1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍጋኒስታን፤ ስደት የጠናባቸዉ የጦርነት ልጆች፤

ሐሙስ፣ መስከረም 12 2009

ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 88 ሺህ ሕፃናት በአዉሮጳ ኅብረት ሃገራት ለጥገኝነት ተመዝግበዋል። ከእነዚህ መካከል ገሚሱ ከአፍጋኒስታን የተሰደዱ ናቸዉ። ሀገራቸዉ ዉስጥም በርካታ የጦርነት ልጆች ለመሰደድ ዕድላቸዉን እየተጠባበቁ ነዉ። አፍጋኒስታን ዉስጥም በአሁኑ ወቅት 1,2 ሚሊየን ሰዎች ስደት ላይ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/1K6qJ
Afghanistan Flüchtlingslager in Kundus
ምስል Getty Images/AFP/S. Marai

[No title]

ትንሿ ናዉዚያ በፍጥነት ወደቀች። ቀዩ የራስ መሸፈኛዋ በአዋራማዉ መሬት ላይ ያንጸባርቃል። በስደተኞቹ መጠለያ ጣቢያ ጎልቶ የሚታየዉ ቀለም ነዉ። የምትኖርበት ስፍራ ጭቃማ ነዉ። ትዉስታዋ ይህ ነዉ፤

«ተኩስና ፍንዳታዉን አስታዉሳለሁ። አንድ እጅግ ብሩህ እና ከፍተኛ ፍንዳታ እንደዉም በእኛ የአትክልት ስፍራ ደርሷል።»

የጀርመን ወታደሮች የጦር ሰፈር ሲውገኝበት በነበረዉ ሰሜን አፍጋኒስታን ኩንዱስ ዉስጥ የተካሄደዉ ዉጊያ አባት እና ጓደኛዋ የነበረችዉን የአጎቷን ልጅ ነጥቋታል። የ10 ዓመቷ ናዉዚያ ቀጠለች፤

«ቤቴ በተለይ ደግሞ ጓደኞቹ ይናፍቁኛል።»

ናዉዚያ ከእናቷ እና ከስምት ወንድም እህቶቿ ጋር ከኩንዱስ ወደ ዋና ከተማዋ ካቡል የተፈናቀሉት። የነበረችዉን አነስተኛ የእርሻ ቦታ፣ ከብቶች እና ሰብል ትቶ የተሰደደዉ ይህ ቤተሰብ ከካቡል በስተምሥራቅ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ በሠራዉ የጭቃ ጎጆ ዉስጥ ተጠልሎ ይገኛል። በዚህ ስፍራ ከኩንዱስ ክፍለ ሀገር በጦርነት ምክንያት የተሰደደ 50 የሚሆን ቤተሰብ ሰፍሯል። እናም አዲሱ የስደተኞች መጠለያ በሰማይ ጠቀስ ፎቆች አቅራቢያ በጭቃማ ስፍራ ጎልቶ ይታያል። ከበርካቶቹም አንዱ መሆኑ ነዉ።

በመጠለያዉ የሚገኙት ሰዎች ራሳቸዉን መርዳት ይጠበቅባቸዋል። ናዉዚያ እና እህት ወንድሞቿ ትምህርት ቤት አይሄዱም። ሴቶቹ ከእናታቸዉ ጋር በመሆን የሰዎችን ልብስ በማጠብ ሥራ ተሠማርተዋል፤ ወንድሞቿ ከብቶች ይጠብቃሉ፤ ወይም የግንባታ ሥራ ባሉባቸዉ ስፍራዎች በቀን ሠራተኝነት ይሸቅላሉ።

«በሜዳችን ከጓደኞቼ ጋር ኳስ መጫወት እችል ነበር። ያ በጣም ይናፍቀኛል። የፍራፍሬ ዛፎቻችንም እንዲሁ። አንድ ነገር ብቻ እመኛለሁ፤ ይኸዉም በቶሎ ወደቤታችን ተመልሰን በድጋሚ ኳስ መጫወት ነዉ።»

የናዉዚያ ወንድም የ13 ዓመቱ መሐመድ አክባር ይህን ሲናገር ታላቅ ወንድሙ አብዱል መናን ራሱን በማወዛወዝ ሃሳቡን መጋራቱን ያሳያል።

Afghanistan Flüchtlinge in einem Camp bei Kabul
ምስል picture-alliance/epa/Bildfunk/J. Jalali

15 ዓመቱ ነዉ። ታላቅ እንደመሆኑ በጫንቃዉ ላይ ከአሁኑ በርካታ ኃላፊነት የተሸከመ ይመስላል። ኩንዱስ በነበሩበት ጊዜ ሶስት ዓመት ብቻ ነዉ መማር የቻለዉ። በመጠኑ ማንበብ እና መጻፍ እንደሚችል ይናገራል። ሃሳቡ ግን ትልቅ ነዉ።

«ወደ ጀርመን ሄጄ ሥራ በመሥራት ለቤተሰቦቼ ገንዘብ ለማጠራቀም እፈልጋለሁ። ጉዞዉ አደገኛ መሆኑን አዉቃለሁ። ነገር ግን የጀርመን ኑሮ እንዴት ጥሩ እና አስተማማኝ እንደሆነ ሰምቻለሁ።»

አብዱል መናን ወደ አዉሮጳ ለመምጣት እንዲችል ለህገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች የሚከፍለዉ ገንዘብ ከቤተዘመዶች እና ከሌሎች ሰዎች ለመበደር ሞክሯል። ይህንንም ለእናቱ በመንገርም ኩንዱስ የሚገኘዉ መሬታቸዉን እንዲሸጡም ጠይቋል።

«እርግጥ ነዉ እዚሁ ከእኛ ጋር እንዲኖር ነዉ የምፈልገዉ። ነገር ግን የእኛ ኑሮ ምንኑም የማይሻሻል ከሆነ የግድ እሱን እዚሁ መያዝ አይኖርብኝም፣ እንደዉም አደፋፍረዋለሁ።»

ይላሉ የነናዉዚያ እናት። ትልቁ ልጃቸዉ ወደ ጀርመን መጓዝ ከቻለም የእሳቸዉም ኑሮ ይሻሻል የሚል ተስፋ የሰነቁ ይመስላል። ባጠቃላይ 1,2 ሚሊየን የአፍጋኒስታን ዜጎች በሀገራቸዉ ዉስጥ ተሰደዉ ይኖራሉ። ካለፈዉ ዓመት ጥር ወር አንስቶ እስከ ነሐሴ ወር ማለቂያ ድረስም 250 ሺህ የሚሆኑት በጦርነት ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸዉ ተፈናቅለዋል። በሀገራቸዉ ዉስጥ ከተፈናቀሉት 56 በመቶ የሚሆኑትም ከኩንዱስ እንደመጡት እንደ ናዉዚያ፣ መሐመድ እና አብደል መናን ያሉ ልጆች ናቸዉ።

ሸዋዬ ለገሠ/ዛንድራ ፒተርስማን

ኂሩት መለሰ