1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥንታዊ ሥነ-ጽሑፍ ቅርስ ጥበቃ

ሐሙስ፣ ሰኔ 12 2006

በመስጊዶች እና ቤተክርስትያን ዉስጥ የሚገኙ ጥንታዊ የሥነ-ጽሑፎች አብያተ-መጻሕፍት፤ የአንድ ሀገር፤ አህጉር ብሎም የሰዉን ልጅ የእድገት ታሪክ ያዘሉ በመሆናቸዉ እንክብካቤ እና ልዩ ጥበቃ ሊደረግላቸዉ ይገባል።

https://p.dw.com/p/1CLNm
Bildergalerie Timbuktu Restauration jahrhundertealter Manuskripte
ምስል CSMC

«የበረሀዋ ዕንቁ» በመባልም ወደ ምትታወቀዉ ወደ ምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ማሊ፤ ቲምቡክቱ ከተማ፤ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በቅርስነት እጎአ 1988 ተመዝግባለች። በውስጧ ያሉት ጥንታዊ መስጊዶች እና አብያተ-መፅሐፍት ስለ ቲምቡክቱ ታሪካዊነት እና ጥንታዊነትም ይመሰክራሉ። ይህም ስፍራ የአገር ጎብኝዎች መስብ ነበር። ግን በሰሜናዊ ማሊ የሚንቀሳቀሰዉ አክራሪዉ እስላማዊ ቡድን ፍላጎት፤ ጥንታዊትዋን የምራዕራብ አፍሪቃ የባሕል እና የቅርስ ማዕከል ቲምቡክቱን፤ ማጥፋት ነዉ። በሰሜናዊ ማሊ የሚገኙና በዘመናት የሚቆጠር እድሜ ያላቸዉን ጥንታዊና ታሪካዊ የሥነ- ጽሑፍ ቅርሶች በአብዛኛዉ፤ ይዞታቸዉ በከባድ ሁኔታ የተበላሸ ነዉ። እነዚህ ቅርሶች ታሪካዊ መረጃቸዉ በጽንፈኛዉ ቡድን ጥቃት ቸርሶ እንዳይጠፋ፤ ነዋሪዎች ከከተማዋ በድብቅና በፈቃደኝነት ወደ ማሊ መዲና ባማኮ እያሸሹ ይገኛሉ። እነዚህ በድብቅ ባማኮ ከተማ ላይ በድብቅ የደረሱት ጥንታዊ ሥነ- ጽሑፎች፤ ታሪካዊነታቸዉ ተጠብቆ ለትዉልድ እንዲሻገር፤ ከጀርመን ሃንቡርግ ዩንቨርስቲ በመጡ ምሁራን፤ እየታደሱ ቅርስነታቸዉ ተጠብቆ እንዲቆይ እየተደረገ ነዉ።
ኤቫ ብሮዞቭስኪ ወደ ማሊ መዲና ባማኮ ለማቅናት ዝግጅት ላይ ናቸዉ። ጥንታዊ የሥነ- ጽሑፍ እቅርሶች ጥንታዊ ይዞታቸዉ በማስጠበቅ ሞያና የጥንታዊ የእጅ ሥነ-ፅሁፎች አዋቂ የሆኑት የ 34 ዓመትዋ ጀርመናዊት ኤቫ ብሮዞቭስኪ፤ ዋና ሥራቸዉን በማሊ ባማኮ ከተማ ካደረጉ አንድ ዓመትን አስቆጠሩ። ኤቫ ብሮዞቭስኪ በሰሜናዊ ማሊ ቲምቡክቱ ቤተ- መፃሕፍት ይገኝ የነበረዉንና በዘመናት የሚቆጠር እድሜ ያለዉን የሥነ-ጽሁፍ ቅርስ ለትዉልድ እንዲቆይ በማደስና ይዘታቸዉ እዲጠበቅ እያደረገ ካለዉ አንድ ጀርመን ቡድን አባልም ናቸዉ።

በምዕራባዊትዋ አፍሪቃዊት ሀገር ማሊ የሚገኙት ጥንታዊ እጅ ሥነ-ጽሁፎች፤ በምዕራብ አፍሪቃ እጅግ ትልቅና ዋንኛ የታሪክ ማህደር በመሆናቸዉ፤ ከጎርጎረሳዊዉ 1988 ዓ,ም ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት «UNESCO»በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል። ከማሊ መዲና 1000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዉ የሰሜናዊትዋ ማሊ ቲምቡክቱ ከተማ፤ በመካከለኛዉ ክፍለ ዘመን ሙሰሊም ሱልጣኔቶች ማዕከልም ነበረች። በቲምቡክቱ ከተማ የተገኘዉ እና እስከ 1200 ዓመት እድሜ እንዳለዉ የሚነገረዉ የሥነ- ጽሑፍ ቅርስ፤ በጥንት ዘመን የነበረዉን የተፈጥሮ ፍልስፍና፤ የከዋክብት ቆጠራ ምርምር እንዲሁም የሕክምና ጉዳዮችን፤ እና የቁራንን ፍች ወይም ታሪኩን የሚዘረዝሩ ጽሁፎችን ያካተተ ነዉ።
በቲምቡክቱ ቤተ- መጻሕፍት የሚገኙት ሥነ-ፅሁፍች ጀርመን ቤተ-መጻሕፍት ዉስጥ ከሚገኙትና በዝርዝር መረጃዎችን ከሚሰጡት መጻሕፍት ጋር ሲወዳደር፤ የቲምቡክቱ ሥነ-ጽሑፎች ወደር የማይገኝላቸዉ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸዉ የቅርስ ይዞታ ናቸዉ ሲሉ የሚገልፁት የ 34 ዓመትዋ የጥንታዊ ሥነ-ጽሁፍ ጥበቃ ጉዳይ አዋቂ ኤቫ ብሩዞቭስኪ በኩራት ይናገራሉ።
የቲምቡክቱን ጥንታዊ የሥነ-ፅሁፍ ቅርሶች አሰባስቦ መዲና ባማኮ ላይ በአንድ ማዕከል ዉስጥ በዘመናዊ ዲጂታል መዝገብ በማስቀመጥ፤ የማሊ እና የዓለማቀፍ ተመራማሪዎች ሥነ- ጽሑፉን ለምርምር ሥራቸዉ እንዲጠቀሙበት ቀላል መንገድን እንዲያገኙ እቅድ ተይዞአል። እንደ የጥንታዊ ሥነ-ጽሑፎች ጉዳይ አዋቂዋ እንደደ ኤቫ ብሮዞቭስኪ እስካሁን እስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ጥንታዊ ሥነ -ጹሑፍ ከቲምቡክቱ ወደ ባማኮ ተዛዉረዋል፤
« ከ 280 እስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርስ ጥንታዊ ሥነ-ጽሑፎች ይገኛሉ። ሁሉም ሥነ-ጽሑፍ እድሳት የሚፈልግ አይደለም። ጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኙ ጥንታዊ ሥነ-ጽሑፎችም አሉ። እንድያም ሆኖ ወደ ባማኮ ከተዛወሩት ሥነ-ጽሑፎች መካከል፤ ገሚስ ያህሉ እጅግ የተበላሹ በመሆናቸዉ፤ እድሜ እንዲኖራቸዉ በዲጂታል መዝገብ እንዲሰፍሩ፤ ጥበቃ እና እድሳትን ይሻሉ»
በቲምቡክቱ በሚታየዉ እጅግ ደረቅና በረሃማ የአየር ሁኔታ ምክንያት ጥንታዊ ሥነ-ፅሁፎቹ ያረፈባቸዉ አብዛኞቹ ወረቀቶች ደርቀዉ መሰባበር እና መቆራረጥ ጀምረዋል። በሌላ በኩል ብልና ሌሎች ነፍሳቶች ወረቀቶችን እየበበሉ ቅርስነቱን እያሳጡት ነዉ። ወረቀቱ ላይ የተፃፉባቸዉ ቀለሞችም ቢሆኑ፤ በያዙዋቸዉ አሲዳማ ንጥረ ነገሮች ምክንያት የተበላሹ በርካታ ጽሑፎችም እንዳሉ ተመልክቶአል። አንድ ግዜ በብል የተበሉና የጠፉ ሥነ-ጽሑፎችን መልሶ ማግኘት ስለማይቻል፤ ጥንታዊ ሥነ- ጽሑፎቹ እንዲጠበቁ እና ለትዉልድ እንዲተላለፉ ለጥበቃ ሥራዉ፤ በቂ ገንዘብ መመደብ አለበት ሲሉ ኤቫ ብሮዞቭስኪ ለዓለም መድረክ ማስጠንቅያቸዉን ያስተላልፋሉ፤
« በአሁኑ ሰዓት ጥንታዊ ሥነ-ጽሑፎችን የመጠበቁ ጉዳይ እጅግ አስቸኳይ ነዉ,,,,,,እንደነዚህ እንደተረሱት እንደብርቅዩ ነገሮች የሚያሳስብ ሌላ ነገር የለም »
በሰሜናዊ ማሊ ቲምቡክቱ ከተማ የተገኘዉ ጥንታዊ የሥነ-ጽሑፍ ቅርስ ይዞታዉ እንዲጠበቅ የሚያደርገዉ ፕሮጄ ከጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ከዓለማቀፍ ገንዘብ ለጋሾች እንዲሁም ጌርድ ሄንክል ተቋም ይረዳልል። እስካሁን ይህንኑ ጥንታዊ የሥነ-ጽሑፍ ቅርስ ለማስጠበቅ በሚደረገዉ ጥረት ጀርመን ዲስልዶርፍ ከተማ ከሚገኘዉ ተቋም ወደ 500.000 ይሮ ለግሶአል። የተቋሙ ዋና ተጠሪ ሚሻኤል ሃንዝለር፤ ከተቋሙ ዋና ተግባራት አንዱ ጥንታዊ የእስልምና ቅርሶችን ማዳን ነዉ፤
« ስለ እስልምና አንድ ልዩ የጥናት መረሃ- ግብር አለን፤ በአፍሪቃ ምርምርና ጥናታችን ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት በተለይ ፖለቲካ በግዜዉ በእስልምና ዉስጥ፤ የነበረዉን ታሪካዊ ሂደት እና እንቅስቃሴ አዜነንበታል። ለኛ ተቋም በተለይ ትልቅ ትኩረትና መስብ የነበረዉ ጥቂት ትኩረት የተሰጣቸዉን ሥነ-ጽሑፎች መገምገም ነበር። ከነዚህ ታሪካዊ የእጅ ጽሑፎች መካከል ከ 2 እስከ 3 በመቶ ያህሉ ጥናት የተካሄደባቸዉ ሲሆን በጣም ትልቁ ክፍል ያልተጠና እና ትኩረት ያልተሰጠዉ ነዉ»
ከሰሜናዊ ማሊ በድብቅ ወደ መዲና ባማኮ የተዛወረዉ፤ ጥንታዊ የሥነ-ጽሑፍ ቅርስ ተከማችቶ የሚገኘዉ ከቆርቆሮ በተሰራ ሳጥኖች ዉስጥ ነዉ። ጥንታዊ ሥነ-ፅሁፍን ከሚያበላሹት እንደ ብል ከመሳሰሉ ነፍሳትና ሌሎች አደጋዎች በተጨማሪ የተቀመጠበት ቆርቆሮ የዝገት አሻራ ሌላ የመበላሸት አደጋን ደቅኖበት ይገኛል። በዚህም ምክንያት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሥነ-ጽሑፎቹ የተቀመጡበት የቆርቆሮ ሳጥኖች ልዩ በሆኑ ሳጥኖች መቀየር እንዳለበት ተመልክቶአል።
የሥነ-ፅሑፍ ቅርሶቹ በምን አይነት ሳጥን ቢቀመጡ የመበላሸት አደጋዉ ሊቀንስ እንደሚችል በተለይ የጥንታዊ ሥነ-ጽሑፍ ቅርስ አጠባበቅ ባለሞያዋ ኤቫ ብሮዞቭስኪ ይገልፃሉ፤
የሥነ-ጽሑፎቹ ማስቀመጫ፤ የአየር ለዉጥን የሚቋቋም እና አየር የሚያስተላልፍ መሆን ይኖርበታል። አንድ ሰዉ ሳጥኖቹን በመጀመርያ ሲያቸዉ ሳጥኖቹ እንደቀድሞዎቹ ፖስታዎች በዉስጣቸዉ የሚገኘዉ የአዉሮጳ ሀገር መፅሐፋ ሳይሆን፤ ጥንታዊ ሥነ- ጽሑፍ መሆኑን የሚያሳዉቁ መሆን አለባቸዉ። በሌላ በኩል ማስቀመጫ ሳጥኑ አየር መለዋወጥ ሁኔታን የሚቋቋም ፤ ሥነ-ጽሑፎችን ከአቧራና ከተባይ የሚጠብቅ አይነት መሆን ይኖርበታል። በዚህም አለ በዝያ ሳጥኑ ሲታይ የቲምቡክቱ ጥንታዊ ሥነ-ጽሑፍ ያለበት ሳጥን መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። በጥንት ግዜ ሥነ-ጽሑፎች እንደሚጠረዙት ሁሉ ፤ ሁሉም ሥነ-ጽሑፎች መለበድ ይኖርባቸዋል»
እንደ ኤቫ ብሮዞቭስኪ ሁሉ በጀርመን ሃንቡርግ ዩንቨርስቲ በእስያ አፍሪቃ እና አዉሮጳ ጥንታዊ ሥነ-ጽሑፎች ላይ ተመራማሪዉ ዲሚትሪ ቦንዳረቭ በምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ሀገር በማሊ ሥነ-ጽሑፎች ላይ ምርምር አካሂደዋል፤ የቲምቡክቱ ጥንታዊ ሥነ-ጽሑፎች እንዳይጠፉ በማደስ እንዲሁም በዲጂታል መዝገብ ሥራ ላይ የሚንቀሳቀሰዉ ፕሮጂ ዋና ተጠሪም ናቸዉ፤
«ሥለ ጥንታዊ የሰዉ ልጆች አኗነር ታሪክን ማወቅ ከፈለግን እነዚህ ጥንታዊ ሥነ-ጽሑፎች ትልቅ እና እዉነተኛ ሃብት ናቸዉ! እስካሁን ያልታወቁ ብዙ ነገሮችን እንድንረዳና እንድናዉቅ ይረዱናል።ሥነ- ጽሑፎቹ፤ ለምሳሌ ከሳይንስ ምርምር ሥራዎች እጅግ ጠንካራ እዉቀትን ያዘሉ እናም ስለአፍሪቃ ታሪክ በይበልጥ እዉቀትን የሚያሳዩ መዝገቦች ናቸዉ»
በመካከለኛዉ ክፍለ ዘመን የዘመኑ ተመራማሪዎች በባህር በኩል አድርገዉ ከተለያዩ የአፍሪቃ አካባቢዎች ወደ ቲምቡክቱ በመግባት፤ የተለያዩ ምርምር ሥራዎችን አድርገዋል ታሪክንም ጽፈዋል። በሌላ በኩል ቲምቡክቱ የሰሃራ በረሃን አቋርጠዉ ለትምርትና ለመገበያየት ከተለያዩ የአካባቢዉ ሃገራት የሚመጡ ሰዎች የመገናኛ ቁልፍ ከተማም ነበረች። በዚህም ምክንያት ለዘመናት ከተለያዩ አፍሪቃ አካባቢዎች በቲምቡክቱ የተቀመጡት በርካታ የሥነ-ጽሁፍ መረጃዎች አካባቢዉን ልዩ እና ዋንኛ የጥንታዊ የመረጃ ስብስብ ማዕከል አድርጎታል፤ ሲሉ ዲሚትሪ ቦንዳረቭ ይገልጻሉ፤
«በዚህ አካባቢ የተገኙት የተለያዩ ሥነ-ጽሑፎች፤ የተመለከቱ የጥንታዊ ሥነ-ጽሑፍ አዋቂዎች የአፍሪቃን ታሪክ በከፊል ዳግም እንደ አዲስ መጻፍ ይኖርበታል ሲሉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል»
እንደ ዲሚትሪ ቦንዳረቭ፤ አካባቢዉ ላይ በተገኘዉ ጥንታዊ ሥነ-ጽሑፍ መሰረት ስለ አዲሱ የእስልምና ታሪክ እና በሰሜናዊ ማሊ ስለነበሩ ስለተለያዩ የእስልምና ቡድኖች መረጃዉን በማገላበጥ በተሻለ መንገድ መግለጽ ይቻላል። ይህ ሁሉ ጥንታዊና ታሪካዊ መዝገብ በሰሜናዊ ማሊ በሚንቀሳቀሰዉ አክራሪ ቡድን ግጭት ይወድም ነበር። በጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ,ም እስላማዊ አክራሪዎች ቲምቡክቱ እና ጋዎ ከተማን ጨምሮ ሰሜናዊ ማሊን ከተቆጣጠሩ በኃላ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ታሪካዊ መረጃን ማዉደም ጀምረዉ ነበር። ይህን ያደረጉት ዋና ምክንያት ደግሞ፤ ይኽ ጥንታዊ ቅርስ ታሪካዊ ጠቀሜታዉ ታይቶ በምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ዋጋ ስለተሰጠዉ ምዕራባዉያንን ለማጥቃት ያደረጉት ርምጃ ነበር።
በባለሞያዎች እጅ ለመታደስ የበቃዉ ጥንታዊዉ የቲምቡክቱ የሥነ-ጽሑፍ ቅርስ አብደል ካድር ሃድራ እና ሌሎች በግል ፍላጎት የተነሳሱ ግለሰቦች ሥነ-ጽሑፉን ከቲምቡክቱ ወደ ማሊ መዲና ባማኮ በድብቅ በማሸሻቸዉ በመሆኑ ምስጋና ሊቸራቸዉ ይገባል። ምክንያቱም ሥነ- ጽሑፍን ከቲምቡክቱ ወደ ማሊ መዲና ባማኮ አሽተዉ ሲወስዱ በሕይወታቸዉ ላይ ፈርደዉም ነበር። የማሊ ተወላጁ አብደል ካድር ሃድራ፤ በቲምቡክቱ ግዝፍና ታዋቂዉ በሆነዉ የማማ አድራ ቤተ -መጻሕፍት ዳይሪክተርና በከተማዋ የሚገኙ የጥንታዊ ሥነ-ጽሑፎች ጥበቃ ቡድን ተጠሪ ናቸዉ፤
« ሥነ-ጽሑፉን ከቲምቡክቱ የማሸሹ ተግባር አደገኛና እጅግ እጅግ ከባድ ሥራ ነበር። እንደድል ሆኖ ሁሉም ነገር በሰላም ተጠናቀቀ። በአሁኑ ሰዓት በባማኮ እና በቲምቡክቱ በሁለቱ ከተሞች መካከል የተለያዩ ኮሚቴዎችን አቋቁመናል። እነዚህ ኮሜቴዎች ስነ-ጽሑፎቹን በጥንቃቄ በመኪና ላይ ይጭናሉ ሌሎቹ በመኪና ወደ ባማኮ ያደርሳሉ፤ ሶስተኛዉ ኮሜቴ ደግሞ ባማኮ የደረሰዉን ቅርስ ተቀብሎ ደሕንነቱ ወደ ሚጠበቅበት ቦታ ያደርሳል። በርግጥ ይህ የሥራ ሂደት እጅግ ከባድ እና እጅግ በአዝጋሚ ሁኔታ ነዉ እየተከናወነ ያለ ነዉ»
ታሪካዊዉን የሥነ-ጽሑፍ ቅርስ በድብቅ ከቲምቡክቱ ወደ ባማኮ የማሻገሩ ተግባር ስድስት ወራትን ፈጅቶአል። በቲምቡክቱ ግዝፍና ታዋቂዉ የማማ አድራ ቤተ -መጻሕፍት ዳይሪክተርናw፤ በከተማዋ የሚገኙ የጥንታዊ ሥነ-ጽሑፎች ጥበቃ ቡድን ተጠሪ አብደል ካድር ሃድራ፤ ከዚህ አድካሚ ሥራ በኃላ እጅግ ከፍተኛና ታሪካዊ ዋጋ ያለዉ የሥነ-ጽሑፍ ቅርስ ከመጥፋት በመዳኑ ደስተኛ ናቸዉ።
« በእዉነቱ ከሆነ አብዛኞቹ ሥነ-ጽሁፎች እጅግ እጅግ ጥንታዊና እንዳይበላሹ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚሹ ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ የተበላሹ መሆናቸዉ እሙን ነዉ። ከቲምቡክቱ ወደ መዲና ባማኮ የተዛወሩት ጥንታዊ ሥነ-ጽሑፎች ነገ ዛሪ ሳይባል መታደስ እና ታሪካዊ ይዘታቸዉ ተጠብቆ እንዲዘልቅ ማድረግያዉ ግዜ አሁን ነዉ። እጅግ ጥንታዊ የሆነዉ ይህ ሥነ- ጽሑፍ በዲጂታል መዝገብ ሰፍሮ ግልባጭ መቀመጡ ለምርምር ሥራ መረጃ ጠቀሜታ እንዲዉል ቀላል መንገድንም ይከፍታል»

እንድያም ሆኖ ገና ብዙ ሊሰራ የሚገባ ጉዳይ መኖሩን የጥንታዊ ሥነ-ጽሑፎች እድሳት ባለሞያዋና የቲምቡክቱን ጥንታዊ የሥነ-ጽሑፍ እድሳት ፕሮጄ ባልደረባ ኤቫ ብርዞቭስኪ ይገልፃሉ። ኤቫ ለአንዳንዶቹ የወረቀት ላይ ሥነ- ጽሑፎች እድሳት ስልጠናን ሲሰጡ፤ ሌሎች ሥነ-ጽሑፎች የተቀመጡበትን ሳጥኖች ንፅህና የማፅዳትና፤ የጥበቃዉን ተግባር ይወስዳሉ። በዚህም ኤቫ ብርዞቭስኪ የእድሳቱ ተግባር የሰለጠኑ ባለሞያዎች ጥንታዊ ሥነ-ጽሑፍ ቅርሶቹን የሚያድሱበት ቦታን ማሊ መዲና ላይ ከፍተዋል። በዚህ ቦታ ላይ እድሳት ማድረጉ ቢጀመርም እጅግ አዝጋሚ በሆነ መልኩ ነዉ።
« ስድሳቱን እና ጽዳቱን አንድ ሰዉ ቢሠራዉ ኖሮ፤ ሥራዉ ለዘመናት አይጠናቅም። በርካታ ሰዎች እንዲሰሩት፤ ሰፋ ያለ የፊናንስ እገዛ ቢያገኝ በርግጥም ሥራዉ በቅልጥፋና ቶሎ መጠናቀቅ ይችላል። ግን አሁን ባለበት ሁኔታ ምናልባትም አአንድ አeና ከዛም በላይ አስራተ ዓመታት መጠበቅ ይኖርብናል»
የቲምቡክቱ ጥንታዊ የእጅ ሥነ-ጽሑፍ ቅርሶች፤ ታሪካዊ ይዞታቸዉን ጠብቀዉ ለዘመናት በታሪክ ማህደርነት እንዲዘልቁ በሚደረገዉ እንቅስቃሴ ገንዘብ ለጋሾች እጃቸዉ እንደማያጥር የዘርፉ ባለሞያዎች ተስፋቸዉን ይገልጻሉ። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ዘገባዉን በመጫን ይከታተሉ!

አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ

Im Krieg zerstörte Kulturstätten Timbuktu
ምስል picture alliance/dpa
Bildergalerie Timbuktu Restauration jahrhundertealter Manuskripte
ምስል CSMC
Bildergalerie Timbuktu Restauration jahrhundertealter Manuskripte
ምስል CSMC
Bildergalerie Timbuktu Restauration jahrhundertealter Manuskripte
ምስል CSMC
Bildergalerie Timbuktu Restauration jahrhundertealter Manuskripte
ምስል CSMC