1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈላሾች የቤተሰብ ዕርዳታና ድህነትን የመቀነስ ድርሻው

ዓርብ፣ ነሐሴ 5 1998

በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ የታዳጊ ሃገራት ተወላጆች ሠርተው፤ ጥረውና ግረው ቤተሰብ ወዳጅን ለመደገፍ የሚልኩት ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ነው። ከአፍሪቃ እስከ ላቲን አሜሪካ ይሄው በአንዳንድ አገሮች በጀት ላይ ያለው ድርሻ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ይህ አንዱ፤ በደቡብ አፍሪቃ የአፓርታይዱ አገዛዝ ዘመን ቅርስ አንቆ የያዘው የቱሪዝም እንዱስትሪ አዝጋሚ ዕርምጃም ሌላው ርዕሳችን ነው።

https://p.dw.com/p/E0dc
የአፍሪቃ የረሃብ ገጽታ
የአፍሪቃ የረሃብ ገጽታምስል AP

እርግጥ መጠኑን በትክክል እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር አዳጋች ነው። ቢሆንም ብሪታኒያ ውስጥ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው መጤ ቤተሰቦች ገንዘብ በሚልኩባቸው ምርምሩ ባተኮረባቸው በአብዛኞቹ አገሮች ይሄው ገንዘብ ከውጩ ዓለምአቀፍ ቀጥተኛ መዋዕለ ነዋይ ያመዝናል። የብሪታኒያ ዜጎችም ሆኑ ባለሃብቶች ወደ ታዳጊው ዓለም የሚያሻግሩት መዋዕለ ነዋይ ያን ያህል አይደለም። ግን በሌላ በኩል በብሪታኒያ የሚኖሩ መጤዎችና ቤተሰቦቻቸው ወደ ትውልድ አገሮቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ድህነትን በመቋቋሙ በኩል የማይናቅ ክብደት እያገኘ ሄዷል። ጥናቱ እንዲካሄድ ያደረገው የብሪታኒያ ዓለምአቀፍ የልማት ተቋም ሚኒስትር ጌሬት ቶማስ ከእሢያና ከተቀረው ታዳጊ ዓለም የመነጨው በአገሪቱ የሚኖር መጤ አስተዋጽኦ ታላቅ መሆኑን ያረጋግጣሉ።

ለቤተሰብና ለወዳጅ ገንዘብ በመላክ ድህነትን መታገላቸውንም በብሪታኒያ አብዛኛው ሕዝብ በበጎ መንፈስ እንደሚረዳና እንደሚደግፈው ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ለዘመድ አዝማድ ወደ ታዳጊው ዓለም የሚላከው ገንዘብ ከሞላ-ጎደል በመላው ጥናቱ ባተኮረባቸው አገሮች ከውጩ ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ የላቀ ነው። እርግጥ የመዋዕለ-ነዋዩን መጠን በትክክል ለመናገር እምብዛም አያዳግትም። መጤዎች የሚልኩትን ገንዘብ መመዘኑ ግን አስቸጋሪ ነው። ሆኖም ዓለምአቀፉ የልማት ተቋም ተግባሩ ዛሬ ድህነትን በመቋቋሙ ረገድ ታላቅ ድርሻ እንዳለው አይጠራጠርም።
በዓለምአቀፍ ደረጃ መጤዎች ከያሉበት አካባቢዎች ወደ ትውልድ አገሮቻችው የሚልኩት ገንዘብ ግዙፍና ሰፊ ዕድገት የሚታይበት ነው። በወቅቱ በዓለምአቀፉ የፊናንስ እንቅስቃሴ አኳያ ከፍተኛ ድርሻ እየያዘና ከዚያም በላይ በተቀባዮቹ አገሮች የበጀት ሚዛን ላይ የበለጠ ወሣኝ እየሆነ ነው፤ ጥናቱ እንደሚለው። በዚህ መንገድ የሚላከው ገንዘብ ዛሬ በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ የታዳጊው ዓለም ቤተሰቦች ገቢ ማሻሻያ፤ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ዋስትናም ሆኗል። ጥናቱ የተካሄደው ዓለምአቀፍ ድርጅቶች፣ ለጋሽ ወይም አበዳሪዎችና ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች የያዙት የተቀናበረ ጥረት አንድ አካል ሆኖ ሲሆን ዓላማውም የመጤዎች የገንዘብ አቅርቦት ለልማት የሚኖረውን ጠቀሜታ ከፍ ለማድረግ እንዲቻል ጭብጥ መረጃዎችን ማግኘት ነው።

ለብሪታኒያ ዓለምአቀፍ ተቋም ጥናቱን ባለፈው ግንቦት ወር ያካሄደው ICM የተሰኘ ኩባንያ ለምርምሩ መሠረት እንዲሆነው በብሪታኒያ 143 በሚሆኑ አካባቢዎች ጥቁሮችና ውሁዳን የሕብረተሰብ ካፍላት ለሚገኙባቸው ቤተሰቦች መጠይቅ አቅርቦ ነበር። ከዚህም ቢያንስ በዓመት አንዴ ገንዘብ ለዘመዶቻቸው የሚልኩ 1778 ሰዎች የሰጧቸው መረጃዎች መልሰው ደርሰውታል። በዚሁ የመጠይቅ ውጤት መሠረት የመጀመሪያው መጤ ትውልድ ወደ ብሪታኒያ የፈለሰው በ 50ኛና በ 60ኛዎቹ ዓመታት በመሆኑ አዲሱ ትውልድ ከምንጭ አገሩ ትስስሩን እንዳያጣና ዕርዳታውም እንዳያቆለቁል የሚሰጉ አልጠፉም።

ሆኖም ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ አዋቂዎች በአንጻሩ ሂደቱ አዳጊ ነው፤ ይቀጥላል ባዮች ናቸው። መጤዎች ለወገን በሚልኩት ዕርዳታ ማደግ ተጠቃሚዎቹ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄደው ገንዘብ በማስተላለፍ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎችም ናቸው። በብሪታኒያ ተቀማጭ የሆነው Travelex የተሰኘ ኩባንያ ሃላፊ ሱራይ ቫጋኒ እንደሚሉት በዚህ መስክ የተያዘው ንግድ ያለማቋረጥ እያደገ ው። በብሪታኒያ፣ በአሜሪካም ሆነ በሌሎች በበለጸጉ አገሮች በትውልድ አገሩ የሚኖሩ ቤተሰቦቹን ገንዘብ በመላክ የሚደግፈው ቁጥር፤ የዕርዳታውም መጠን እየጨመረ ነው የሚሄደው።
ጥናቱ እንዳመለከተው የብሪታኒያ መጤዎች ከሃምሣ ወደሚበልጡ የተለያዩ አገሮች ገንዘብ አስተላልፈዋል። ይህም ከአሥር አራቱ ወደ አፍሪቃ ሲሆን ከላኪው ብዛት አንጻር ዋነኛዋ ተቀባይ ናይጄሪያ ነበረች። በሁለተኛ ደረጃ ሕንድ፣ ቀጥሎም ፓኪስታንና ጃሜይካ፤ ከዚያም 5 በመቶ ጋና! ግማሹ መጤ ገንዘቡን የላከው ደግሞ ለወላጆች ሲሆን ሩቡ ለሌላ በተ-ዘመድ፣ ጥቂቱም ማለት 5 በመቶ ገደማ የሚጠጋው ለሕጻናት ነበር። ለጓደኞች ገንዘብ የሚልከውም ያንኑ ያህል ያክላል።

ለመሆኑ በተቀባዮቹ አገሮች ገንዘቡ በምን በምን ተግባር ላይ ነው የሚውለው? አብዛኛው ገንዘብ 31 በመቶው በተቀዳሚ ለምግብ፣ ከዚያም 21 በመቶው የሕክምና ወጪንና ዘላቂ ግልጋሎት ያላቸው ቁሳቁሶችን የመሳሰሉ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ጥቅም ላይ ይውላል። ትምሕርትና መኖሪያም እያንዳንዳቸው 17 በመቶውን ያህል ድርሻ ይይዛሉ። እርግጥ ገንዘቡ በሥራ ላይ የሚውልበት መልክና መጠን ከአካባቢ ወደ አካባቢ የተለያየ ነው።
ለምሳሌ 40 በመቶው አፍሪቃውያን ከውጭ የሚላከው ገንዘብ በአብዛኛው ለምግብ ግዢ ተግባር ላይ ይውላል ሲሉ ሌሎች 24 በመቶ ደግሞ ለትምሕርት ወጪ ነው ባዮች ናቸው። በአንጻሩ 29 በመቶ ገደማ የሚጠጉ ቻይናውያን ገንዘቡ ይበልጡን ለአልባሣት ግዢ ሥራ ላይ እንደሚውል ነው የሚናገሩት። በአጠቃላይ አብዛኛው ተጠያቂ ወደ ምንጭ አገሩ የሚልከው ገንዘብ ከቤተ-ዘመዱ መተዳደሪያ 40 በመቶውን ያህል ድርሻ እንደሚይዝ ያምናል። ይህ ደግሞ ትክክለኛ ግምት ከሆነ የተቀባዩን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻሉ በኩል የሚኖረው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው።

በብሪታኒያ ለታዳጊው ዓለም ዘመዶቹ ገንዘብ ከሚልከው መጤና ቤተሰቡ 34 በመቶው አፍሪቃዊ፣ 31 በመቶው የደቡብ እሢያ ዝርያና 17 በመቶው ደግሞ የካራይብ ምንጭ ያላቸው ጥቁሮች እንደሆኑም ጥናቱ ያመለክታል። ገንዘብ ላኪውም በጾታ ሲነጻጸር ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ጥቂት የሚያመዝኑበት ሲሆን ሴቶች የላቀ ድርሻ ያላቸው በአፍሪቃ ብቻ ነው።

እርግጥ በበለጸገው ዓለም የሚኖሩ መጤዎች የገንዘብ ማሻገር ተግባር የብሪታኒያው ጥናት በዚህ መልክ ባይመለከተውም በቤተ-ዘመድ ዕርዳታ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ብዙዎች በተለያዩ የንግድ ተግባራት የሚሳተፉ መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎችም ናቸው። በቱሪስትነት ለአዳጊ የትውልድ አገሮቻቸው የውጭ ምንዛሪ ጠቃሚ ምንጮች እየሆኑም ሄደዋል። ይህ ሁሉ ተጣምሮ ሲታሰብ መጤውም ሆነ እንበል የውጩ ሰፋሪ በታዳጊ አገሮች ታላቅ የገንዘብ ምንጭ መሆኑ ነው።

ወደ ሁለተኛው ርዕሳችን ሻገር እንበልና ደቡብ አፍሪቃ በመሠረቱ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ መስፋፋት ባመቸ ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋ የታደለች አገር ናት። ቢሆንም አገሪቱ ከዚህ የኤኮኖሚ ዘርፍ የሚገባውን ያህል እየተጠቀመች ነው ለማለት አይቻልም። እርግጥ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአፓርታይዱ አገዛዝ ከተወገደ ወዲህ ባሉት ባለፉት 12 ዓመታት የደቡብ አፍሪቃ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከእጥፍ በላይ ዕድገት አሣይቷል። በዚሁ ጊዜ ከዓለም ዙሪያ ወደ አገሪቱ የተጓዘው የውጩ ጎብኚ እስካለፈው 2005 ዓ.ም. ድረስ ከ 3.6 ወደ 7.3 ሚሊዮን ከፍ ብሎ መገኘቱ ነው የሚነገረው።

የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት እንደሚለው ይህም ባለፈው ዓመት ከአገሪቱ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት 8 በመቶውን ድርሻ ሊይዝ የበቃ ነበር። የ 19 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ገቢ ያስገኘው ንግድ አንድ ሚሊዮን ለሚሆን ሕዝብ የሥራ መስክ እንዲከፈትም ረድቷል። ግን የአፓርታይድን ጎጂ ቅርስ ለማስወገድ በምትጥረው አገር ይህ ያን ያህል የስኬት ታሪክ ሆኖ ሊታይ የሚችል አይደለም። ዛሬም ከንብረት ባለቤትነት በሰፊው እንደተገለለ ያለው ብዙሃኑ ጥቁር ሕዝብ የቱሪዝሙ ገቢ ተጠቃሚ ሆኖ አይገኝም። የአብዛኛው ሃቅ ዛሬም የቀጠለው ድህነቱ ነው።

የደቡብ አፍሪቃን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሚያንቀሳቅሱት ንብረት ያላቸውና የወረሱ፤ በብዛትም እንደ ጥንቱ ጥቁር ያልሆኑ ደቡብ አፍሪቃውያን ናቸው። ርስታቸውንና የእርሻ መሬታቸውን ወደ መዝናኛ ቦታነት፤ ቤቶቻቸውንም ወደ እንግዳ ማረፊያ በመለወጥ ይነግዳሉ። የአፓርታይዱ ዘመን ተጨቋኞች ግን የቱሪዝሙን ንግድ ለመቀላቀል የሚረዳ ይህን መሰል ንብረት የላቸውም። አላቸው ከተባለም ገቢው እጅግ ዝቅተኛ በሆነባቸው መንደሮች ታውንሺፕስ የተወሰነ ነው። እነዚሁ ታውንሺፕስ በመባል የሚታወቁ የአፓርታይዱ ዘመን የጥቁሮች መኖሪያ መንደሮች ዘረኛው አገዛዝ ከታላላቆቹ ከተሞች ውጭ የከለላቸው ነበሩ። ታዲያ ዛሬም ተስማሚው የአልግሎት መዋቅር ያልተስፋፋባቸው ድሃ አካባቢዎች እንደሆኑ ናቸው።

የጥቁሮች ንብረት-አልባነት እርግጥ በቱሪዝሙ መስክ ብቻ ሣይወሰን በአጠቃላዩ የደቡብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ዘርፍ የሚንጸባረቅ ሃቅ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ይህም ለዓመታት የጥቁሮችን የእንቅስቃሴ መብት ገትቶ፣ የትምሕርት፣ የጤናና ሌሎች አገልግሎቶችንም ነፍጎ የኖረ የዓመታት ዘረኛ ፖሊሲ ውጤት ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ሥራ የማግኘት ዕድላቸውንና ገቢያቸውን የማሻሻል ዕድላቸውንም ዝቅ አድርጎት ነው የኖረው። ይህ ደግሞ የግድ መለወጥ ይኖርበታል።

የፕሬቶሪያው መንግሥት እርግጥ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ አንዳንድ ዕርምጃዎችን ለማንቀሳቀስ መጣሩ አልቀረም። ጥቁሮች የቱርዝሙን ኢንዱስትሪ ዘርፍ እየተቀላቀሉ መሄድ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማቃለል አስፈላጊውን ሁኔታ ማመቻቸቱ አጣዳፊ ጉዳይ እንደሆነ ከመቼውም በላይ ታምኖበታል። የአገሪቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ቼዲሶ ማቶና በቅርቡ እንዳስረዱት የተለያዩ ተቋሟት ከሚያደርጉት የገንዘብ ድጎማ ባሻገር ንግዱን የመቀላቀሉን ሁኔታ የሚያቃልል ሥልጠና የመስጠት ዕቅድ አለ።

በአጠቃላይ የደቡብ አፍሪቃን ብዙሃን ጥቁሮች የኤኮኖሚ ሃይል የማሳደጉ የመንግሥቱ የፖሊሲ ጥረት የቱሪዝሙን ዘርፍ ገጽታም እየለወጠ እንደሚሄድ ነው የሚታመነው። በመንግሥቱ ፖሊሲ መሠረት አፓርታይድ ካስከተላቸው ችግሮች ለመላቀቅ ጥቁሮች በኤኮኖሚው ዘርፍ የሚኖራቸው ተሳትፎ በተለያየ መንገድ መጠናከር ይኖርበታል። የንብረት ባለቤት ለመሆን መብቃት አለባቸው፤ በከፍተኛ የአስተዳደር መድረኮች ላይ የሚኖራቸው ድርሻም መጨመሩ ግድ ነው። በዘር ምንጭ የተነሣ ሰፍኖ የቆየው ልዩነት የግድ መወገድ ይኖርበታል።