1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፓን ጊ ሙን ድጋሚ መመረጥና አፍሪቃ

ሐሙስ፣ ሰኔ 16 2003

ፓን ትልቁን አለም አቀፍ ድርጅት የመምራት ብቃትና ቅልጥፍናቸዉ ብዙ እያስተቻቸዉ ነዉ።በተለይ ለአፍሪቃ መሥራት የሚገባቸዉን ያሕል አልሰሩም የሚል ወቀሳ ይሰነዘርባቸዋል።ያም ሆኖ በድጋሚ ለመመረጥ ከሐያላኑ መንግሥታት ሙሉ ድጋፍ ነበር ያገኙት።

https://p.dw.com/p/RVOM
ምስል picture-alliance/dpa

23 06 11

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን የያዙትን ሥልጣን ለተጨማሪ አምስት አመት እንደያዙ እንዲቀጥሉ ባለፈዉ ማክሰኞ ተመርጠዋል።ፓን ትልቁን አለም አቀፍ ድርጅት የመምራት ብቃትና ቅልጥፍናቸዉ ብዙ እያስተቻቸዉ ነዉ።በተለይ ለአፍሪቃ መሥራት የሚገባቸዉን ያሕል አልሰሩም የሚል ወቀሳ ይሰነዘርባቸዋል።ያም ሆኖ በድጋሚ ለመመረጥ ከሐያላኑ መንግሥታት ሙሉ ድጋፍ ነበር ያገኙት።ተቀናቃኝ እጩ ሥላልቀረበም የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ፓንን በጅምላ ድምፅ ነዉ ነዉ የመረጣቸዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝርዝር ዘገባ አለዉ።

ለሳቸዉ ከዚያ በፊት እንደሚሆን ቢያዉቁትም ሲሆን ሲያዩት በርግጥ አስደሳች ነበር።ማክሰኞ ሆነ።ዋሽንግተን ከሚገኘዉ ከዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ቤተ-መዘክር ለዚሁ ሥነ-ሥርዓት ሲባል ኒዮርክ ድረስ በተጓዘዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ (ቻርተር) ላይ ቀኝ እጃቸዉን አሳረፉ።አሉም።
«እኔ ፓን ጊ ሙን---የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊነት ለማገልገል ቃል አገባለሁ።»

ከእንግዲሕ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር እስከ 2016 ድረስ የግዙፉ ዓለም አቀፍ ድርጅት ትልቅ ዲፕሎማት ናቸዉ።ብቻቸዉን ነዉ-የተወዳደሩት።አንድ መቶ ዘጠና ሁለት አባል ሐገራትን የሚወክሉት ዲፕሎማቶችም በተናጥል ድምፅ መስጠት አላስፈለጋቸዉም።በጅምላ ጭብጨባ አፀደቁላቸዉ።እንደ «ድልድይ አገለግላለሁ» አሉ ፓን በአፀፋዉ።«ለወደፊቱም ዓለምን እንደሚያገናኝ ድልድና ሸምጋይ ማገልገሌን እቀጥላለሁ።»

ድምፀ-ለንቋሳ-ለስላሳዉ የስልሳ-ሰባት ዓመት ደቡብ ኮሪያዊ ዲፕሎማት ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ መንግሥታት ሙሉ ድጋፍ አልተለያቸዉም።ለድጋሚ ዘመነ-ሥልጣን የመመረጣቸዉ መሠረትም ሌላ አይደለም። ከዚሕ ባለፍ ግን ያሉትን መሆናቸዉን ብዙዎች ይጠራጠራሉ። እንደሚያዉም በተቃራኒዉ የተከፋፈለችዉን ዓለም የማቀራረብ ዲፕሎማሲያዊ ክሒል፥ ብስለት፥ ሌሎችን የማድመጥ ብልጠት፥ ተናግሮ የማሳመን ብቃትም የላቸዉም ነዉ የሚባል።

በእንግሊዘኛ ቅላፄቸዉ ሳይቀር ይተቻሉ።የአፍሪቃዊ ቀዳሚያቸዉ የኮፊ አናን አይነት ግርማ ሞገስማ ጨርሶ የላቸዉም ነዉ-የሚባለዉ።መንበሩን ፕሪቶሪያ ያደረገዉ ዓለም አቀፍ የሥልታዊ ጥናት ተቋም የበላይ ጃኪ ሲለርስ እንደሚሉት ፓን በድጋሚ በመመረጣቸዉ በተለይ አፍሪቃዉያን የሚደሰቱበት ምክንያት የለም።

«እንደ ጠንካራ መሪ አይታዩም።እንደሚመስለኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድርጅትን ለማሻሻልና የአፍሪቃዉያንን ድምፅ በመወከሉ ረገድ ከቀዳሚያቸዉ ከኮፊ አናን ጋር ጨርሶ አይወዳደሩም።እርግጥ አናን አፍሪቃዊ ባን ጊ ሙን ደቡብ ኮሪያ መሆናቸዉ አይዘነጋም።ከዚሕ ዉጪ ግን እንደሚመስለኝ በድጋሚ በመመረጣቸዉ አፍሪቃዉያን የሚደሰቱበት ምክንያት የለም።አፍሪቃዉያን አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ከአፍሪቃ ጋርና ሥለ አፍሪቃ ብዙ ሊሰራ ይገባዋል የሚል ስሜት አላቸዉ።»

የሊቢያ ፖለቲካዊ ምሥቅልቅል የፓን ጊ ሙንን ዲፕሎማሲያዊ ክሒል፥ ጥረትና ትኩረት የሚጠይቅ ነበር።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በሊቢያ ላይ ያሳለፈዉን ዉሳኔ በምክር ቤቱ ዉስጥ ያሉትም ሆኑ ከምክር ቤቱ ዉጪ ያሉ አብዛኞቹ የአፍሪቃ መንግሥታት ደግፈዉታል።ምዕራባዉያኑ ግን ጃኪ ሲለርስ እንደሚሉት አጓጉል ነዉ የተረጎሙት።«በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ያሉት ሰወስቱ የአፍሪቃ ሐገራት ደቡብ አፍሪቃ፥ ናይጄሪያና ጋቡን ከሌሎቹ ጋር የጋራ አቋም ይዘዉ ነበር።የዉሳኔ ቁጥር 1970 እና 1973 ደግፈዉ ድምፅ ሰጥተዋል።ማናቸዉም ቢሆኑ ግን ብሪታንያና ፈረንሳይ የወሰዱትን የአዲስ ቅኝ አገዛዝ አይነት እርምጃ ይወሳዳሉ ብለዉ አልጠበቁም ነበር።»

ድብደባዉን የአፍሪቃ ሕብረት ተቃዉሞታል።በተቃዉሞዉ ሰበብ በአፍሪቃ ሕብረትና በተባበሩት መንግሥታት ታሪክ ብዙም የማይታወቅ ልዩነት ፈጥሯል።እራሳቸዉን «ድልድይ» ሚሉት ፓን ጊ ሙን የድርጅታቸዉ ዉሳኔ በአግባቡ እንዲተረጎም የሞከሩት የለም።የሁለቱን ተቋማት ልዩነት ለማጥበብም የፈየዱት የለም። ሲለርስ እንደሚሉት ፓን ከደቡባዊዉ ዓለም ይልቅ የምዕራቦች ታማኝነታቸዉ ነዉ የሚጎላዉ።«ባንዳድ ሁኔታዎች ያለዉ አመለካከት እሳቸዉ የዩናይትድ ስቴትስና የምዕራቡን ፍላጎት የሚወክሉ መሆናቸዉን በተደጋጋሚ አስመስክረዋል የሚል ነዉ።ከደቡብ ንፍቀ ክበብ የሚነሱ ጉዳዮችን በበቂ ሁኔታ ትኩረት አልሰጡም የሚል ነዉ።»

ፓን ጊ ሙን በሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ አመራር፥ አሠራራቸዉን ካልቀየሩ ሲለር ደበብ ባሉት ክፍለ ዓለም በተለይ በአፍሪቃዉያን ዘንድ ተቀባይነት ማግኘታቸዉ አጠራጣሪ ነዉ።

ነጋሽ መሀመድi

አርያም ተክሌ


ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ