1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኪነ ጥበብ

የጀግና ሴቶች ተከታታይ ፊልም እየተሰናዳ ነው

ዓርብ፣ ሚያዝያ 27 2009

በኢትዮጵያ በተለይ ከከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ለሚኖሩ ልጃገረዶች ህይወት ቀላል አይደለም፡፡ አሁንም ዘረፈ ብዙ ችግሮችን ይጋፈጣሉ፡፡ «ጸሐይ መማር ትወዳለች» በተሰኘው የቴሌቪዥን መሰናዶአቸው የሚታወቁት አዘጋጆች በአዳጊ ሴቶች ችግሮች ላይ የሚያጠነጥኑ የአኒሜሽን ተከታታይ ፊልሞች እና መጽሐፍትን እያሰናዱ ይገኛሉ፡፡

https://p.dw.com/p/2cV2g
[No title]

የ«ጥበብ ልጆች» እየመጡ ነው

ሦስት ጥበብ ለባሾች፡፡ ፍቅር፣ ትግስት እና ፍትህ፡፡ ፍቅር ከፍተኛ የሆነ ፍጥነትና ጥንካሬ አላት፡፡ ትግስት ትንቢተኛዋ ሴት ናት፡፡ የወደፊቱን የማየት ችሎታ ተችራለች፡፡ ፍትህ ደግሞ ውስጥ አዋቂዋ ይሏታል፡፡ በከፍተኛ ኃይል የሌሎችን ስሜት እና ችግር ማየት ትችላለች፡፡ «እነዚህ ሦስት ሴቶች አንድ ላይ ሲመጡ ኃይላቸው እጥፍ ድርብ በመሆን ማንም ሊያስቆማቸው አይችልም፡፡» በአንድ የቆሙቱ እነዚህ ሴቶች «የጥበብ ልጆች» በሚል ስያሜ ይታወቃሉ፡፡ በዚሁ ስያሜ የሚጠራ ተከታታይ የ«አኒሜሽን» ፊልም ገጸ- ባህሪያት ናቸው፡፡

አሰያየማቸው ድርብ ትርጉም አለው፡፡ አንድም በፊልሙ ላይ የሚለብሷቸው ልብሶች የሀገር ባህል የጥበብ ቀሚሶች በመሆናቸው ሁለትም የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ጥበባቸውን ስለሚጠቀሙ ነው፡፡ ኢ-ፍትሐዊነት እና ጎጂ ልማዶችን ለመዋጋት ታጥቀው የተነሱት እነዚህ ሴቶች ገሚስ ፊታቸውን በጭምብል ሸፍነው ችግር የተከሰተበት ቦታ ከተፍ ይላሉ፡፡ 

የጥበብ ለባሾቹ፣ የጥበብ ልጆቹ ፈጣሪ ብሩክታዊት ጥጋቡ ነች፡፡ ዊዝ ኪድስ ወርክሾፕ የተሰኘው ድርጅት አጋር መስራች ስትሆን ድርጅቱን በስራ አስኪያጅነት ትመራለች፡፡ የቴሌቪዥን ዝግጅት ተከታታዮች በድምጽ ያውቋታል፡፡ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በአሁን ስሙ ደግሞ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሚተላለፈው «ጸሐይ መማር ትወዳለች» የሕጻናት ዝግጅት ላይ የጸሐይንም እና የእናቷንም ሚና ደርባ ትጫወታለች፡፡ ድርጅቷ ከዚህ ዝግጅት በተጨማሪ «ትንሾቹ መርማሪዎች» እና «አሳትፉኝ» የተሰኙ መሰናዶዎችንም በማቅረብ ይታወቃል፡፡ 

Bruktawit Tigabu  Addis Ababa, Ethiopia
ምስል Bruktawit Tigabu

«የጥበብ ልጆችን» የመስራት ሀሳብም የመጣው «አሳትፉኝ» የተሰኘውን እና ልጆች ራሳቸውን በአንድ ደቂቃ ፊልም እንዲገልጹ የሚያደርገውን ዝግጅት ለመስራት ወላይታ ሶዶ በቆየችበት ወቅት ነበር፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ከተለያዩ የወላይታ ወረዳዎች የተውጣጡ 12 ልጆችን የማሰልጠን ዕድል ታገኛለች፡፡ ስልጠናው ልጆች በራሳቸው እንዲተማመኑ እና ብቁ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነበር፡፡ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ከምታሰለጥናቸው ልጆች መካከል አንዷ ያለዕድሜዋ ልትዳር እንደሆነ ትሰማለች፡፡ 

«ልክ የመጨረሻ ጊዜ አካባቢ ላይ ʻአንቺ እስካሁን ትነግሪናለሽ፡፡ በራሳችን እንድንተማመን፣ ሀሳባችንን እንደንገልጽ፣ ጠንካራ እንድንሆን ትነግሪናለሽ፡፡ ለምሳሌ ከመሃላችን እንዲህ አይነት ችግር አለ፡፡ እንዴት ነው የምንፈታው? እንዴት ነው ለሌሎች የምንቆመው?ʼ ብለው ሦስት ልጆች መጥተው ፈታኝ ጥያቄ ጠየቁኝ፡፡ አሁን እንደምነግርህ ቀላል አይደለም፡፡ በጣም ስሜታዊ የሚያደርግ ነበር፡፡ ምክንያቱም ልጅቷ የ13 ዓመት ልጅ ነች፡፡ በዚያ ዕድሜ ከትምህርት ተፈናቅሎ ለትዳር መታሰብ ይሄ አሁን በጽሁፍ፣ በጥናት የምናነበው ብቻ ሳይሆን በቃ የቀንተቀን አጋጣሚ እንደሆነ የሚያሳይ ነገር ነበርና ለእኔ እንደመነሻ ነው የሆኑት» ትላለች ብሩክታዊት የ«ጥበብ ልጆች» ዝግጅትን ለመጀመር ምክንያት የሆናትን ገጠመኝ መለስ ብላ ስታስታውስ፡፡ 

ብሩክታዊት የአዳጊዋን ልጅ ሁኔታ ሰምታ እና አዝና ብቻ አልተቀመጠችም፡፡ ከመጣችበት ማኅብረሰብ ጋር በመነጋገር ልጅቷ ወደ ትምህርት ገበታዋ እንድትመለስ አድርጋለች፡፡ ጉዳዩን ያሳወቋትን እነዚያን ሦስት የስልጠናዋ ታሳታፊዎችንም አልረሳቻቸውም፡፡ የ«ጥበብ ልጆቹ» ፍቅር፣ ትግስት እና ፍትህ የተወለዱት በእነርሱ አምሳያ ነው፡፡  

«እነዚያ ሶስት ልጆች ለእኔ እውነተኛ ጀግኖች ነበሩ፡፡ በታሪክ ጀግኖችን በተለያዩ ስራዎች እናውቃለን፡፡ ግን በአጠገባችን የምናየውን ማንኛውም ፍትሃዊ ያልሆነ ነገርን የሚቋቋምም ጀግና ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሴት ልጆች እንደዚህ አይነት ዝግጅት ብሰራ የምለውን የግድ እንደሆነ ነው ያረጋገጡልች» ትላለች ብሩክታዊት፡፡

Tibeb Girls  Addis Ababa, Ethiopia
ምስል Bruktawit Tigabu

የ«ጥበብ ልጆች»ን እንደዚህ የጠነሰሰችው ብሩክታዊት ቀጣይ ትኩረቷ «በምን መልኩ ቢቀርብ ከ10 እስከ 15 ዓመት ያሉ ልጆችን ቀልብ ሊስብ ይችላል?» የሚል ሆነ፡፡ «በዚህ የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ልጆች ምን አይነት ነገሮች ይወዳሉ? ስለሚለው የተለያዩ ጥናቶች አሉ፡፡ በእኛ ማህበረሰብ በተለይ በአኒሜሽን ለዚህ የዕድሜ ክልል የተሰራ ነገር አልነበረምና በትክክል መስራቱን እርግጠኛ አልነበርኩም፡፡ ያው መሞከር ነበረብኝ፡፡ ልጆቹን ባማከለ ሁኔታ ነው የተቀረጸው ይሄ ዝግጅት፡፡ ስለዚህ ከጽሁፉ፣ ከንድፉ፣ ከሥዕሉ በዚህ ከ10 እስከ 15 የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ሴት እና ወንድ ልጆች እያማከረን ነው የቀረጽነው» ትላለች ከዝግጅቱ አፈጣጠር ጀርባ የነበረውን ሂደት ስትተርክ፡፡  

የምትፈልገውን መልዕክት በአኒሜሽን ለማስተላለፍ ስትነሳ እንደዚህ አይነት ፊልሞች በኢትዮጵያውያን አዳጊ ልጆች ዘንድ ተወዳጅ መሆናቸውን ታሳቢ አድርጋ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሳተላይት ዲሽ በትንንሽ ከተማዎች እና የገጠር አካባቢዎች ሳይቀር መስፋፋት ልጆች በአረብ ሳት እና ናይል ሳት የሚተላለፉ የካርቱን እና አኒሜሽን ፊልሞችን በቀላሉ እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ 

ወላጆች እንዲህ አይነት ፊልሞችን በቪሲዲ እና ዲቪዲ በርካሽ እንደ ልብ ማግኘታቸውም ሌላ ምክንያት ነው፡፡ ልጆቻቸው ለአዋቂዎች የተሰሩ ፊልሞችን አለዕድሜያቸው እያዩ «አጓጉል ነገሮችን» ከሚማሩ በሚል በ«ፍላሽ ዲስክ» ሳይቀር እንደዚህ አይነት ፊልሞችን እየገለበጡ እንዲያመጡ አድርጓቸዋል፡፡ ፊልሞቹ ሕጻናትን እና አዳጊዎችን ቋንቋ ለማስተማር ይጠቅማል በሚል ለልጆቻቸው በገፍ የሚያቀርቡ ወላጆችም አሉ፡፡ 

ይህ ግን የራሱን ችግሮች ይዞ መምጣቱ አልቀረም፡፡ በተለይ በከተማ አካባቢ ያሉ ልጆች ለ«ጀግና» ያላቸው ምስል እንደ «ስፓይደር ማን» ካሉ የፊልም ገጸ-ባህሪያት ጋር የተጣበቀ መሆኑ የተለመደ ሆኗል፡፡ ተዋናይ፣ አዘጋጅ እና የፊልም ባለሙያው ሚካኤል ሚሊዮን ይህ በአካል ገጥሞታል፡፡ የአድዋ ድልን ምክንያት በማድረግ ሰውኛ ፕሮዳክሽን እና ኢንተርቴይመንት በተሰኘው ድርጅቱ አማካኝነት ተማሪዎችን ሰብስቦ ለ10 ቀን የቆየ አውደ ጥናት (ወርክሾፕ) ሲሰጥ የታዘበውን እንዲህ ያጋራል፡፡ 

Bruktawit Tigabu  Addis Ababa, Ethiopia
ምስል Bruktawit Tigabu

«ከአራት እስከ 13 ዓመት ያሉ ተማሪዎችን ሰብስበን እነዚህ ልጆች ጀግናቸው ማነው? ብለን ለመገምገም ያደረግነው ነው፡፡ ምን እንደሰራንባቸው እንድናወቅ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ 10 የካርቱን ጀግናዎቻቸውን እና 10 ደግሞ የምናውቃቸውን እነ አጼ ቴዎድሮስን፣ እነ አጼ ምኒልክን፣ እነ አጼ ዩሃንስን እንዲሁም ደግሞ የተለያዩ ጀግናዎችን አንድ ላይ ሞልተን ጎን ለጎን እንዲመርጡ አደርግናቸው ማለት ነው፡፡ ከዚያ ሲመርጡ ትልልቆቹ ሁኔታችን ገብቷቸው ይመስለኛል መጀመሪያ ከመምረጣቸው በስተቀር አብዛኞቹ ወደ 86 በመቶዎቹ  እነ ስፓይደር ማን፣ እነ አይረን ማን፣ እነ ሱፐር ውመን የተለያዩ የሆሊውድ የካርቱን ጀግኖችን ጀግናዬ ብለው ነው የመረጡት» ይላል፡፡ 

ሚካኤል በአውደ ጥናቱ  መገባደጃ ላይ በተደረገ ምርጫ ወደ 70 በመቶው የሆኑት አዳጊዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ኢትዮጵያውያን ጀግኖችን መምረጣቸውን በስኬት ያነሳል፡፡ ብሩክታዊትም የ«ጥበብ ልጆች» ኢትዮጵያዊ፣ አፍሪካዊ ሊያውም በእንደዚህ አይነት ፊልሞች እምብዛም ባልተለመደ መልኩ ሴት ጀግኖችን በአዳጊዎች አመለካከት ውስጥ ለማስረጽ ሆን ተብሎ እንደተወጠነ ታስረዳለች፡፡ በጀግኖቹ አማካኝነት ደግሞ የምትፈልገውን መልዕክት ታስተላልፋለች፡፡  

«እኛ የምናነሳቸው ሃሳቦች ከልጆች ከ10 ዓመት አይነቶች ጋር ቁጭ ብሎ ለመነጋገር የሚከብዱ ርዕሰ ጉዳይ ናቸው፡፡ አላቻ ጋብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለ ግርዛት ሊሆን ይችላል፡፡ በቃ አሁን ህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ አንገብጋቢ ችግሮች ግን ልጆች ላይ እየደረሱ ያሉ ናቸው፡፡ ልጆች ቁጭ ብለን የማናነጋገራቸው ስለ ጉርምስና ወይም ኩርድና፣ የሰውነት ለውጥ መምጣት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ከ10 እስከ 15 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ብዙ ለውጥ፣ ብዙ ፈተናዎች የሚያዩበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ድርቅ ባለ መልኩ ሳይሆን በሚወዱት፣ ሊያፈቅሩት፣ ጓጉተው ሊያዩት በሚችሉት መልኩ እነዚህን የማህበራዊ ጉዳዩች የምናስተምራቸው እንደገና እነርሱም ለዋጭ ሆነው የተዘጋጁ ዜጋዎች የምናደርጋቸው እንዴት ነው ከሚለው አንጻር ይሄ አንሜሽን ቢሰራስ በሚል ነው» ስትል ከ«ጥበብ ልጆች» ጀርባ ያለውን ዋና አላማ ታብራራለች፡፡     

Tibeb Girls  Addis Ababa, Ethiopia
ምስል Bruktawit Tigabu

ብሩክታዊት ህልሟን ወደ ተግባር ለመቀየር ብዙ ርቀት ተጉዛለች፡፡ የ«ጥበብ ልጆች» ለተከታታተይ ሦስት ዓመታት ምን ዓይነት ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳሉ?፣ ምንስ ዓይነት የአመለካከት ለውጥ በእነርሱ ማምጣት ይፈለጋል?፣ እንዲተላለፉ የሚፈለጉ የዕውቀት እና የክህሎት ሃሳቦችስ ምንድናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች የሚመልስ መርሃ ግብር መንደፋቸውን ትናገራለች፡፡ በመጀመሪያው ዓመት የሚተላለፈው ዝግጅት የታሪክ አካሄድ ተሰርቶ መጠናቀቁን ትገልጻለች፡፡

ገጸ-ባህሪያቱ ዙሪያ መለስ ካሉ ሌሎች ደጋፊዎቻቸው ጋር ተስለው ወደ አኒሜሽን ለመተርጎም መዘጋጀታቸውንም ታብራራለች፡፡ ለሙከራም የመጀመሪያውን ክፍል ሰርተው በገጠር ላሉ ልጆች ጭምር በማሳየት ጥሩ ምላሽ እንዳገኙ ታስረዳለች፡፡ የ«ጥበብ ልጆች»ን በትምህርት ቤት አስተማሪዎች፣ በቤት ውስጥ ወላጆች እንደ አጋዥ መሳሪያ መጠቀም የሚችሉበትን መመሪያ ማውጣታቸውንም ትገልጻለች፡፡ ይህን ሁሉ ሰርታ አሁንም ግን የገንዘብ ጉዳይ ቀይዶ ይዟታል፡፡ 

«ይሄ ዝግጅት ቢያንስ ለሁለት ወይም ለሶስት ዓመት በቀጣይነት መሄድ ይኖርበታል፡፡ ከዚያ በኋላ ራሱን እንዲችል የሚያደርግ አካሄድ ነው የቀረጽነው፡፡ ምክንያቱም ይሄ ዝግጅት አኒሜሽን ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው አፍሪካ ሀገር በአፍሪካውያን የተሰሩ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የልጆች ዝግጅቶች እጥረትም ስላለ፣ የምናነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ከኢትዮጵያም ድንበር ዘለል እና የጋራ የሆኑ ችግሮች ስለሆኑ ወደፊት የተለያዩ ጣቢያዎች በፍቃድ እየወሰዱ የሚያስተላልፉት ዝግጅት ስለሚሆን ራሱን በገንዘብ የሚችል ይሆናል» ስትል ብሩክታዊት ተስፋዋን ታጋራለች፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ 

ሸዋዬ ለገሠ