1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሬዝዳንት ሽታይንማየር የኢትዮጵያ ጉብኝት በጀርመን መገናኛ ብዙሃን ዕይታ

ቅዳሜ፣ ጥር 25 2011

ሱድዶቸ ጋዜጣ በጄንዋሪ 28 ዕትሙ ፕሬዝዳንት ሽታይንማየር ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የተሃድሶ ለውጥ ስኬት እና አገሪቱን መልሶ ለመገንባት በሚካሄደው ጥረት ጀርመን ድጋፏን ለማጠናከር እንዲሁም ከአፍሪቃ አገራት ጋር ያላትን ወዳጅነት እና ትብብር ለማጠናከር ጉብኝት ማድረጋቸውን ነው የጠቆመው::

https://p.dw.com/p/3Ccgu
Äthiopien Bundespräsident Frank-Walter Steinmeier in Addis Abeba
ምስል DW/A. Steffes

የኢትዮጵያ እና የጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከአንድ ምዕተ ዓመት የዘለለ ታሪክ እንዳለው የተለያዩ መዛግብት ይጠቁማሉ :: ለአብነት በጎርጎሮሳውያኑ 1915 ዓ.ም አካባቢ የጀርመኑ ንጉስ ካይዘር ዊልሄልምስ ዳግማዊ ታላቋ ብሪታንያ በምትቆጣጠራቸው በተለይም በአውስትራሊያ ኒውዝላንድ እና ህንድ የጦር ኃይሏን እና የንግድ ቁሳቁሶቿን ለማመላለስ የምትጠቀምበትን የስዊስ ካናል የጀርመን ዋና ስትራቴጂካዊ ቀጣና ለማድረግ እንዲሁም በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ያሉትን የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ኃይል ለማዳከም በነበራቸው ምኞት ጠንካራ የመንግሥት አስተዳደር አላት ብለው የሚያስቧትን ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ላይ እንድትሳተፍ ልዑካኖቻቸውን ከበርሊን ድረስ በመላክ ልጅ እያሱን ያግቧቧቸው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ይህንኑ በተመለከተም የእንግሊዙ ዜና ማሰራጫ ቢቢሲ የኢትዮጵያው ልዑል ልጅ እያሱ በጀርመን የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ዕቅዶች ላይ የነበራቸውን የተጽዕኖ ፈጣሪነት ሚና ልዩልዩ መረጃዎችን አጣቅሶ በስፋት ዘግቧል / How Ethiopian prince scuppered Germany's WW1 plans / :: የሩቁን እንኳ ትተን በጎርጎሮሳውያኑ ዘመን1935 ዓ.ም በተካሄደው የኢትዮ-ኢጣልያ የማይጨው ጦርነት ወቅት በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት አያቱ የንጉሰ ነገሥቱ ምርኮኛ የነበሩ እና በኋላም እዛው መቅደላ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊት አግብተው ኑሮዋቸውን በዛው በጎንደር የመሰረቱት የጀርመናዊው ሃል ልጅ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ልዩ አማካሪ ዳቪድ ሃል 2 ሚልዮን ዶችማርክ የሚያወጣ መውዜር የተባለ የጦር መሳሪያ ከጀርመን ለኢትዮጵያ ማስመጣቱን አንዳንድ ቆየት ያሉ ታሪኮች ይዘክራሉ:: በሁለቱ ሃገራት መካከል የተጀመረው ትብብር ጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባው በተለይም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ከ 1945-48 ዓ.ም በጀርመን በተከሰተው ከፍተኛ የምግብ እጥረት እና ረሃብ ችግር ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ 2 መቶ ሺህ ዶላር የሚያወጣ ቡና ብርድ ልብስ እና ሌሎችንም ቁሳቁሶች ለጀርመን ሕዝብ ከለገሱ በኋላ እንደሆነ ይነገራል :: ለሌላው ሕዝብ የሚያዝን እና ለጋሽ የሆነው የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ ለጀርመን ሕዝብ ላደረገው ውለታም ምስጋና ለማቅረብ ከ2ተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ የፌደራል ሪፐብሊክ ጀርመን የመጀመሪያው ቻንስለር የነበሩት ዶክተር ኮንራድ አደንአወር እና የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ቴዎዶር ሆይሽ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት በ 1954 ዓ.ም ንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለሥላሴ በጅቡቲ ወደብ አድርገው በስዊስ ካናል በኩል በመርከብ አስር ቀናት ያህል ተጉዘው ዋና ከተማ ቦን ሲገቡ የሃገሬው ሕዝብ በነቂስ ወቶ እጅግ ከፍተኛ የሆነ አቀባበል አድርጎላቸዋል:: በዚህም ንጉሥ ኃይለስላሴን ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ የጀርመንን ምድር የረገጡ የመጀመሪያው አፍሪቃዊ የዓለም መሪ / ርዕሰ ብሄር / ሆነው በታሪክ እንዲመዘገቡ አድርጓቸዋል::
በእንዲህ ዓይነቱ ጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባዉን የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ለተጀመረው የተሃድሶ ለውጥ ጅማሮ ያላቸውን ድጋፍ እና አጋርነት ለማረጋገጥ የጀርመኑ ርዕሰ ብሄር ዶክተር ፍራንክ-ቫልተር ሽታይንማየር ካለፈው ዕሁድ ጀምሮ ለአራት ቀናት ይፋዊ ጉኝት አድርገዋል:: ጉብኝታቸውን በተመለከተም የጀርመን ጋዜጦች እና ልዩልዩ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ የዜና ሽፋን ሰተውታል:: ጥቂቶቹን ለመዳሰስ እንሞክራለን ::
ሱድዶቸ ጋዜጣ በጄንዋሪ 28 ዕትሙ ፕሬዝዳንት ሽታይንማየር ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የተሃድሶ ለውጥ ስኬት እና አገሪቱን መልሶ ለመገንባት በሚካሄደው ጥረት ጀርመን ድጋፏን ለማጠናከር እንዲሁም ከአፍሪቃ አገራት ጋር ያላትን ወዳጅነት እና ትብብር ለማጠናከር ጉብኝት ማድረጋቸውን ነው የጠቆመው:: ጋዜጣው ርዕሰ ብሄሩ ዓለማቀፋዊ በሆኑ እንደ አየር ንብረት ባሉ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ወቅት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ በመጣው የሕዝቦች ፍልሰት ዙሪያም ትኩረት ሰቶ መነጋገር እንደሚገባ መግለጻችውን ጠቁሟል:: " እኛ አውሮጳውያንም ሆንን አፍሪቃውያን በተለይም የነገ ተስፋ ለሆኑ ታዳጊ ወጣቶች ብሩህ እና የተሻለች ዓለምን ለመፍጠር ጠንክረን መስራት ይገባናል " ሲሉ በአዲስ አበባው ጉብኝታቸው ወቅት ማስገንዘባቸውንም ጋዜጣው አክሎዋል:: እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረሰው ታሪካዊ የሰላም ስምምነት አበረታች የሚደነቅ እና በቀጣናውም ልማትን እና ብልጽግናን ለማጠናከር ትልቅ እገዛ እንደሚኖው ፕሬዝዳንቱ መግለጻቸውንም ጋዜጣው በዘገባው አብራርቷል::
የጀርመኑ መንግስታዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኤ.አር.ዲ ደግሞ በዕለታዊ የቅኝት / ዳሰሳ / - " ታገስሻው " ዝግጅቱ በአፍሪቃ ጋና እና ጋምቢያን ቀጥሎም ደቡብ አፍሪቃ እና ቦትስዋናን አሁን ደግሞ ኢትዮጵያን የጎበኙት ፕሬዝዳንት ሽታየንማየር ካለፈው ዓመት ጀምሮ በለውጥ ሂደት ላይ ለሚገኘው እንዲሁም ከኤርትራ እና ሌሎችም አገራት ጋር የሰላም ስምምነት በመፈረም በአፍሪቃ ቀንድ ዘላቂ እና አስተማማኝ ደህነነት ለማስፈን ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኘውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ አስተዳደር ድጋፍ ለመስጠት ወደዛው ማቅናታቸውን ገልጿል:: ኤ.አር.ዲ " የዲሞክራሲ ለውጥ ሃዋርያ የምስራቅ አፍሪቃ ኮከብ " ሲል ያወደሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለውጡን ከማጠናከሩ ጎን ለጎን በአገሪቱ የሚታየውን የብሄር ግጭት እና ስራ አጥነት ለመቅረፍ መንግስታቸው ጠንክሮ በመስራት ላይ መሆኑንም በዘገባው አመልክቷል:: በእርስ በእርስ ግጭት እና ቀውስ ውስጥ ለሚገኙ ሌሎች የአፍሪቃ አገራትም በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጅማሮ ጥሩ ምሳሌ እና ሞዴል ሊሆን እንደሚችል ነው ፕሬዝዳንት ሽታንማየርን ጠቅሶ ዘገባው ያመለከተው::
ጀርመን በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ በተራድዖ ትብብር ብቻ ሳይሆን በልማት በኢንቨስትመንት እና  በቴክኖሎጂ ሽግግር ጭምር ለማገዝ ያላትን ቁርጠኝነት አመላካች መሆኑም የፕሬዝዳንት ሽታይንማየር ጉብኝት አመላካች ሆኖ በተለያዩ የጀርመን ጋዜጦች ተጥቅሷል:: ኤ.አር.ዲ ቬስትፋልሽ ሩንድሻው እና ሌሎችም የጀርመን ጋዜጦች በፕሬዝዳንት ሽታይንማየር የተመራው የልዑካን ቡድን በጀርመኑ የልማት ተራድዖ ድርጅት ድጋፍ የሚደረግለትን የፌደራል የቴክኒክ ሞያ ትምህርት እና ሥልጠና ኢኒስቲቲዩትን እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት የሳይንስ እና የባህል ማዕከል በምህጻሩ ዩኔስኮ በዓለም የቅርስ መዝገብ የተመዘገቡትን ታሪካዊዎቹ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት መጎብኘታቸውን ዘግበዋል:: በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ለማሳለጥም እንደ ሲመንስ ካሉ የኤሌክትሮኒክስ ተቋማት እና ግዙፉ የጀርመን የመኪና አምራች ድርጅት ፎልክስ ቫገን ጋር በኢትዮጵያ መገጣጠሚያ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም የተደረሰውን ስምምነት ጨምሮ ሌሎች ውይይት የተካሄደባቸውን  የኢንቨስትመንት አማራጮች በዘገባዎቻቸው ዳሰዋል:: አሁን ላይ የተጀመረውን የዲሞክራሲ ሥርዓት በተቋማዊ አደረጃጀት ለማጠናከር በሂደት ላይ የሚገኘው ለውጥ አራማጁ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ 50 በመቶ ያህል የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያደረገው ሥር ነቀል ለውጥም ለሌሎች የአፍሪቃ አገራት ምሳሌ ሆኖ የሚጠቀስ እና በፕሬዝዳንት ሽታይንማየርም አድናቆት የተቸረው ጉዳይ እንደነበር በርሊነር ሞርገን ፖስት ዘግቧል::
ከፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ ጉብኝት ፍጻሜ በኋላ በአውሮፕላናቸው ላይ በተከሰተው የቴክኒክ እክል ምክንያት ጉዞዋቸው ለሰዓታት መስተጓጎሉም የጀርመን ጋዜጦችን እና ሌሎች መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር:: በተለይም የጀርመን ባለስልጣናት ለጉዞ የሚጠቀሙባቸው በግዙፉ የአውሮፕላን ማምረቻ ኢንዱስትሪ ኤርቡስ የተመረቱት እና ከ2ተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ የፌደራል ሪፐብሊክ ጀርመን የመጀመሪያው ቻንስለር በነበሩት ዶክተር ኮንራድ አደንአወር እና በመጀመሪያው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቴዎዶር ሆይሽ የተሰየሙት ዘመናዊ የእንግዳ ማረፊያ መኝታ ክፍሎች እና የሚሳኤል ጥቃትን የሚከላከል ልዩ የጸረ-ሚሳኤል መሳሪያ እንደተገጠሙላቸው የሚነገረው ሁለቱ ዘመናዊ ጀት አውሮፕላኖች የገጠማቸው ተደጋጋሚ የቴክኒክ እክል የሰሞኑ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኗ ቆይቷል:: ታዋቂዎቹን ቢልድ እና ዴር ሽፒግል ጋዜጦች ጨምሮ ኤ.አር.ዲ የቴሌቭዥን ጣቢያ ሽተርን የዜና አውታር እና ሌሎችም የመገናኛ ዘዴዎች ፕሬዝዳንት ሽታይንማየርን እና 55 አባላት ያሉት የፖለቲካ የንግድ እና የባለሙያዎች የልዑካን ቡድን የሚጓዙበት ኤርቡስ ያመረተው A-340 ቴዎዶር ሆይሽ አውሮፕላን የቴክኒክ እክል ከገጠመው በኋላ አዲስ አበባ ሆቴል ውስጥ ለመቆየት መገደዳቸውን አስታውቀዋል:: ይህ ዓይነቱ ችግር ፕሬዝዳንቱ ሲገጥማቸው የመጀመሪያ አለመሆኑን ያስታወሰው ፍራንክፉርተር ሩንድሻው ጋዜጣ በበኩሉ ርዕሰ ብሄር ከመሆናቸው አስቀድሞ እንደ ጎርጎሮሳውያን 2014 ዓ.ም የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ዘመን በተመሳሳይ ኢትዮጵያን ጎብኝተው በሚመለሱበት ወቅት የሚጓዙበት አውሮፕላን ጎማ ፈንድቶ እስኪጠገን ከጉዞ ተስተጓጉለው ነበር ብሏል ::
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር በጀርመኑን የፋይናንስ ሚኒስትር ኦለፍ ሾልዝ የሚመራውን የልዑካን ቡድን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው አውሮፕላን በደረሰበት ድንገተኛ የቴክኒክ ችግር ኢንዶኔዚያ ለማረፍ ተገዷል:: ከሁለት ወራት በፊትም የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል የአርጀንቲናውን የቡድን 20 አገራት ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት የሚጓዙበት የኤርቡስ ጀት አውሮፕላን በደረሰበት ከባድ የቴክኒክ ብልሽት ምክንያት መካፈል እንዳልቻሉ ይታወሳል:: ከሶስት ሳምንት በፊትም ወደ ደቡባዊ አፍሪቃ አገራት ለጉብኝት ያቀኑት የጀርመኑ የኢኮኖሚ እና የልማት ትብብር ሚኒስትር ጌርድ ሙለር አውሮፕላናቸው በደረሰበት ብልሽት ሳቢያ ከማላዊ ለመመለስ እክል ገጥሟቸው እንደነበር ተዘግቧል:: ባለፈው ረቡዕ ደግሞ የጀርመን ርዕሰ ብሄር በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት እንዳጠናቀቁ በተመሳሳይ የአውሮፕላን የቴክኒክ እክል ጉዞዋቸው መስተጓጎሉ የመገናኛ ብዙሃንን አትኩሮት ሲስብ የክስተቶቹ መደጋገም ደግሞ የኤርቡስ አውሮፕላን አምራች ኩባንያንም ስም በተደጋጋሚ እንዲነሳ ለማድረግ ችሏል:: 

Berlin, Bundespräsident Frank-Walter Steinmeier geht an Bord der Regierungsmaschine "Theodor Heuss"
ምስል picture-alliance/dpa/B. Pedersen
Bundespräsident Frank-Walter Steinmeier in Äthiopien
ምስል picture-alliance/dpa/B. Pedersen
Bundespräsident  Steinmeier Besuch in Äthiopien
ምስል Deutsche Botschaft


እንዳልካቸው ፈቃደ
ልደት አበበ