1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍቅረኛሞች ቀን ዜናዎች

ዓርብ፣ የካቲት 6 2007

እጎአ የካቲት 14 ቀን ማለትም ነገ በየአመቱ የፍቅረኛሞች ቀን ወይም «ቫለንታይንስ ደይ» ይከበራል። ይህ ቀን በምዕራቡ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ዘንድም በደማቅ መከበር ከጀመረ ሰነበተ።

https://p.dw.com/p/1EaKH
Valentinstag in Paris
ምስል picture alliance/abaca

በተለይ የዘንድሮው የፍቅረኛሞች ቀን ወይም «ቫለንታይንስደይ»ቅዳሜ ዕለት መዋሉ፤ ቀኑን ለሚያከብሩ ፍቅረኛሞች ዘና ብለው እንዲውሉ እድል ፈጥሮላቸዋል። የፍቅረኛሞች ቀን በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ይከበራል። ዕለቱን በርካቶች አበባ እና ጣፋጭ ከፍቅረኛቸው ጋር በመለዋወጥ ያሳልፉታል። የጀርመን ቋንቋ ተንከባካቢ ማህበር ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው፤ ጀርመን ውስጥ በብዛት ተወዳጅነት ካተረፉ የመጠሪያ ስሞች መካከል ለወንድ ቫለንታይን ለሴት ደግሞ ቫለንቲይና የሚሉት ስሞች ናቸው። የስሙ ተወዳጅነት እየጨመረ የመጣው ቅዳሜ ዕለት የሚከበረው የፍቅረኛሞች ቀን እውቅናን እያገኘ በመምጣቱ ይሆናል ሲል ማህበሩ ገልፃል። ማህበሩ እኢአ 2013 ዓም በመዘገባቸው የመጠሪያ ስሞች መዘርዝር ላይ ቫለንታይን 52ኛውን ስፍራ ሲያገኝ ፤ የሴቶቹ መጠሪያ ደግሞ 63ኛውን ስፍራ ይዟል። ቫለንታይን የሚለው ቃል ከላቲን « ቫለስ» ከሚለው ቃል የመነጨ ሲሆን ትርጉሙም ጤነኛ እና ጠንካራ እንደማለት መሆኑ ተገልጿል።

የፍቅረኛሞች ቀን በተለይ በሮም ከተማ የሚያከብሩ ፍቅረኛሞችያለ የሮማ ካቶሊካዊት ርእሰ ሊቃነ ጻጻሳት ፍራንሲስ ምርቃት እና ቡራኬ ቀኑን ማክበር ግድ ይላቸዋል። የቫቲካን ምክር ቤት ረቡዕ ዕለት እንዳስታወቀው፤ ቅዳሜ ዕለት ከፍራንሲስ ጋር እንደ አምናው አይነት አከባበር አይኖርም ሲል ገልጿል።ነገር ግን ጥንዶች መልዕቶች ፣ ፎቶ እና ቪዲዎቾች መላክ ይችላሉ ተብሏል።

Valentinstag
ምስል Fotolia/detailblick

ባለፈው ዓመት በሮም የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከ 30 ሀገራት የተውጣጡ 15 000 የሚደርሱ ወጣት ጥንዶች በተሰበሰቡበት ርዕሰ ሊቃነ-ፃፃሳት ፍራንሲስ ተገኝተው ቡራኬ ሰጥተዋል።

በጀርመን በዚህ የፍቅረኛሞች ቀን የአበባ እና የጣፋጭ ነጋዴዎች ብዙ ማስተዋወቂያ አስቀድመው ያደርጋሉ።በዚህም ቀን ለብዙዎች አበባ መለዋወጥ አይቀሬ ሆኗል። ባለፈው አመት ብቻ ጀርመን ለዚሁ ቀን ስትል 122,5 ሚሊዮን ፅጌሬዳዎች ከሌሎች ሀገራት ገዝታ አስገብታለች። የጀርመን ፌደራላዊ ስታትስቲክስ ጽህፈት ቤት፤ በታሪክ ይህን ያህል ፅጌረዳዎች በየካቲት ወር ወደ ጀርመን ገብተው አያውቅም ሲል ነው የገለፀው። አብዛኛዎቹን አበቦች ለጀርመን የሸጠችው ሀገር ደግሞ ጎረቤት ሀገር ኔዘርላንድስ ናት። 86,2 ሚሊዮን ፅጌረዳዎች በመሸጥ ከ 70 ከመቶው በላይ ግብይትን ሸፍናለች። ከ20 ሚሊዮን በላይ ፅጌረዳዎቿን ወደ ጀርመን በመላክ ደግሞ ኬንያ በሁለተኛነት ስፍራ ተቀምጣለች።

በዚሁ ቀን በርካታ ፍቅረኛሞች ከሚለዋወጡት ቀይ ፅጌሬዳ ባሻገር የፍቅር ምልክት የሆነው ቀይ የልብ ምልክት ነው። ከደብዳቤ፤ ከአሻንጉሊት ፣ ከጌጣ ጌጥ ማስቀመጫ ፤ ብቻ ከየቦታው የልብ ምልክት አይጠፋም። ልብ የፍቅር ምልክት ከሆነ በታሪክ ቆይቷል። « በህዝብ እምነት ልብ ማዕከላዊ ስፍራ የያዘ ነው ያሉት የምልክቶች ተመራማሪ የነበሩት ማንፍሪድ ሉርከር ። ሉክነር ልብ ከአንድ ሰው የውጭ ገፅታ ይልቅ ፤ አጠቃላይ የውስጥ ገፅታውን ይገልፃል ነበር ያሉት። ለጥንት ግብፃዊያን ፤ ልብ፦ የአእምሮ ፣ የፍላጎት፣ የስሜት መግለጫ የሁሉም ነገር ማዕከል ተደርጎ ይወሰድ ነበር። የሰው ልጅ ልብ ፤ አንድን ሰው የሚያቆይ « የሚመታ የሰውነት ክፍል ብቻ አይደለም ይላሉ የህክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ዮሀን ካስፐር ሩገስ፤ ልብ ስስ እና በቀላሉ የሚጎዳ የሰውነታችን አካል ነው በማለት ልብን ይገልፃሉ። ስለሆነም ልብ በብዙ ባህል የአንድን ሰው ነፍስ በአካሉ ላይ ያንፀባርዋል ሲሉ ያብራራሉ።

Bildergalerie Valentinstag in Afghanistan
ምስል DW/H. Sirat

«ቫለንታይንስደይ» የሚለው ስያሜ የተሰጣቸው በ3ኛው ክፍለ ዘመን በዛሬይቱ ኢጣሊያ ይኖሩ የነበሩት ቫለንታይን በወቅቱ ጥሩ ልብ እንደነበራቸው ይገለፃል። ተወዳጁ ጳጳስ በወቅቱ ለፍቅረኛሞች ከግቢያቸው አበባ እየቆረጡ ይሸልሙ በተለይም በጊዜው በሮማ ንጉስ ክልክል በነበረው በክርስትና ዕምነት መሰረት ፍቅረኛሞችን በድብቅ በጋብቻ ያስተሳስሩ እንደነበር ይነገራል።በዚህም ምክንያት ዳግማዊን ጉስክላውዲዮስ፤ ቫለንታይንን የካቲት14 ቀን269 ዓም ሮም ላይ በሞት መቅጣታቸውን ታሪክ ይገልፃል። ምናልባትም ጥንዶች በዚህ ዕለት አበባ የሚለዋወጡበት ምክንያት ይህ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። «ቫለንታይንስደይ» የሚለው ስያሜ ቫለንታይን ከተባሉ ሰው እንደመጣ ቢታወቅም በወቅቱ አንድ ብሎም ሁለት ቫለንታይን የተባሉ ቅዱሳን ስለመኖራቸው ግን ግልፅ አይደለም።

የፍቅረኛሞች ቀን በታይላንድ

ታይላንድ አዳጊ ወጣቶች በፍቅረኛሞች ቀን ከአንድ ነገር እንዲቆጠቡ አሳስባለች። « ጥሩ ነገር ተመገቡ ነገር ግን ከግብረስጋ ግንኙነት ተቆጠቡ» የሚል ዓላማ ይዞ ሐሙስ ዕለት የተጀመረው የመንግሥት ዘመቻ፤ አዳጊ ወጣት ጥንዶችን ሞራላዊ ግዴታ ለማስጨበጥ የታለመ ነው። በዚህም ተሳትፎ ባለስልጣናቱ ልጃ ገረጆች ያለ እቅዳቸው እና ፍላጎታቸው ቀድመው እንዳይፀንሱ እና ወጣቶች በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመቀነስ ማሳሰብ ፈልጓል። እንደ ታይላንድ የጤና ሚኒስቴር ከሆነ ታይላንድ በርካታ አዳጊ ወጣቶች ለዕርግዝና የተዳረጉባት ሀገር ናት። በዚህም ምክንያት በርካታ ወጣቶች በህገ ወጥ መንገድ እና አስተማማኝ ባልሆነ መንገድ ፅንስን ለማስወረድ ሲሞክሩ ተስተውሏል። መንግሥት የማህበራዊ መገናኛዎችን እና የጥንድ ማገናኛ እና ማፈላለጊያ ድረ ገፆችን ላልተፈለገ የአዳሚ ወጣቶች እርግዝና ተጠያቂ ያደርጋሉ። የሀገሪቱ መንግሥት በዚህ አመት 43 ሚሊዮን ኮንዶሞች በነፃ ለማደል ማቀዱንም አስታውቋል።

Bildergalerie Valentinstag Vorbereitungen
ምስል Getty Images/Afp/Paul Ellis

የኔዘርላንድስ ፓስታ ቤት ረቡዕ ዕለት እንዳስታወቀው ደግሞ በፍቅረኛሞች ቀን ደብዳቤ የሚልኩ ኔዘርላንዳዊያን በከንፈር የሳሙትን ቴንብር ሊልኩ ይችላሉ። ቴንብር በሚለጠፍበት ቦታ አንድ የከንፈር አሻራ በቂ ይሆናል። ሲል ነው ፖስታ ቤቱ በድረገፁ ላይ ያሰፈረው። ለከንፈሩ አሻራ ግን ሰዎች አስቀድመው ሊፒስቲክ ወይም የከንፈር ቀለም መቀባት ግድ ይላቸዋል።

በርግጥ ምን ያህል ፍቅረኛሞች እዚህ ጀርመን ውስጥ ቀኑን እንደሚያከብሩ ነገ የሚታይ ይሆናል። በዚህ በኖርድ ራንን ቬትቫሊያ ፌደራል ግዛት ከተማው በቀይ ልብስ፣ ፅጌሬዳ እና ልብ ባትደምቅም ፤ በሁሉም ቀለማት አሸብርቋል። ወቅቱ የፌሽታ ጊዜ ነው። የፋሲካ ፆም ከመግባቱ በፊት ሰው እንደፈለገው የሚበላ እና የሚጠጣበት የካርኔቫል በዓል ትናንት መከበር ጀምሯል። እስከ ሚቀጥለው ረቡዕ ድረስ ይቀጥላል።

ልደት አበበ

ተክሌ የኋላ