1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በማቆያዎች ያሉ ኑሮ ተመችቶናል ይላሉ

ዓርብ፣ ጥር 5 2009

“ጫካው” ተቃጠለ፡፡ የተጥመለመለ ግዙፍ እና ጥቁር ጭስ ወደ ሰማይ ወጣ፡፡ በየመጠለያው የተሰገሰጉት የምግብ ማብሰያ ሲሊንደሮች ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ እያሰሙ ሽቅብ ጎኑ፡፡ የእሳቱ ወላፈን ድንኳን ይሁን የላስቲክ ቤት፣ የጣውላ ዛኒጋባ ይሁን ተጎታች የመኪና ቤት- ሁሉንም ሳያስተርፍ ያነድ ገባ፡፡

https://p.dw.com/p/2Vn7m
Oromos in Calais refugee Camp
ምስል DW/T.Waldyes

በማቆያዎች ያሉ ኑሮ ተመችቶናል ይላሉ

ፖሊሶች ተሯሯጡ፡፡ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ተራወጡ፡፡ ሰውን ከእሳቱ አሸሹ፡፡ ቃጠሎውንም በቁጥጥር ስር አዋሉ፡፡ የሺህዎች መኖሪያ የነበሩ መጠለያዎች ግን አመድ ሆኑ፡፡ ይህ በካሌ ጫካ የሆነ ነው፡፡ በጥቅምት ወር አጋማሽ፡፡

ካሌ ፈረንሳይ ጫፍ ላይ ተቀምጣ እንግሊዝን አሻግራ የምትመለከት ቦታ ነች፡፡ የካሌ ጫካ ለስሙ ጫካ ይባል እንጂ ጥቅጥቅ ያለ ደን አልነበረም፡፡ ዙሪያ ገባውን ዛፎች ቢኖሩም ገላጣ ስፍራው ይበዛል፡፡ በገላጣው ቦታ ላይ ታዲያ የመጠለያዎች ጫካ ነበር፡፡ ሊያውም የአስር ሺህዎች መኖሪያ፡፡ ከኢትዮጵያ እስከ ኤርትራ፣ ከቻድ እስከ ሱዳን፣ ከኢራቅ እስከ አፍጋኒስታን የመጡ ስደተኞች መናኸሪያ ነበር፡፡ 

ዛሬ ነበር ሆኗል፡፡ ከቃጠሎው የተረፉትን የፈረንሳይ መንግስት አፍርሷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያውያን እና የኤርትራውያን መጽናኛ የነበረው የጀንግሉ ቅዱስ ሚካኤል የላስቲክ ቤተክርስቲያን እንኳ ከዚህ አላመለጠም፡፡ አፍረሽ ግብረ ኃይል እና ኤክሳካቫተር ዘምተውበታል፡፡ መጠለያቸውን ላጡት ስደተኞች የፈረንሳይ መንግስት መፍትሄ አበጅቶላቸዋል፡፡ ጉዳያቸው በቅጡ እስኪታይ በመላው ፈረንሳይ ባሉ አነስተኛ ከተሞች እንዲቆዩ ወደየቦታዎቹ አጓጉዟቸዋል፡፡   

ኡመር ሃጆ ይህን ዕድል ከተጠቀሙ ኢትዮጵያውያን መካከል ነው፡፡ ወደ ደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ ከተወሰዱት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አሁን ሱስቶ በተሰኘች አነስተኛ ከተማ ውስጥ ከ33 ኢትዮጵያውያን ጋር እየኖረ ይገኛል፡፡ ከካሌ ስለነበረው አወጣጥ እና አሁን ስላለበት ቦታ እንዲህ ይገልጻል፡፡

Calais Flüchtlingslager
ምስል DW/T.Waldyes

“ካሌ የእዚህ ሀገር የስደተኛ ተጠያቂ ሰው መጥቶ ለእኛም ሆነ እዚያ ላለው ህዝብ እያንዳንዱ ጋር እየሄደ ‘ከዚህ መነሳት የግድ ነው፡፡ ከዚህ ትነሱና ለአካለ መጠን ያልደረሱትና ቤተሰብ ያላቸው ወደ እንግሊዝ ይሄዳሉ፡፡ ሌሎቹ እዚሁ ወረቀት ይሰጣቸዋል፡፡ ለእናንተ የሚያስፈልገው እንክብካቤ ይደረግላችኋል፡፡ እዚህ ጉዳት ነው እንጂ ጥቅም የለም’ ብሎ ከዚያ ተነሳን፡፡ ከዚያ እንደተነሳን መጀመሪያ ያቩኮ ነው የመጣነው፡፡ ያቩኮ አንድ ሳምንት ቆይተን ከዚያ ወደ ሱስቶ መጣን፡፡ አሁን ሰላም ነው ያለነው፡፡ ቆንጆ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው” ይላል፡፡ 

ሱስቶ የተሰኘችው እርሱ ያለባት ከተማ በዓለም በወይን ጠማቂነቷ ስሙ በገነነው ቦርዶ ውስጥ የምትገኝ ናት፡፡ የሀገሬው መንግስት ዜጎቹ ለበጋ ዕረፍት የሚገለገሉባቸውን ቤቶች ወደ ስደተኞች ጊዜያዊ መቆያ ቀይሮ ተገን ጠያቂዎቹን በየቦታው ደልድሏቸዋል፡፡ ስደተኞቹ በአንድ ቤት ውስጥ ሶስትም፣ አራትም፣ ስድስትም እየሆኑ ይኖራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ጋር መኝታ ክፍል የግል፣ መታጠቢያ ቤት እና ሳሎን የጋራ ይሆናል፡፡ ሌሎቹ ዘንድ መኝታ ክፍልን ለሁለት መጋራት ግድ ይላል፡፡  

የፈረንሳይ መንግስት ስደተኞቹን ይንከባከቡ ዘንድ የመደቧቸው ሰዎች የተዘጋጀ ምግብ ያቀርቡላቸዋል፡፡ ስደተኞቹ እንደሚናገሩት ከሆነ ጊዜያዊ የስደተኞች መለያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለአንዳንድ ነገር መግዢያ በሚል ከዚህ ወር ጀምሮ  300 ዩሮ ማግኘት ጀምረዋል፡፡ የቋንቋ ትምህርትም እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ እርሱን ሲያጠናቅቁ ደግሞ የሙያ ትምህርት እንደሚሰጣቸውና ከዚያ ወደ ስራ እንደሚገቡ ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ 

Calais Flüchtlingslager
ምስል DW/T.Waldyes

ስደተኞቹ ዛሬ ትንሽ ዕረፍት ያግኙ እንጂ ፈረንሳይ ለመደረስ በርካታ ስቃዮችንና መሰናክሎችን አልፈዋል፡፡ ኡመር ወደ አውሮፓ ለመግባት 600 ገደማ ሰዎች በጫነ ጀልባ ሜዴትራንያንን ባህርን ሲያቋርጥ ጀልባቸው ተሰንጥቆ በተዓምር እንደተረፉ ይናገራል፡፡ ድንገት የኢጣሊያ ነፍስ አድን መርከብ ባይደርስላቸው ኖሮ አንድ ሰዓት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ሁሉም ያልቅላቸው እንደነበር በሀዘን ያስታውሳል፡፡ እርሱ ዕድለኛ ሆኖ አውሮፓ ቢደርስም ሺህዎች ግን የባህር ሲሳይ ሆነው ቀርተዋል፡፡ 

እንደተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት መረጃ ከሆነ በጎርጎሮሳዊው 2016 ብቻ 3‚740 ስደተኞች ሜዴትራንያንን ሲያቋርጡ ጀልባቸው ተገልብጦ ሞተዋል፡፡ ይህ እንግዲህ በየበረሃው ቀልጠው የቀሩትን ሳይጨምር ነው፡፡ ከአርሲ ተነስቶ፣ ሱዳን እና ሊቢያን አቋርጦ፣ ጣሊያንን ረግጦ ፈረንሳይ የገባው ኡመር ህልሙ እንግሊዝ መሻገር ነበር፡፡ ፈረንሳይ እንዳይቆይ አስወሰነውት ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ ህጋዊ ወረቀት የማግኘቱ ጉዳይ እንደነበር ይናገራል፡፡ ለዚያም ነበር ካሌ ላይ ሁለት ወር ገደማ መቆየቱ፡፡

“ይቺ ሀገር ፈረንሳይ ‘ለኢትዮጵያውያን ወረቀት አትሰጠም፡፡ እዚህ ምንም ጉዳይ አይታይህም ’ ስንባል ነው ወደ እንግሊዝ እንሄዳለን ብለን ካሌ መሄድ የመረጥነው” ይላል ኡመር፡፡

ኡመር ካሌ ሲፈርስ ህልሙ ቢጨናገፍም እርሱ የሚያውቃቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ግን ወደ “ተስፋቸውን ምድር” ገብተዋል፡፡ የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ መንግስታት በተስማሙት መሰረት ብሪታንያ “ለአካለመጠን ያልደረሱ” ስደተኞችን ማጣሪያ አካሄዳ ወደሀገሯ ወስዳለች፡፡ የ27 ዓመቱ ኡመር እንደአንዳንዶች ዕድሜውን ቀንሶ ዕድሉን እንዳይሞክር ተፈጥሮ ገድባዋለች፡፡

በየከተማው የተበተኑት ኢትዮጵያውያንም እንደእርሱ ወጣቶች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ከ24 እስከ 30 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ መሆናቸውን ኡመር ይናገራል፡፡ ኤርሽራዶ በተባለች አነስተኛ ከተማ የተመደበውና ስሙ እንዲጠቀስ የማይፈልገው የአሰላ ወጣት ዕድሜው 25 ነው፡፡ “በእንግሊዝ ህጋዊ የስደተኛ መለያ ወረቀት በሶስት ወር ውስጥ ይሰጣል” ሲባል በመስማቱ ወደዚያ ለመሻገር በካሌ አንድ ወር እንደቆየ ይናገራል፡፡ 

Calais Flüchtlingslager
ምስል DW/T.Waldyes

በአውሮፓ ህጋዊ ወረቀት ስራ ለማግኘት አንድ መስፈርት ነውና እርሱም ሆነ ሌሎች ስደተኞች ያንን አስቀድሞ መያዝ አጥብቀው ይፈልጉታል፡፡ የአሰላው ወጣት በኤርሽራዶ ቆይታው ምንም ጊዜዊ ቢሆንም ሲሻው የነበረውን ወረቀት አግኝቷል ፡፡

“የ10 ዓመት የሚሰጥ ወረቀት አለ፡፡ ለጊዜው የተሰጠን የስድስት ወር ወረቀት የሚቀየር ጊዜያዊ ወረቀት ነው፡፡ የ10 ዓመቱ ከሶስት ወር በኋላ ይመጣል ተብሏል፡፡ ከፓስፖርቱ ጋር አብራ የምትመጣ የስደተኛ ካርድ የምትሰጥ አለች፡፡ ይሰጣል እየተባለ ነው፡፡ እዚህ ያለነው ወደ 48 ሰዎች ወረቀቱን አግኝተናል ማለት ይቻላል” ይላል፡፡  

የአሰላው ወጣት ከእርሱ ጋር ያሉትም ሆነ በአቅራቢያው ባሉ ከተሞች የተደለደሉት ኢትዮጵያውያን ሁሉም ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ኡመርም በዚህ ይስማማል፡፡ በሁለቱም ቦታዎች ከወለጋ እሰከ አርሲ፣ ከጅማ እስከ ሸዋ፣ ከባሌ እስከ ሀረርጌ የተሰደዱ ወጣቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ብዙዎቹ ሀገር ለቀው የወጡበት ምክንያት ደግሞ ተመሳሳይ ነው፡፡ በኦሮሚያ ከፈነዳው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ እስር እና ግድያ አሰግቷቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ 

ከስደተኞቹ ውስጥ አብዛኞቹ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ ናቸው፡፡ የአሰላው ወጣት ለምሳሌ በአምቦ ዩኒቨርስቲ በኢንጂነሪንግ እንደተመረቀ ከሀገር ለመውጣት መገደዱን ይናገራል፡፡ ኡመር ደግሞ ነጋዴ ነበር፡፡ ሁለት ልጆቹን እና ባለቤቱን ሀገር ቤት ትቶ ነው ስደት የገባው፡፡ እርሱም ሆነ ሌሎቹ ሀገራቸውን የለቀቁት ወደው ሳይሆን ተገደው እንደሆነ ያስረዳል፡፡ 

“እነኚህ ልጆች ገና ወጣት ናቸው፡፡ ያው እነርሱ [የተሰደዱበት] በመንግስት ምክንያት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ግጭት፣ ብዙ ችግር ሀገራችንን ላይ ስላለ እንደ ኦሮምያ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ ሁሉም በመንግስት እየተጎዳ ነው፡፡ የሚማር ትምህርቱን ትቶ፣  የሚነግድ ንግዱን ት፣ በእርሻ የሚኖር የራሱን እርሻና መሬት ትቶ ስደቱን የመረጠው ያው በመንግስት ምክንያት ነው፡፡ ከመንግስት ጋር መኖር ሲያቅተው ነው፡፡ ሰርቶ መኖር አልቻለም፤ ነግዶ መኖር አልቻለም፤ ተምሮ በትምህርቱ [ትልቅ] ቦታ ላይ መድረስ አልቻለም፡፡ መንግስት ያመጣው ችግር ነው እንጂ ይህን ህዝብ ያሰደደው ወድዶ፣ ወይ የራሱን  ሀገር ጥሎ፣ የራሱን ሀገር አልፈልግም ብሎ ለቅቆ የሚሄድ ሰው የለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ፍላጎትም ያለው ሰው ያለ አይመስለኝም ” ይላል ኡመር፡፡ 

Calais Flüchtlingslager
ምስል DW/T.Waldyes

የኦሮሞ ወጣቶች ብሶት እና ተቃውሞ በካሌ እያሉም ሳይቀር በግልጽ የሚታይ ነበር፡፡ በኦሮሚያ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመግለጽ እንደምልክት ያገለገለው የተጣመረ እጅ በካሌ ባቋቋሙት ትምህርት ቤት ግድግዳ ላይ በትልቁ ስለውት የአላፊ አግዳሚው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ በኦሮሞዎች ዘንድ የተቃውሞ ባንዲራ ተብሎ የሚታወቀውን ሰንደቅ ዓላማ ከቤቶቻቸው ጣራ ከፍ አድርገው ተክለውም ታይተዋል፡፡ 

በካሌ ኦሮሞዎች ጎላ ብለው ይታዩ እንጂ ከሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ የመጡ ስደተኞችም በርካታ ነበሩ፡፡ ከአዲስ አበባ በተለምዶ ጨርቆስ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የሄዱ ወጣቶች በአንድ ግቢ ተሰባስበው ነበር የሚኖሩት፡፡ በጣውላ የተሰራቸው አነስተኛ መጠለያቸው ግድግዳ ላይ ካሌን ደርሰው ወደ እንግሊዝ የተሻገሩ የሰፈራቸው ልጆች ስም በዝርዝር ተጽፏል፡፡ እንደ እነርሱ ይሳካላቸው ዘንድ አምላካቸውን ይለምኑት የነበሩ ወጣቶች ዛሬ ተበታትነዋል፡፡ አሁን የት እንዳሉ ዱካቸውን ማግኘትም አስቸጋሪ ነው፡፡ 

ኡመር እና የአሰላው ወጣት ስለካሌ ቆይታቸው ሲጠየቁ ያንገሸግሻቸዋል፡፡ “ህይወታችንን ለማትረፍ ከሀገር ቤት ተሰደን ተመሳሳይ ስጋት ውስጥ እንድንገባ ያደረገን ቦታ ነው” በሚል ይገልጹታል፡፡ ዳግም ያንን ቦታዞር ብለው ማየትም አይሹም፡፡ እነርሱ እንደዚህ ቢሉም በመቆያ ቤቶች ያሉ ስደተኞች ወደ ካሌ ተመልሰው መጠለያዎችን መቀለስ መጀመራቸው እየተዘገበ ነው፡፡ ጉዳዩ የሚያሳስባቸው የእንግሊዝ መገናኛ ብዙሃን ወደ ቦታው በመጓዝ ጭምር የስደተኞቹን መመለስ የሚያረጋግጡ ዘገባዎች አውጥተዋል፡፡ 

እንደ መገናኛ ብዙሃኑ ዘገባ በስድስት የተለያዩ የካሌ ቦታዎች የስደተኞች መሰባሰቢያን ተመልክተዋል፡፡ የካሌ መጠለያ ከመፍረሱ በፊት ስደተኞችን በሚረዳ የግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ ታገለግል የነበረችውና አሁን በበጎ ፍቃደኝነት የምትሰራው አሌክሳንድራ ሲመንስም ይህንኑ ታረጋግጣለች፡፡ ከተመለሱት ውስጥ ኢትዮጵያውያን አሊያም ኤርትራውያን ይኖሩ እንደው ጠይቂያት ነበር፡፡  

“አሁን መቀመጫዬን ፓሪስ ስላደረግሁ እርግጠኛውን የስደተኞቹን ዜግነት አላውቅም፡፡ ነገር ግን በርከት ያሉ ሰዎች ጉዟቸውን ወደ [እንግሊዝ] ለመቀጠል ወደ ካሌ መመለስ መጀመራቸው መረጃው አለኝ፡፡ በካሌ ካምፕ ቆይተው ወደ መቆያ ጣቢያዎች እንዲዘዋወሩ በተደረጉት ስደተኞች ላይ ተመስርቼ እንደምገምተው ወደቦታው ከተመለሱት ውስጥ አፍሪካውያን ይኖሩበታል፡፡ ነገር ግን ከየትኛው ሀገር እንደሆኑ ለመናገር አልደፍርም” ትላለች፡፡

Calais Flüchtlingslager
ምስል DW/T.Waldyes

ኡመርም ሆነ የአሰላው ወጣት ወደካሌ የተመለሰ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ አለማየታቸውንም ሆነ መኖሩንም አለመስማታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በካሌ የነበሩትን ስደተኞች ብዛት እና ማንነት በእርግጠኝነት ለማወቅ አዳጋች ነበር፡፡ ይፋዊ የሆነ የስደተኛ ጣቢያ ባለመሆኑ ተገቢውን ምዝገባ የሚያካሄድ ተቋም አልነበረም፡፡ አሌክሳንድራ በምትሰራበት ግብረ ሰናይ ድርጅት የነበረው መረጃ ላይ ተመርኩዛ በቁጥር ከፍተኛ ቦታውን ይዘው የነበረው አፍጋኒስታናውያን እና ሱዳናውያን እንደነበሩ ታስታውሳለች፡፡ የኤርትራውያን ቁጥርም ከፍ ያለ እንደነበር ትናገራለች፡፡ ኢትዮጵያውያን በቁጥር ከኤርትራውያን ያነሱ እንደነበሩም አልዘነጋችም፡፡ 

አሌክሳንድራ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ወደ እንግሊዝ ለመሻገር ዕድሜ ተቀንሶ “ለአካለ መጠን አልደረስኩም” እንደሚባል ሁሉ ዜግነት ተቀይሮም “ኤርትራዊ ነኝ” እንደሚባልም ጭምር አታውቅም፡፡ አንድ መልክና ቀለም ያላቸውን የአፍሪካ ቀንድ ልጆች ፓስፖርትና ሰነድ በሌለበት መለየት እንደው ፈታኝ ነው፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ