1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀሐዬ አያሌው የስደት ጉዞ

ዓርብ፣ ሐምሌ 3 2007

በርካታ አፍሪቃውያን በሊቢያ በኩል የሜዲትራኒያንን ባሕር አቋርጠው ወደ አውሮጳ ተሰደዋል። ብዙዎቹ ሲሳካላቸው ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ደግሞ በረሀ መሀል ሞተዋል፣ ሌሎች ባሕር ውስጥ ሰምጠው ቀርተዋል። ፀሐዬ አያሌው፤ አውሮፓ ከገባ 11 ወር ሆነው።

https://p.dw.com/p/1Fvqh
Bildergalerie Rettung von Flüchtlingen durch deutsche Cargo schiffe im Mittelmeer
ምስል OOC Opielok Offshore Carriers

የፀሐዬ አያሌው የስደት ጉዞ

ፀሐዬ ከስድስት ዓመት በፊት ተወልዶ ካደገበት አዲስ አበባ ከተማ ፤ ሱዳን ላይ ስራ አግኝቶ ነበር በሕጋዊ መንገድ ከኢትዮጵያ የወጣው። ካርቱም ከተማ ላይ ለ5 ዓመታት ከሰራ በኋላ ከቀጣሪው ጋር ባለመስማማቱ፤ ቀጣሪው እሱን እና አብረውት የሚሰሩትን ሌሎች ኢትዮጵያውያን የኮንትራት ሰራቸኞች አገራቸው እንደሚመልሳቸው ይነግራቸዋል። በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ ጥሩ አማራጭ መስሎ ያልታየው ፀሐዬ ፤ በባልደረቦቹ ጋር ለመጥፋት ይወስናል።ያኔ ነበር የፀሀዬ መጨረሻው ያልታወቀው ጉዞ የጀመረው።

Flüchtlinge im Mittelmeer (Symbolbild)
ምስል picture-alliance/dpa/Bundeswehr/Hptm Kleemann

«ወደፊት መጓዝ ነው የታየኝ» ያለው ፀሐዬ ፤ ደላላ አፈላልጎ የሰሀራ በረሀን አቋርጦ ሊቢያ ለመግባት በተዘጋጀች መኪና ላይ ከጓደኞቹ ጋር ተጭነው ጉዞ ጀመሩ። በጉዞ ላይ የገጠመው ችግር የፀሐዬ የመጀመሪያ ፈተና ነበር። በመቀጠል ሊቢያ እንደገባ፤ አጋቾች እጅ ላይ ይወድቅ እና ገንዘብ እንዲያመጣ ይጠየቃል። ይህ ካልሆነ መደብደብ እና መገረፍ አይቀርለትም ነበር። ፀሐዬ ከቤተሰብ ገንዘብ ጠይቆ እስከሚላክለት ድረስ 13 ቀናት በአጋቾቹ እጅ ቆይቷል።

ፀሐዬ 94 ሰዎችን ባሳፈረች ትንሽ ጀልባ ተጭኖ ባህር ለማቋረጥ ጎዞ መጀመሩን ገልፆልናል። የአፍሪቃ ስደተኞቹ በኢጣሊያ የባህር ኃይል ተረድተው ወደ ኢጣሊያ ቢገቡም፤ ፀሀዬን ጨምሮ አንዛኞቹ በስፍራው መቆየት አልፈለጉም። ፀሐዬ ወደ ብሪታንያ ለመሄድ ቢፈልግም፤ አውሮፓ ሲገባም ብዙ መሰናክሎች እንዳሉ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀበትም። ከ 6 ወራት በላይ በጉዞ ላይ የነበረው ፀሐዬ በመጨረሻም በፓሪስ አድርጎ ጀርመን ገብቶ ጥገኝነት ጠይቋል። የጠበቀው የአውሮፓ ህይወት ግን ይህ አልነበረም።

የአፍሪቃውያን የባህር ስደት አሁን ድረስ እዚህ አውሮፓ ትልቅ ችግር ሆኗል። በተለይ ቁጥራቸው በርካታ ሰዎች ተገን እየጠየቁ በመሆኑ አውሮፓ ለስደተኞች የምታደርገው እንክብካቤ ከስደተኞቹ ፍላጎት ጋር አልመጣጠን እያለ ፤ ተስፋ ሲቆርጡ ይስተዋላል። የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ፤ በህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ላይ ጠንካራ ርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል። ይህ ለስደተኞች መቀነስ መፍትሄ ይሆን? ከጊዜ ጋር የሚታይ ይሆናል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ