1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍቅረኛሞች ቀን አከባበር በአዲስ አበባ

ዓርብ፣ የካቲት 7 2006

እጎአ የካቲት 14 ቀን ማለትም ዛሬ በተለይ በምዕራብ ሀገራት የፍቅረኛሞች ቀን ይከበራል። በአዲስ አበባ እና አካባቢዋም ከአመት ዓመት ቀኑን የሚያከብሩት ፍቅረኛሞች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ወጣቶቹ የት እና እንዴት ያከብሩታል? አከባበሩ ምን ይመስላል?

https://p.dw.com/p/1B8Dv
Bildergalerie Valentinstag Vorbereitungen
ምስል Getty Images/Afp/Indranil Mukherjee

የፍቅረኛሞች ቀን ወይም «ቫለንታይንስ ደይ» በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ይከበራል። «ቫለንታይንስ ደይ» የሚለው ቃል የመጣው በ3ኛው ክፍለ ዘመን በዛሬይቱ ኢጣሊያ ቫለንታይን ተብለው በሚጠሩ ሰው አማካኝነት ሲሆን እኝህም ሰው በወቅቱ ለፍቅረኛሞች ከግቢያቸው አበባ እየቆረጡ ይሸልሙ በተለይም በጊዜው በሮማ ንጉስ ክልክል በነበረው በክርስትና ዕምነት መሰረት ፍቅረኛሞችን በጋብቻ ያስተሳስሩ እንደነበር ይነገራል። በዚህም ምክንያት ዳግማዊ ንጉስ ክላውዲዮስ ፤ ቫለንታይንን የካቲት 14 ቀን 269 ዓም ሮም ላይ በሞት መቅጣታቸው ተገልጿል። ይሁንና ከ200 ዓመት በኋላ ቫለንታይን ቅዱስ ተብለው በንጉስ ጌላሲዪስ ተሰየሙ። ቀስ በቀስም ቀኑ የፍቅረኛሞች ቀን እየሆነ ሄደ። ዛሬ በብዛት ፍቅረኛሞች አበባ እና ጣፋጭን ከፍቅረኛቸው ጋር በመለዋወጥ ያሳልፉታል።

Valentinstag Vorbereitungen in Holland
ቀይ ፅጌሬዳ በብዛት ወንድ ለሴት አፍቃሪው በዚህ ቀን የሚያበረክትላት የአበባ አይነት ነውምስል Reuters

በዚህ በፍቅረኛሞችቀን ለምሳሌ ሴት ጃፓናውያን ለፍቅረኞቻቸው ቸኮላት በስጦታ መልክ ሲያበረክቱ ይህ በሆነ በወሩ « ኃይት ደይ» ወይም ነጭ ቀን ይሉታል፤ ወንዶቹ ደግሞ ነጭ ቸኮላት ያበረክቱላቸዋል። ወደ ብራዚል ያመራን ከሆነ ደግሞ ይህ ቀን እንደ ምዕራብ ሀገራት የካቲት 14 ሳይሆን በጎርጎሮሲያውያኑ ሰኔ 12 ይከበራል። ወደ ምዕራብ ሀገራት ስንመጣ በኢጣሊያ የፍቅረኛሞችንቀን ፤ ፍቅረኛሞች ወንዝ ወይም ውሃ ወዳለበት ድልድይ በመሄድ በቁልፍ ጋን ላይ ስማቸውን እና ቀን የመሳሰሉትን በመፃፍ ቁልፉን አቅራቢያቸው ባለ የድልድይ ብረት ላይ በመቆለፍ ሁለቱም ፍቅረኛሞች ተመኝተው የቁልፉን በክፈቻ ወደ ውሃ ይወረውራሉ። የተመኙትን እያንዳንዳቸው ጮክ ብለው ባይናገሩም ለዘላለም የማያልቅ ፍቅርን መመኘታቸው አይቀሬ ነው። ወደ ፊንላንድ የሄድን እንደሆን «ቫለንታይንስ ደይ» እንደ ጓደኛሞች ቀን ነው ታስቦ የሚውለው። በብዛት ደስ የሚላቸውን ሰው በድብቅ የደስታ መግለጫ ካርድ በመላክ ለዛ ሰው ያለቸውን ፍቅር እና አክብሮት ይገልፃሉ። ከዛ ያለፈ ስጦታ ግን አይለዋወጡም።

ይህ ቀን በዚህ በጀርመን ብዙ ትርጉም እያገኘ የመጣው የአበባ እና የጣፋጭ ነጋዴዎች ብዙ ማስተዋወቂያ ስላደረጉ እንደሆነ ይገለፃል። እንዲህ እንዲህ እያለ የምዕራቡ ዓለም የፍቅረኛሞች ቀን አፍሪቃ ደረሰ። በደቡብ አፍሪቃ ለምሳሌ ፍቅረኛሞች አደባባይ ወጥተው ነጭ እና ቀይ ልብስ አድርገው ያከብሩታል። ነጭ ግልፅነትን ሲያመላክት ቀይ ደግሞ ፍቅርን ለመግለጫ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀኑ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ በሚስተዋልበትስ አዲስ አበባ ደግሞ ቀኑ እንዴት እንደሚታሰብ የአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ማህሌት ገልፃልናለች።

አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ቀን ሴቷ ያላሰበችውን ወይም ያልጠበቀችውን ነገር ለማድረግ ወንዱ ላይ የሚጣልበት ጫና ከፍተኛ ነው። ማህሌት ጊዜ ኖሯት በሰፊውም ባይሆን የዛሬውን ምሽት ከፍቅረኛዋ ጋር ለማሳለፍ አስባለች።

Vorbereitungen für Valentinstag im Irak
የፍቅረኛሞች ቀን በኢራቅምስል DW/M. Al-Saidy

ሌላው በአዲስ አበባ የሚኖረው አብይ የፍቅረኛሞችን ቀን ባለፉት አመታት ሲያከብር ቆይቷል። የዘንድሮውን ግን ትንሽ ለየት ይላል። ከፍቅረኛው ጋር ተለያይቷል። ቀኑን ግን ለማክበር ወስኗል።ይህ ቀን ለአንዳንድ የአልባሳት እና አበባ መሸጫ ቤቶች ከፍተኛ የገቢ ማስገኛ ቀን ነው። ሽመልስ ፤ በአዲስ አበባ የሴቶች የልብስ መደብር አለው። ወጣቱ እንደገለፀልን ገበያው ደርቷል። እንደውም «ከአቅርቦታችን ከሰው ከፍላጎት ጋር ሊመጣጠን አልቻለም» ይላል።

ምንም እንኳን ይህ ቀን በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ በሚገኙ በበርካታ ወጣቶች ዘንድ ቢከበርም፤ ሁሉም የፍቅረኛሞች ቀን በሚከበርበት ልማድ አይስማማም። ለምሳሌ በፌስ ቡክ ከታምሩ የደረሰን አስተያየት አለ፤ «እኔ የማውቀው ዘመን አመጣሽ መሆኑን ነው። አገር ውስጥ ያልነበረ፤ አካሄዱ ወደ ባህል አጥፊነት እንደ ሰደድ እሳት ተጓዥ ነው እላለሁ» ብሏል።እያሱ ደግሞ « ስንቱን ቀን እናክብር ተዉን አቦ እኛ ለራሳችንም ኑሮ ከብዶናል።» ነው ያለው።በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ በሚገኙ በበርካታ ወጣቶች ዘንድ ስለሚከበረው የፍቅረኛሞች ቀን ሙሉ ዝግጅቱን ከዚህ በታች በድምፅ ያገኙታል።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ