1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀረ «ኤች አይ ቪ» ቅስቀሳ መቀዛቀዝ ያስከተለዉ ሥጋት፤

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 12 2008

ለመጀመሪያ ጊዜ ደቡብ አፍሪቃ ኤድስን የተመለከተ ጉባኤ በምድሯ ስታስተናግድ የሀገሪቱ መሪዎቹ የሰዉነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያዳክመዉ፣

https://p.dw.com/p/1JSFg
Ban Ki-moon und Charlize Theron auf der Pressekonferenz der International AIDS Conference 2016
ምስል picture-alliance/dpa

የፀረ HIV ቅስቀሳ እና ሥጋቱ

በምህፃሩ «ኤች አይ ቪ» የሚባለዉ ኤድስን ያስከትላል ወይ ሲሉ በመጠየቃቸዉ ተሰብሳቢዎቹን ማስደንገጡ ለታሪክ ተመዝግቦላቸዋል። በጉባኤዉ ላይ ቀርቦ ሕክምና ስለማግኘት እና የአካባቢዉ ሃገራት በሽታዉ ምን ያህል ሕይወት እየቀጠፈ መሆኑን እንዲረዱ ተማፅኖ ያቀረበ አንድ በኤድስ በኅታ ሰዉነቱ የሰለሰለ የ11 ዓመት አዳጊ ልጅ ወደመድረኩ ሲወጣም የያኔዉ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ታቦ ምቤኪ ከስብሰባዉ አዳራሽ ሹልክ ብለዉ ወጡ። «አትፍሩን፤ እኛም እንደእናንተዉ ነን፤» የሚል ድምጹን ያሰማዉ ጆሲ ጆንሰን በቀጣዩ ዓመት ወደማይቀርበት ዓለም በለሆሳስ አለፈ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም ደርባን ላይ በተካሄደዉ ጉባኤም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት ቀጣይ ዓመታት የደቡብ አፍሪቃ ባለስልጣናት በሽታዉን በተመለከተ በነበራቸዉ ግንዛቤ ምክንያት መድኃኒት ባለማቅረባቸዉ በሀገሪቱ ዉስጥ ከ330ሺህ በላይ ሕዝብ ማለቁን የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናት አሳይቷል። ለሁለተኛ ጊዜ የኤድስ ጉዳይ ተመራማሪዎች እና ተሟጋቾች ወደ ደርባን በዚህ ሳምንት ተመልሰዉ ዓለም አቀፍ ጉባኤ መገናኘታቸዉ ሀገሪቱ ከዓመታት ወዲህ ያሳየችዉ የአስተሳሰብ ለዉጥ ማሳያ እንደሆነ ነዉ የተነገረዉ።

Aids-Aktivist Nkosi Johnson
ደቡብ አፍሪቃዊ የAIDS ሰለባምስል AP

ዛሬ ደቡብ አፍሪቃ የፀረ «ኤች አይ ቪ»መድኃኒትና ሕክምና መርሃግብሯ ከዓለም ከፍተኛዉ መሆኑን መናገር ችላለች። መድኃኒቱን ለሕዝቧ ባለማቅረቧ 57 ዓመት ደርሶ የነበረዉ የዕድሜ ጣሪያ ወደ62,9 ዓመት ከፍ ብሏል። እንዲያም ሆኖ ደቡብ አፍሪቃ 6,8 ሚሊየን ሕዝቧ ተሐዋሲዉ በደሙ ስለሚገኝ በዚህ ረገድ ከዓለም ግንባር ቀደሟ ሀገር ሆናለች። ከእነዚህ መካከልም ገሚሱ ብቻ ነዉ ፀረ «ኤች አይ ቪ» መድኃኒት የሚያገኘዉ። ገንዘባቸዉን ለመድኃኒትም ሆነ ሕክምና አቅርቦቶች በመለገስ የሚታወቁት የማይክሮ ሶፍት መሥራት ቢል ጌትስ ይህን የሚያስተካክል ርምጃ ካልተወሰደ በቀር፤ እስካሁን ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ ሃገራት ተሐዋሲዉ የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ የተደረጉ ጥረቶች መና ሊቀሩ እንደሚችሉ በጉባኤዉ ዋዜማ አሳስበዋል።

ሰዎች ከበሽታዉ ራሳቸዉን እንዲጠብቁ የሚደረጉ ቅስቀሳዎች አሁን መቀነሳቸዉ ለሚታየዉ ችግር መንስኤ ከሚሆኑ ነገሮች አንዱ ሊሆን እንደሚችል የሚናገሩ አሉ።

እስከ የፊታችን ዓርብ በሚዘልቀዉ በ21ኛዉ የ«ኤድስ» ጉባኤ እንደተገለጸዉም እስከዛሬ በመላዉ ዓለም የHIVን ስርጭት ለመቀነስ የተካሄዱት እንቅስቃሴዎች ቀላይ የማይባሉ ዉጤቶች አስገኝተዋል። ያም ሆኖ ግን፤ በአሁኑ ጊዜ በተለይ ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ ሃገራት ዕድሜያቸዉ በ10 እና 19 ዓመት መካከል የሚገኙ አዳጊ ወጣቶችን ሕይወት በአጭሩ ከሚቀጥፉ በሽታዎች ዋነኛዉ «ኤች አይ ቪ»/«ኤድስ» እንደሆነ ተገልጿል።

Symbolbild HIV Medikamente Therapie UN
ፀረ HIV መድኃኒትምስል picture-alliance/dpa/L.Bo Bo

ከአፍሪቃ ሃገራት አኳያ ስትታይ «ኤች አይ ቪ»/«ኤድስ» የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ ባከናወነችዉ ተግባር የላቀ ዉጤት ኢትዮጵያ ማስመዝገቧም የፌደራል የ«ኤች አይ ቪ»/«ኤድስ» መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ፈይሳ ገልጸዉልናል። ደርባን ላይ ትናንት የተጀመረዉ 21ኛዉ ዓለም አቀፍ የ«ኤች አይ ቪ»/«ኤድስ»ጉባኤ ላይ የቀረቡ ዘገባዎች ምንም እንኳን የፀረ «ኤች አይ ቪ»መድኃኒት ተጠቃሚዎች ተበራክተዉ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ቢቀንስም ዛሬም በየዓመቱ 2,5 ሚሊየን ገደማ ሕዝብ በተሐዋሲዉ እንደሚያዝ አመልክተዋል። በአንድ ወቅት ብዙ ሲነገርለት ቢቆይም አሁን መቀዛቀዙ ችግሩ ተዳፍኖ ዉስጥ ዉስጡን ትዉልድ እንዲያቃጥል ዕድል ሊሰጠዉ እንደማይገባ አፅንኦት በመስጠት የሚናገሩት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ወገኖች፤ መገናኛ ብዙሃን ዛሬም ትኩረት እንዲሰጡት ያሳስባሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ