1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥናታዊ ፅሁፎች እጥረት

ዓርብ፣ ጥር 16 2006

በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ላይ የሚዘግበው «ሴቴ» የተሰኘው ታዋቂ የጀርመን መፅሄት ሰሞኑን አንድ ፁሁፍ ለአንባቢዎቹ አቅርቧል። ይህም ጥናታዊ ፁሁፎች በቀላሉ ለኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማት እንደማይደርሱ ያመላክታል። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ምንስ መፍትሄ ሊሆን ይችላል?

https://p.dw.com/p/1AwKX
Wintersemester startet in Brandenburg
ምስል picture-alliance/dpa

ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ዎልፍጋንግ ቲትሮፍ የመቀሌ ዮንቨርሲቲ ዲን ናቸው። ወደ መቀሌ የተጓዙት በዓለም ባንክ ፕሮጀክት አማካኝነት እንደሆነ ይናገራሉ። የስራውን ኃላፊነት የያዘው የጀርመን የአካደሚ ልውውጥ አገልግሎት ተቋም በምህፃሩ DAAD ሲሆን ተቋሙ በተለይ በምህንድስና እና በሳይንሱ ዘርፍ ምሁራንን ወደ ተለያዩ ዮንቨርሲቲዎች በመላክ ያለውን የትምህርት ልውውጥ እድገት ለማፋጠን ይጥራል። የሳይንስ ተቋም ዲን የሆኑት ቲትሮፍ በመቀሌ ዮንቨርሲቲ ለአንድ አመት ፣ በአለማያ ዮንቨርሲቲ ደግሞ ለ3 ዓመት አገልግለዋል። እሳቸው እንደሚሉት የእውቀት ሽግግሩን ለማድረግ ከፍተኛ ችግር አለ።

« እዚህ በርካታ ችግሮች ነው ያሉት። የቤተ ሙከራ መሳሪያዎችን ከማስፋፋት አንስቶ እስከ እውቀት መቅሰሚያ መገገዶች ይደርሳል። ለቤተ ሙከራ የሚያስፈልጉ አንዳንድ መሳሪያዎችንስ ቀስ በቀስ ማሟላት ይቻላል፤ እውቀት መቅሰሚያ መንገዱ ላይ ግን ብዙ መሰናክሎች አሉ። እስካሁንም ሳይንሳዊ የጥናት ፁሁፎችን ልናገኝ የቻልነው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድረ ገፅ አማካኝነት ነው። የተወሰኑ ፕሮግራሞች አሏቸው ችግሩ ግን እስከ 2015 ዓም ነው የሚዘልቀው። ከዛ በኋላ እንዴት እንደሚቀጥል ማንም አያውቅም። »

E-Learning
የርቀት ትምህርት ፕሮግራም በኬንያምስል GIZ/Dirk Ostermeier

ሌላው ችግር አብዛኛው የጥናት ፁሁፎች በግል ማሳተሚያ ቤቶች እጅ መሆናቸው እና ክፍያ መጠየቃቸው ነው ይላሉ ፕሮፌሰሩ። አዳጊ ሀገር ለሚገኙ የትምህርት ተቋማት ፍፁም ለመክፈል የሚዳግት። « «ኔቸር» የተሰኘውን መፅሄት በምሳሌነት ብንወስድ በዓመት ባለ አምስት አሀዝ ዶላር ነው የሚጠይቀው። ይህ እስከ ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል። ምክንያቱ አንድ ትልቅ የዮንቨርሲቲ ቤተ መፅሀፍት ብዙ ሺ መፅሄቶችን ሊይዝ ይችላል። ብሪታንያ የሚገኙ ቤተ መፅሀፍት ለምሳሌ እስከ 200 ሚሊዮን ዮሮ የሚደርስ ገንዘብ ነው ለጥናታዊ ፁሁፎች ብቻ የሚያወጡት።»ይህን ችግር ለመፍታት ከጀርመን እና ከሌሎች ሀገራት ጋ በጋሪዮሽ የምንሰራበትን መንገድ እየሞከርን ነው። ይሁንና ገና ጅማሬ ላይ ነው ያለነው ይላሉ ፕሮፌሰር ቲትሮፍ።

Hauptcampus der Universität Addis Abeba AAU
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዮንቨርሲቲምስል DW

ተማሪዎች እና አስተማሪዎች እንደ አማራጭ የሚጠቀሙት እና ያለ ክፍያ አንዳንድ ጥናቶች፣ መዘርዝሮች እና የትምህርት መፅሀፍትን ለማግኘት የሚረዳው ኢንተርኔት ነው። ቢሆንም ግን ኢንተርኔት ማግኘቱ ብቻ በቂ አለመሆኑን ነው ፕሮፌሰሩ የሚያስረዱት።« ኢንተርኔት ተማሪዎች በርካታ መረጃዎቹን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ችግሩ ግን ሁሉም በጅምላ ታጭቀው ያሉ መረጃዎች ስለሆኑ ተማሪዎቻችን የትኞቹ ትክክለኛ እና የትኞቹ ጠቃሚ ያልሆኑ እንደሆነ ለይቶ ለማወቅ ያዳግታል። ይህ ደግሞ ለኛ ሌላ ትልቅ ፈተና ነው። ስለዚህ ለተማሪዎቹም ይሁን ለአስተማሪዎች አንድ ጥሩ ጥናታዊ ፁሁፍ ምን እንደሚመስል ማስረዳት አለብን። ይህ ደግሞ እጅግ ከባድ እየሆነ መጥቷል። »

በአዲስ አበባ የሚኖረው እና በቅርቡ በርቀት ትምህርት በድህረ ምረቃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው አብነት ጥናታዊ ፁሁም የማግኘቱ ሁኔታ በከፊልም ቢሆን የተሟላ ነበር ይላል። በሌላ በኩል ወጣት ታጠቅ በአሁኑ ሰዓት በጀርመን ዮንቨርሲቲ የኤልክትሪካል ምህንድስና ተማሪ ነው። እንዲሁም በሌላ የምህንድስና ዘርፍም 2ኛ ዲግሪ አለው። በጀርመን ሀገር ትምህርቱን ሲከታተል የሚፈልገውን ጥናታዊ ፁሁፎች አግኝቶ መማር አልዳገተውም።

ፕሮፌሰር ዎልፍጋንግ ፒትሮፍም እንደገለፁልን የጥናት ፁሁፎችን ለተማሪዎች እና አስተማሪዎች ለማድረስ ያለው መንገድ ውስን ነው። ታድያ በምን መንገድ አዲስ የሚወጡ የቴክኖሎጂ እና የሳይንስ ጥናቶችን ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማድረስ ይቻላል? ወጣት ታጠቅ በግሉ አማራጭ ሊሆን ይችላል የሚለውን አካፍሎናል።

አዳዲስ ሳይንሳዊ እና የቴክኖሎጂ ጥናታዊ ፁሁፎች ለኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማት በቀላሉ የማይደርሱበትን ምክንያት እና ምን መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል፤ በወጣቶች ዓለም ዝግጅት ዳሰናል። ሙሉ ዝግጅቱን ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ