1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍልስጤማውያን የስለት ዐመፅ በእሥራኤል

ሐሙስ፣ ጥቅምት 11 2008

እሥራኤል ውስጥ ፍልስጤማውያን የተለያዩ ስለታማ መሣሪያዎችን በመጠቀም በእሥራኤላውያን ላይ የሚያካሂዱት ዐመፅ ዛሬም እንደቀጠለ ነው። የእስራኤል ወታደሮችም በአፀፋው ጥቃት አድራሾችን ተኩሰው መግደላቸውና ማቁሰላቸውም አልቆመም።

https://p.dw.com/p/1GsrR
Israel Messerattacken
ምስል Getty Images/AFP/M. Abed

[No title]

በዛሬው እለትም እየሩሳሌም ውስጥ በአንድ አውቶብስ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲሞክሩ ነበሩ የተባሉ ሁለት ፍልስጤማውያንን የእስራኤል ወታደር ተኩስ ከፍቶ አንዱ ሲገደል፣ ሌላው በፅኑዕ ቆስሏል። በሌላ በኩል ባለፈው እሁድ በስህተት ተገድሏል የተባለው ኤርትራዊ ትናንት ቴላቪቭ ውስጥ በተካሄደ የሻማ ማብራት ስነስርዓት ተዘክሯል።
እሥራኤል ውስጥ ፍልስጤማውያን በእሥራኤላውያን ላይ የሚያካሂዱት የጩቤ አመፅ ዛሬም እንደቀጠለ ነው ። የእስራኤል ወታደሮችም በአፀፋው ጥቃት አድራሾችን ተኩሰው መግደላቸውና ማቁሰላቸውም አልቆመም ።በዛሬው እለትም እየሩሳሌም ውስጥ በአንድ አውቶብስ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲሞክሩ ነበሩ በተባሉ ሁለት ፍልስጤማውያን ላይ የእስራኤል ወታደር ተኩስ ከፍቶ አንዱ ሲገደል ፣ሌላው በፅኑ ቆስሏል ። በሌላ በኩል ባለፈው እሁድ በስህተት ተገድሏል የተባለው ኤርትራዊ ትናንት ቴላቪቭ ውስጥ በተካሄደ የሻማ ማብራት ስነስርዓት ታስቧል ። ፍልስጤማውያን እስራኤል ውስጥ የጩቤ አመፅ ከጀመሩ 22 ቀናት ተቆጥረዋል ። በነዚህ ጊዜያት በተለያዩ የእስራኤል ከተሞች ፍልስጤማውያን በእሥራኤላውያን ላይ ባደረሱት የስለት ጥቃት እና የእሥራኤል ወታደሮችም በአፀፋው በወሰዷቸው እርምጃዎች ህይወታቸው ያለፈው ቁጥር ወደ 60 ተጠግቷል ።ከመካከላቸው 49 ኙ ፍልስጤማውያን ፣9ኙ ደግሞ እስራኤላውያን ናቸው ። ከሟች ፍልስጤማውያን 25 ቱ ጥቃት አድራሾች ናቸው ። በዚህ ጥቃትና አፀፋ ጥቃት በስህተት የተገደሉም አሉ ። የእሥራኤል ወታደሮች በስህተት ገደሏቸው ከተባሉት መካከል አንድ እሥራኤላዊ አይሁድና አንድ ኤርትራዊ ይገኙበታል ። የዶቼቬለ የእየሩሳሌም ዘጋቢ ዜናነህ መኮንን እንደሚለው ፖሊስ ሲያዩ መደናገጥና የቆዳ ቀለም መመሳሰል ለዚህን መሰሉ አደጋ ያጋልጣል ።
ባለፈው እሁድ የእስራኤል ወታደር ቤርሸባ በተባለች ከተማ ተኩሶ የገደለውይኽው ኤርትራዊ ነፍሱ ከመውጣቱ በፊት ተመቶ በወደቀበት ፣ በአካባቢው ተሰባስበው በነበሩ ሰዎችም ተመቷል ።ሆስፒታል ከገባ በኋላ ህይወቱ ያለፈውን ኤርትራዊ በመምታት የተጠረጠሩ 4 ግለሰቦች ተይዘው በዋስ ተለቀዋል ። ዛሬ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡም ተነግሯል ።ባለፈው እሁድ ህይወቱ ያለፈውን ኤርትራዊ ለመዘከር ትናንት ምሽት ቴላቪቭ ውስጥ የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት ተካሂዷል ።በ20 ዎቹ መጨረሻ የእድሜ ክልል ውስጥ ይገኝ የነበረው ይኽው ኤርትራዊ እሁድ እለት ቤርሸባ ከተማ ማዕከል በሚገኝ አውቶብስ ጣቢያ ነው አደጋው የደረሰበት ። እንድ በድዊን እስራኤላዊ እዚያ በቆሙ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፍቶ ሰዎችንም በስለት ከወጋ በኋላ በአካባቢው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ኤርትራዊው የጥቃት አድራሹ ግብረ አበር መስሏቸው እንደተኮሱበት ተዘግቧል ።
ለፍልስጤማውያን ፣3ሳምንታት ለዘለቀው አመጽ ምክንያቱ የእየሩሳሌሙን የአልአቅሳ መስጊድ እሥራኤል እላፊ ሄዳ ቀስ በቀሰ የመጠቅለል አዝማሚያ እያሳየች ነው የሚል ነው ።ይህ ምክንያት ሆኖ በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት አንድ የተጀመረው የስለት ጥቃት እሥራላውያንን አስበርግጓል ። ዜናነህ አሁን እሥራኤል ውስጥ ያለውን ሁኔታ ከጦር ሜዳ ጋር አመሳስሎታል ።
በስለት ጥቃቱ መዘዝ ህይወት ከመጥፋቱና ሰዎችም ከመቁሰላቸው በተጨማሪ ጥቃቱና የአፀፋ ጥቃቱ በእስራኤልና በፍልስጤማውያን ኤኮኖሚ ላይ ያሳደረው ተፅእኖም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ።
የእስራኤል ፍልስጤማውያን ግጭትን ለማስቆም የመፍትሄ ፍለጋው ጥረት ቀጥሏል ። ባለፈው ማክሰኞ እስራኤል የሄዱት የተመድ ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን ሰላም ለማውረድ ሁለቱ ወገኖች ፈጥነው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበው ነበር ። የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪም እንዲሁ በርሊን ጀርመን ውስጥ የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚኒን ነታንያሁን በጉዳዩ ላይ አነጋግረዋል ። ዜናነህ እንደሚለው ግን መፍትሄው ያለው በእሥራኤልና በፍልስጤማውያን እጅ ውስጥ ነው ።

Israel Messerattacken
ምስል Getty Images/AFP/M. Abed
Israel Gewalt Ausschreitungen Hawara Checkpoint Nablus
ምስል Reuters/A. Talat

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ