ካገኙ በኋላ፦ «አንዲት ትንሽ ርምጃ ብቻ ወደፊት ኼደናል» ብለዋል።

አሰልጣኝ ማኑዌል ባውም ዴቪድ ቫግነር ከተባረሩ በኋላ የመጡ ናቸው። ቡድኑን ቢያንስ ከመውረድ እታደጋለሁ ብለው ቃል ገብተዋል። አሰልጣኝ ዳቪድ ቫግነር በዘንድሮ የቡንደስሊጋ መክፈቻ ጨዋታ ብርቱ በትር የተሰነዘረባቸው በባየር ሙይንሽን ነበር። በዚያ መከረኛ ግጥሚያ ቡድናቸው 8 ግቦችን አስተናግዶ ጎተራ ሲኾን አንድም ግብ ማግባት ተስኗቸው አቅመ ቢስ ኾነው ነው የወጡት። ከዚያ በኋላ ተደጋጋሚ ሽንፈት ገጥሟቸዋል። በብሬመን ከተሸነፉ በኋላ ግን ተሰናብተዋል። በምትካቸውም የቀድሞ የአውግስቡርግ አሰልጣኝ ነው የመጡት።

Deutschland Bundesliga FC Schalke 04 gegen Union Berlin  | Tor Schalke
ምስል REUTERS

አዲሱ አሰልጣኝ የተሰጣቸው ኃላፊነት ያንድ ዘመን ገናና የነበረውን ቡድን ከመውረድ ታድገው 15ኛ ደረጃ ይዞ እንዲጨርስ ማስቻል ነው። የቀድሞው አሰልጣኝ ዴቪድ ቫግነር የወደፊት እጣ ፈንታ በውል ባይለይም፤ አዲሱ አሰልጣኝ ማኑዌል ባውም ትናንት ቡድናቸውን አንድ ነጥብ አስይዘዋል። ለሻልከ ምናልባትም ከወራጅ ቃጣናውም በላይ ኾኖ ለመጨረስ እንደሚችል አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። አሰልጣኙ የትናንቱ ግጥሚያ ወደፊት ለሚመሠርቱት ቡድን የበለጠ ግንዛቤ ያስጨበጣቸው እንደኾነም ጠቅሰዋል።

«በዚህም አለ በዚያ ስኬታማ ግጥሚያ ነበር። ኪሎ ሜትር አዳርሰናል። ሜዳው ላይ ፈጣን እንቅስቃሴ አድርገናል። ከአጨዋወት አንጻር ግን የምር የመሻሻል አቅም አለን።»

በእርግጥ አሰልጣኝ ማኑዌል ባውም የሻልከ አሰልጣኝነትን በያዙ በሦስተኛ ቀናቸው ከላይፕሲሽ ጋር ተጋጥመው ቡድናቸውን ከ4 ለ0 ሽንፈት መታደግ አልቻሉም።

አሰልጣኙ ሻልከን እንደያዙ ከወሰዷቸው ርምጃዎች ረዳታቸውን የመምረጣቸውም ነገር ይነሳል። በሻልከ ቡድን ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ተጨዋቾች አሰልጣኝ የኾኑት ዖኑር ቺኔልን ረዳታቸው አድርገው መምረጣቸውን ይፋ ማድረጋቸው በርካቶችን አስገርሟል። «ለእኔ ታዳጊዎች በጣም ወሳኝ ናቸው» ሲሉም በታዳጊ ተጨዋቾች ላይ ያሳደሩትን እምነት ዐሳይተዋል። «እዚህ በርካታ ተስፋ የሚጣልባቸው ታዳጊ ተጨዋቾችች ይታዩኛል» ሲሉም አክለዋል።

ከዚሁ ከሻልከ ቡድን ጉዳይ ሳንወጣ፦ ዕድሜያቸው ከ19 ዓመት በታች የሻልከእና የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጨዋቾች ባደረጉት ግጥሚያ የቡድኑ ደጋፊዎች የዶርትሙንዱ ታዳጊ ዩሶፋ ሞውኮኮ ላይ የዘረኝነት ስድብ ናዳ በማውረዳቸው ሻልከ በይፋ ይቅርታ ጠይቋል። የካሜሩን ተወላጁ የ15 ዓመቱ አጥቂ ትናንት ሻልከን 3 ለ2 ሲያሸንፉ ሦስቱንም ግቦች ከመረብ ካሳረፈ በኋላ ደስታውን ሲገልጥ ተሳዳቢዎቹን ከመጤፍም አልቆጠራቸውም። ሻልከ ትዊተር ገጹ ላይ፦ «ዕድሜያቸው ከ19 ዓመት በታች ባደረጉት ግጥሚያ ዩሶፉ ሞውኮኮ ላይ ደጋፊዎች በመጮኻቸው ይቅርታ ብቻ ማለት እንችላለን» ብሏል። ዩሶፋ ሞውኮኮ በቡንደስሊጋው ወደፊት ተስፋ ከተጣለባቸው ጥቂት ተጨዋቾች አንዱ ነው። ከአንድ ወር በኋላ 16 ዓመቱን ስለሚደፍንም በቡንደስሊጋው መጫወት ይፈቀድለታል።

U19 Bundesliga |  FC Schalke 04 v Borussia Dortmund -  Youssoufa Moukoko
ምስል Maik H./Team2/Imago Images

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ መሪው ኤቨርተን ከሊቨርፑል ጋር ቅዳሜ ዕለት ባደረገው ግጥሚያ የጉልበት ጉዳት የደረሰበት ዋናው ተከላካይ ቪርጂል ቫንጃይክ ከጉዳቱ ለማገገም ወራት ሊቆጠር ይችላል መባሉ ለሊቨርፑል የራስ ምታት ኾኗል። ቫንጃይክ ሊቨርሉል ባለፈው የጨዋታ ዘመን የፕሬሚየር ሊጉንም ኾነ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን በእጁ እስካስገባበት ጊዜ ድረስ አንድም ጊዜ ከሜዳ ርቆ የማያውቅ ወሳኝ ተጨዋቹ ነው። በሳዲዮ ማኔ ፈጣን ግብ እና በሞሀመድ ሳላህ ኹለተኛ ግብ ሲመራ የቆየው ሊቨርፑል የማታ ማታ በ81ኛው ደቂቃ በዶሚኒክ ካልቬርት ሌዊን በተቆጠረበት ግብ ነጥብ ለመጋራት ተገዷል። ማንቸስተር ዩናይትድ በድንቅ አጨዋወት ኒውካስል ዪናይትድን 4 ለ1 አደባይቷል። ማንቸስተር ሲቲ አርሰናልን 1 ለ0 ሲያሸንፍ፤ ቸልሲ ከሳውዝሀምፕተን 3 እኩል ተለያይቷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ