1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈረንሳይ ፖሊስ ተቃውሞ እና የተሰነዘረበት ጥቃት

ሐሙስ፣ ግንቦት 11 2008

ትናንት ፓሪስ ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ ባካሄዱ የፖሊስ መኮንኖች ላይ ጥቃት ያደረሱት ከባድ ቅጣት እንደሚጣልባቸው የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ ። ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል ባልስ RTL ለተባለው ራድዮ ጣቢያ ዛሬ በሰጡት ቃለ ምልልስ ቅጣቱ ይጠናከራል ከማለታቸውም በላይ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑንም ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/1Iqj7
Paris Frankreich Gewalt gegen Polizei brennendes Polizeiauto
ምስል Reuters/C.Platiau

[No title]

በጥቃቱ የተጠረጠሩም መታሠራቸውን አስታውቀዋል። በሌላ በኩል መንግሥት ይፋ ባደረጋቸው የሥራ ደንቦች ማሻሻያ ላይ የሚካሄደው ተቃዋሞ ቀጥሏል። ትናንት ፓሪስ ውስጥ ፀረ ፖሊስ እንቅስቃሴዎችን በመቃወም ሰልፍ በወጡ ፖሊሶች ላይ የተሰነዘረው ጥቃት እያነጋገረ ነው። በዚሁ ዕለት የፖሊሶቹን ሰልፍ በመቃወም በተካሄደ ያልተፈቀደ ሰልፍ የተካፈሉ ሰልፈኞች አንድ የፖሊስ መኪና ሰባብረው ፈንጂ ወርውረውበት እንዲቃጠል ማድረጋቸው ባለሥልጣናትን አስደንግጧል አስቆጥቷልም። ፈንጂው ሲወረወር መኪናው ውስጥ የነበሩ ሁለት ፖሊሶች መኪናው ከመቃጠሉ በፊት ማምለጥ ችለዋል።
አቃቤ ሕግ የግድያ ሙከራ ባለው በዚህ ጥቃት ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል። የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒሥትር ቤርናር ካዘነቭ እስካሁን በድርጊቱ የተጠረጠሩ 4 ሰዎች መታሠራቸውን ፣ ሌሎች ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች ይያዛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል ባልስ በጥቃት አድራሾቹ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል። ፖሊስ ትናንት በመላው ፈረንሳይ የተቃውሞ ሰልፍ ያካሄደው መንግሥት ያቀረበውን የሥራ ደንቦች ማሻሻያን በመቃወም ከቅርብ ወራት ወዲህ በሚካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ፣ በፖሊስ ላይ የሚንፀባረቁ ጥላቻዎችን እና የሚደርሱ ጥቃቶችን በመቃወም ነበር። የፓሪስ ፖሊስ ኃላፊ ሚሼል ካዶት እንደተናገሩት ካለፈው መጋቢት አንስቶ በተካሄዱ 60 ያህል በሚሆኑ የተቃውሞ ሰልፎች ከ200 የሚበልጡ ፖሊሶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ምንም እንኳን ፖሊስ በሕዝቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም ፀረ መንግስት የተቃውሞ ሰልፎች መካሄድ በጀመረበት በመጋቢት ሁለት ፖሊሶች አንድ የ15 ዓመት ልጅ ሲደበድቡ የሚያሳይ ቪድዮ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ከተሰራጨ በኋላ ጥላቻው ተጠናክሮ ቀጥሏል። የግራ ክንፍ ፖለቲከኞችም መንግሥት ተቃውሞዎችን የሚያስተናግድበትን መንገድ ክፉኛ እየተቹ ነው። የትርፍ ሰአት ክፍያ ማካካሻ፣ የበአላት ክፍያ እና ሠራተኞችን ማባረርና ቅጥርን የተመለከተው አዲሱ የሥራ ደንቦች ማሻሻያ ላይ የሚካሄደው ተቃውሞ ቀጥሏል። በፓሪሱ ፕላስ ደ ላ ሪፐብሊክ ከቀጠሉት ሰልፎች በአንዱ ላይ የተካፈሉት እኚህ መምህርት ለውጥ እንዲመጣ ተቃውሞ አስፈላጊ ነው ይላሉ።
«አብዮቱን እፈልገዋለሁ። ስርዓታችንን መቀየር ኃላፊዎቹንም ማባረር አለብን። እነሱን ከሥልጣን አንስተን እንዴት መሥራት እንዳለብን ራሳችን መወሰን ይኖርብናል።»
የሥራ ደንብ ማሻሻያዎችን የሚቃወሙ ሰልፎችን ከሚጠሩት መካከል አንዳንድ የሠራተኛ ማህበራት ይገኑበታል። ከመካከላቸው አንዱ ጋይል ክዊራንተ የሚመሩት የሠራተኛ ማህበር ነው። ክዊራንተ እንደሚሉት ተቃውሞ ከቀጠለ መንግሥት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መውደቁ አይቀርም።
«እዚህ የሚሆነው ነገር ትኩረት የሚስብ ነው። የሚታየው በመጠኑ ቢሆን ያስፈራል። ለጉዳዩ ክብደት ለመስጠት በተማሪዎች፣ በመብት ተሟጋች እና በሠራተኞች መካከል ኅብረት መፍጠር ያስፈልጋል። ይህ ከተሳካ ደግሞ ተቃውሞው በዚህ አይቆምምና መንግሥት ከአሁኑ ለባሰ ችግር ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል።»
ይሁንና መንግሥት ሥራ አጥነት እንዲቀንስ ይረዳል በሚለው በዚህ ማሻሻያ እንደሚገፋ ነው ያስታወቀው። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ሕጉን በሚመለከት ሃሳባቸውን እንደማይቀይሩ ደጋግመው አስታውቀዋል። ኦሎንድ እንደሚሉት ረቂቅ ሕጉ ክርክር ተካሂዶበት፣ ስምምነት ላይም ተደርሶ የፀደቀ በመሆኑሥራ ላይ መዋሉ አይቀርም። አዲሱ የሥራ ደንብ ማሻሻያ ፣ የሕዝብ ድጋፋቸው ከቀድሞው በባሰ እየቀነሰ ለሄደው ለፕሬዝዳንት ኦሎንድ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን መመረጥ አለመመረጥ ፣ ወሳኝ እንደሚሆን ይገመታል።

Frankreich Marseille Proteste Arbeitsmarktgesetz
ምስል picture-alliance/AP Photo/C. Paris
Frankreich Protest Arbeitsmarktreform Ein Mann mit Tshirt im Tränengasnebel
ምስል Reuters/G.Fuentes

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ