1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀናው የራይፍ በደዊ ብይንና ተቃውሞው

ረቡዕ፣ ሰኔ 3 2007

የሳውዲ አረቢያ ከፍተኛ ፍርድ በኢተርኔት ፀሃፊውና በሰብዓዊ መብት ተከራካሪው ራይፍ በደዊ ላይ ባለፈው ዓመት የተላለፈው ብይን እንዲፀና ያሳለፈው ውሳኔ ተቃውሞ ተሰንዝሮበታል ። እስልምናን ዘልፈሃል የተባለው በደዊ ከአንድ ዓመት በፊት ነበር የ10 ዓመት እሥራትና 1ሺህ የጅራፍ ግርፊያ የተፈረደበት ።

https://p.dw.com/p/1FejI
Raif Badawi Amnesty International Demo
ምስል Getty Images/AFP/T. Schwarz

[No title]

በደዊ የመጀመሪያውን የ 50 ጅራፍ ግርፊያ ከወራት በፊት ተቀጥቷል ። ግርፊያው በሚቀጥለው ሳምንት ይቀጥላል የሚል ስጋት አለ ።ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሳውዲ አረብያ ግርፋቱን እንድትሰርዝ ጠይቋል ።

የሳውዲ አረቢያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በራይፍ በደዊ ላይ ባለፈው ዓመት በግንቦት ወር የተላለፈው የቅጣት ፍርድ ህጋዊ ነው ሲል ነበር ፍርዱ እንዲፀና ትናንት የወሰነው ። ራይፍ ከእሥራትና ከግርፋት በተጨማሪ የ240 ሺህ ዶላር የገንዘብ ቅጣትም ተጥሎበታል፣ ለ10 ዓመታት ሃገሪቱን ለቆ እንዳይወጣም ተፈርዶበታል።ራያፍ እሥራት ግርፋትና የገንዘብ ቅጣት የተበየነበት እስልምናን በመዝለፉ የሃይማኖቱን ክብር በማወረድና በእስልምና በመሳለቁ፣ እንዲሁም የሃይማኖቱን ትዕዛዛት በመጣሱና ሃይማኖቱን በመካዱ ምክንያት መሆኑን ፍርዱን የሰጡት ዳኞች ውሳኔውን በሰጡበት ወቅት አስታውቀዋል ። የትናንቱን ብይን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስደንጋጭ በትር ብሎታል ። የድርጅቱ የሳውዲ አረብያ ና የባህረ ሰላጤው ሃገራት አስተባባሪ ሬጂና ሽፐትል ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ብይኑ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ መልዕክት ያስተላለፈ ነው ብለዋል ።

«በኛ ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ በራሳችሁ ጉዳይ ብቻ ተጨነቁ የሚል ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የተላለፈ መልዕክት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ለኢንተርኔት ፀሃፊውና እና ለሶሻል ሚዲያ ተጠቃሚውም የተላለፈ ምልክት ነው ።በሳውዲ ጥብቅ ቅድመ ምርመራ አለ ። ጋዜጦች ከመታተማቸው በፊት ይመረመራሉ ። አህን ደግሞ ኢትርኔቱን በእጃቸው ማስገባት ይፈልጋሉ ።እስካሁን በዚህ ረገድ የፈለጉትን ማድረግ አልቻሉም ።አሁን ራይፍ በደዊን እንደ ትልቅ ጥፋተኛ በመቅጣት ምልክት እያሳዩ ነው ። እናም መልዕክቱ እጃችሁን ከኢንተርኔት አርቁ፤ ትዊተር ፌስቡክ ኢንስታግራምና የመሳሰሉትን አትጠቀሙ ነው ።ከዚያ በኋላ የሚሆነውን እናያለን »

Backlashgroup #Backlash Kampagne Raif Badawi
ምስል Backlashgroup

ባለፈው መጋቢት መጨረሻ ላይ የበደዊ መጣጥፎች በጀርመንኛ ጭምር ተተርጉመው በኢንተርኔት ቀርበው ነበር ። በነዚህም ፅሁፎች በደዊ በሃያማኖቱ መሠረቶች ላይ ጠንካራ ሂሶችን ሰንዝሯል ። ሆኖም በፅሁፎቹ እስልምናን የሚያንቋሽሽ ነገር ለማግኘት ከባድ ነው ። «የአረቡን ዓለም ማህበረሰብ በጥሞና የሚከታተል ሰው» በሚል ርዕስ በደዊ ባቀረበው በአንድ ፅሁፉ ላይ የሃይማኖቱን አዋቂዎችን ቃል የሚቀበል በማጉረምረም ራሱን ሲጎዳ ይኖራል ፤ እነርሱም እሺ አሜን ብሎ የሚታዘዝላቸውን ሰው ነው የሚፈልጉት ሲል ፅፏል ። እርሱ ባሰፈራቸው በእንደዚህ ዓይነቶቹ ቃላት ሃይማኖታዊው የአባትነት ስሜት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል ። ይሁን እንጂ ይሄ የሚሰድብ ወይም የሚያዋርድ አይደለም ። ሆኖም በደዊ ከታሰረባቸውምክንያቶች አንዱ እስልምናን መዝለፍ ነው ። ሽፐትል እንዳሉት ይህን መሰሉ ክስ ሁሌም በአንድ መንገድ ነው የሚዳኘው ።

Kanada Saudi-Arabien Demonstration für Blogger Raif Badawi
ምስል picture-alliance/empics

«እስልምናን በማንቋሸሽ ክስ ሲቀርብ በሳውዲ አረቢያ ፍርድ አሰጣጥ አንቀጹ እንደተፈለገው የሚለጠጥ ነው ።በሁሉም ጉዳዮች ተመሳሳይ አተረጓጎም የሚሰጥበት ሁኔታም አለ ።»

በበደዊ ላይ እንዲፀና የተወሰነው ብይንከተለያዩ ወገኖች ተቃውሞ ገጥሞታል ። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፈረንሳይ እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስ በበደዊ ላይ የተላለፈው የ1ሺህ ግርፋት ቅጣት እንዲነሳ ጠይቀዋል ። የዋሽንግተን መንግሥት ሳውዲ አረብያ ግርፋቱን እንድትሰርዝና የበደዊንም ጉዳይ እንደገና እንድትመረምር ጠይቋል ። የራይፍ በደዊ ባለቤት ደግሞ ግርፋቱ በሚቀጥለው ሳምንት ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት አላት ። ከዛሬ ሶስት ዓመት አንስቶ በእስር ላይ የሚገኘው የ31 ዓመቱ በደዊ የሳውዲ ነፃ የኢንተርኔት ውይይት መረብ ከተባለው አምደ መረብ መስራቾች አንዱ ነው ። አምደ መረቡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተዘግቷል ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ