1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፑንትላንድና የሶማሊያ ግንኙነት

ረቡዕ፣ ነሐሴ 1 2005

የፑንትላንድ መስተዳደር ባለፈው ሰኞ ሃገሪቱ ከሶማሊያ ጋር የነበራትን ትብብብሮችና ግንኙነቶች በሙሉ እንዳቋረጠች አስታውቋል ። የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኝ አንድሪውስ አታ አሳሞዋ የሶማሊያ መንግሥት ማሰሪያ ያላበጀላቸውና ፑንትላንድን ያላስደሰቱ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ እርምጃውም ለሶማሊያ መንግሥት የማንቂያ ጥሬ መሆኑኑን ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/19LbS
ምስል DW

ከሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት ጋር የነበራትን ግንኙነት ማቋረጧን ያሳወቀችው የሶማሊያዋ ከፊል ራስ ገዝ ግዛት ፑንትላንድ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን በመጣር ተወቀሰች ። አንድ የሶማሊያ ምክር ቤት አባል ፑንትላንድን የሶማሊያን መንግሥት አቅጣጫ ለማሳት በመሞከር ከሰዋል ። የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኝ አንድሪውስ አታ አሳሞዋ ግን የፑንትላንድ እርምጃ ለሶማሊያ መንግሥት የማንቂያ ጥሬ ነው ብለዋል ። እንደ ተንታኙ የሶማሊያ መንግሥት ማሰሪያ ያላበጀላቸውና ፑንትላንድን ያላስደሰቱ በርካታ ጉዳዮች አሉ ። ሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ  የምትገኘው የፑንትላንድ መስተዳደር ባለፈው ሰኞ ነበር ሃገሪቱ ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ጋር የነበራትን ትብሮችና ግንኙነቶች በሙሉ እንዳቋረጠች ያስታወቀው ። መስተዳድሩ ግንኙነቱን ማቋረጡን ባሳወቀበት መግለጫው ሶማሊያ ወደ ቀድሞው የግጭት ፣ የመፈናቀል የጎሳዎች ጥላቻ አዙሪት እንደገና መመለሷን ፣ የፌደራል መንግሥትም ለሃገሪቱ ጊዜያዊ  ህገ መንግሥትም ደንታ እንደሌለው ጠቅሷል ። የፑንትላንድን እርምጃና ወቀሳ ግን በሶማሊያ ባለሥልጣናት ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም ። ሁሴን ባንቱ የተባሉት የሶማሊያ ምክር ቤት አባል ፑንትላንድን የአካባቢው ሰላም እንዲደፈርስ በመሻት ወቀሰዋል ።

Somalia Küste Strand
ምስል AP

« እርምጃውን እንዳጤነው ጥሩ አይደለም ። ፑንትላንድ በአጠቃላይ ሶማሊያን አቅጣጫ ለማሳት ትፈልጋለች ። ትኩረታችንን ወደ ደቡባዊ ሶማሊያ እንዳናደርግ ፣ በሶማሊያም ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍንና ሁሌም አካባቢው ምስቅልቅሉ እንዲወጣ ነው የሚፈልጉት ።»

ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ በሚገኘው የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ቀንድ ተንታኝ አንድሪው አታ አሳሞዋ ግን ፑንትላንድ እርምጃውን የወሰደችው ከአዲሱ የሶማሊያ መንግሥት በኩል ይጠበቁ የነበሩ ተግባራት ባለመከናወናቸው ነው ብለዋል ። አሳሞዋ  እጎአ መስከረም 2012 የሶማሊያ ጊዜያዊ ህገ መንግሥት ቀረፃ ሲጠናቀቅ ብዙ እልባት ያላገኙ ጉዳዮች ፣ እስካሁንም እንዳሉ በመሆናቸው ፑንትላንድ እርምጃውን እንድትወስድ ማድረጉን ያስረዳሉa ። አሳሞዋ ማሰሪያ ያልተበጀላቸው ያሏቸው ጉዳዮች አራት ናቸው ።

« አንደኛው የሶማሊያ ህገ መንግሥት ጊዜያዊ መሆኑ ነው ። በዚህ የተነሳም በህገ መንግሥቱ የሃብት አጠቃቀም ፣ የሸሪአ ህግና የመሳሰሉት ለህዝበ ውሳኔ መቅረብ ያለባቸው በሔራዊ ደረጃም ውይይት ሊካሄድባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ነበሩ ። 2ተኛ ለሃገሪቱ አዲስ የሆነው አጠቃላይ የፌደራሊዝም ጥያቄ ነው ለዚህ ደግሞ አዲሱ መንግሥት የድንበር አካላይ ኮሚሽን ያስፈልገዋል ። የሚመሰረተውም መንግሥት ሥልጣን የሚያከፋፍል ወይም ሥልጣን በማዕከላዊ ደረጃ የያዘ መሆኑ ግልፅ መሆን አለበት ። እኔ አዲሱን መንግሥት ሥልጣኑን ወደ የአካባቢው መስተዳደር ሳያወርድ ለየአካባቢው የጎሳ ተወላጆች  ሥልጣን የሰጠ መንግሥት ነው የምለው ።  »

Konflikte in Somalia
ምስል Bettina Rühl

3ተኛው መልስ ያላገኘ ጥያቄ የፀጥታ ጉዳይ ነው ። አሳሞዋ እንደሚሉት በትንሹም ቢሆን በአሸባብ ላይ የተገኘው የበላይነት ፣ ሳይጠፋ እንዲቀጥል የሶማሊያ ህዝብ ይፈልጋል ሆኖም የሶማሊያ መንግሥት በመላ ሃገሪቱ ሰላም የማስፈን ፖለቲካዊ ፍላጎት አላሰየም የሚል ትችትም ይሰነዘርበታል ። አራተኛው ደግሞ መንግሥት ከሰላም በተጨማሪ እርቅ ማምጣት ባለመቻሉም እየተወቀሰ ነው ። ከነዚህ እልባት ካላገኙ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ፑንትላንድ መንግሥትን በ3 ጉዳዮች ነው የምትወቅሰው ።

« መንግሥት በፌደራሉ ህገ መንግሥት ላይ ምክክር አለማካሄዱ ፣ በፌደራል ና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ በትጋት አለመንቀሳቀሱ ፣ እንዲሁም ለሃብት ክፍፍል ጉዳይ መፍትሄ አለመፈለጉ ናቸው ። »

በነዚህ እልባት ባልተሰጣቸው ጉዳዮች ሰበብ ፑንትላንድ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ግንኙነት ማቋረጧ ደግሞ መዘዞችን ማስከተሉ አይቀርም ።

Bildergalerie Somalia Sicherheitslage Jowhar 2012
ምስል STUART PRICE/AFP/Getty Images

« በመጀመሪያ ሥልጣን ከያዘ ዓመት ሊሞላው ሳምንታት የቀሩት የአዲሱ መንግሥት አቅም ጥያቄ ውስጥ ያስገባል ፣ በሁለተኛ ደረጃ በአመራሩ ውስጥ ጠለቅ ያለ ክፍፍል መኖሩንም ያሳያል 3ተኛ የፌደራል መስተዳድር አወቃቀርም እንዲህ ቀላል አይሆንም ። ይህ ሁሉ ተደማምሮ የአሸባብ ፕሮፓጋንዳ መጠየቂያ መሆኑም አይቀርም ። »

ሆኖም በአሳሞዋ እምነት ፣ ፑንትላንድ የፖለቲካ ስምምነት እንዲደረግ ከመጠየቅ  ውጭ የመገንጠል ጥያቄ ባለማቅረቧ ችግሩ በቀላሉ ሊፈታ ይችላል ። ኢጋድና የአፍሪቃ ህብረት የልዩነታቸው ምክንያቶች በግልፅ የተቀመጡትን ሁለቱን ወገኖች ሊያግባባ የሚችል መንንገድ መፈለግ አይቸግራቸውም

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ