1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጦር ወጪ ተመልካች መዘርዝር

ረቡዕ፣ የካቲት 23 2003

ቦን የሚገኘው በምህጻሩ ቢክ በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ኮንቨርሽን ማዕከል የተባለው መንግስታዊ ያልሆነው ድርጅት እአአ ለ 2009 ዓም የዓለም ሀገሮች ለጦሩ ዘርፍ ያዋሉትን ወጪ የተመለከተበትን መዘርዝር ሰሞኑን አወጣ።

https://p.dw.com/p/R5gh

እአአ ከ 1990 ዓም ወዲህ በያመቱ የሚወጣው የማዕከሉ ጥናት ለጦር ኃይሎች እና ለጦር መሳርያ ግዢ የሚመደበው ገንዘብ ለሌሎቹ የኑሮ ዘርፎች ከሚወጣው ጋ ሲነጻጸር የሚገኝበትን ደረጃ ይመረምራል።



በዓለም አቀፍ ኮንቨርሽን ማዕከል ጥናት እንደሚያሳየው፡ ከዓለም ሀገሮች ሁሉ ለጦር መሳርያ ትጥቅ እና ለጦር ኃይሎቻቸው እጅግ ብዙ ገንዘብ የሚያወጡት የቅርብ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ናቸው። በጥናቱ መዘርዝር ላይ እስራኤል የመጀመሪያውን ቦታ ይዛለች። ሶርያ፡ ዮርዳኖስ፡ ክዌት፡ ኦማን፡ ባህሬን፡ ሳውዲ ዐረቢያ፡ የተባበሩት የዐረብ ኤሚሮች እና ኢራክ ፡ እንዲሁም፡ አልጀርያን እና ሊቢያን የመሳሳሰሉ አፍሪቃውያት ሀገሮች በመጀመሪያዎቹ ሀያ ሀገሮች ዝርዝር ውስጥ ይገኛሉ። ይህም የጦር ኃይሉ በቦኑ ማዕከል ተመራማሪ ያን ግሬበ አስተያየት መሰረት፡  በወቅቱ ብርቱ የህዝብ ተቃውሞ በሚካሄድባት ሊቢያን በመሳሰሉ ሀገሮች ውስጥ ትልቅ ሚና መያዙን  በግልጽ የሚጠቁም ሆኖዋል።
« ሊቢያ በመዘርዝሩ ውስጥ የአስራ ሁለተኛውን ቦታ ይዛለች። እና  የጦር ኃይሉ አባላት፡ ማለትም፡ ከሀገሪቱ መሪ ጎን የቆሙት እና ከድተው አሁን ሽሽት የገቡ የጦር ቡድኖች ሁሉም በአሁኑ ውዝግብ ላይ ጠንካራ ሚና መያዛቸው አያስገርምም። የሊቢያ ጦር በሚገባ የታጠቀ ነው። ባለፉት ቀናት በቴሌቪዥን የታዩ ስዕሎች የጦር መሳርያዎች እና የጦር መሳርያ ማከማቺያዎች አረጋግጠዋል። ይህም ባለፉት ዓመታት ወደ ሀገሪቱ ግዙፍ የጦር መሳርያ መግባቱን ያሳያል።

Britische Artillerie beschießt Basra
ምስል AP

በሌሎች አፍሪቃውያት ሀገሮች አንጻር ከዘንድሮው የማዕከሉ መዘርዝር ውስጥ የኤርትራ ስም የለም። ምክንያቱን ሲያስረዱ፡
« የኤርትራ ስም በመዘርዝሩ ያልተካተተው ስለዚችው ሀገር አንድም ቁጥር ባለማግኘታችን ነው። ይህም ቢሆን ግን ሀገሪቱ አሁንም ከፍተኛ የጦር መሳርያ ትጥቅ ያላት ሀገር ናት ብለን እንገምታለን። ከኢትዮ ኤርትራ ድንበር ጦርነት ፍጻሜ በኋላ በሀገሪቱ ግልጽ የሆነ የጦር ኃይሉን ትጥቅ የማስፈታት ወያእም የጦር መሳርያ የመቀነስ ጥረት አልተካሄደም። »
ከብዙ ጊዜ ወዲህ ውዝግብ የቀጠለባቸው ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክን የመሳሰሉ አፍሪቃውያት ሀገሮች ለጦር ኃይሉ ብዙ ገንዘብ መድበዋል ተብለው ቢታሰቡም፡ ለጦር መሳርያ መግዣ ያወጡት ገንዘብ ያን ያህል አለመሆኑን ጥናቱን ያዘጋጀው ማዕከል ተመራማሪ ያን ግሬበ አስታውቀዋል።
« አፍሪቃውያቱ ሀገሮች ዘመናዩን እና በከፍተኛ ስነ ቴክኒክ የተመረተውን የጦር መሳርያ ለመግዛት የፊናንሱ አቅም ተጓድሏቸው ይገኛል። በዚህ ፈንታ ቀላል የጦር መሳርያ በብዛት የተስፋፋበት ሁኔታ አለ። ግን ይህንኑ የጦር መሳርያ የሚመለከት መረጃ ባለመኖሩ በጥናቱ ሊካተት አልቻለም። በአፍሪቃ የሚታየው ችግር ከመንግስት ጦር ኃይላት ጎን የግል የጸጥታ አስከባሪ ቡድኖች መኖራቸው በብዙ ሀገሮች ለሚታየው የአለመረጋጋት ሁኔታ ምክንያት ሆነዋል። »    »
ማዕከሉ በያመቱ የሚያወጣው መዘርዝር የበለጸጉ መንግስታት ውዝግብ ለበዛባቸው ሀገሮች የጦር መሳርያ እንዳይልኩ ለማድረግ የህዝቦቻቸውን ንቃተ ህሊና ከፍ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ያን ግሬበ አስረድተዋል።
«  በመዘርዝሩ አማካኝነት፡ለወትሮው በድብቅ በሚያዘው የጦር መሳርያ ግዢ መረጃ ላይ ግልጽነት እንዲኖር ለማድረግ ተስፋ አድርገናል። ጀርመንን የመሳሰሉ ኢንዱስትሪ ሀገሮች ውዝግብ ለበዛባቸው ወይም የጦር መሳርያ ትጥቅ እሽቅድምድም ለሚካሄድባቸው ሀገሮች የጦር መሳርያ እንዳይሸጡ ለማድረግ የሚያስችለውን ውይይት በህብረተሰቡ ዘንዳ ለማጀመር እንፈልጋለን። »
ለጦር መሳርያ ብዙ ገንዘብ አለማውጣት ማለት ግን በሀገራቱ ውስጥ  ሰላም ና መረጋጋት ሰፍኖዋል ማለት አለመሆኑን ግሬበ አስታውቀዋል። ለምሳሌ በመዘርዝሩ የመመጨረሻውቹን አርባ ቦታዎች ከያዙት ሀገሮች መካከል ሰላሳዎቹ የመውደቅ ስጋት የተደቀነባቸው ወይም ስርዓት አልበኝነት ያሰጋቸው ሀገሮች ናቸው።

አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ