1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሬዝዳንት ሽታይንማየር የኢትዮጵያ ጉብኝት

ረቡዕ፣ ጥር 22 2011

ጀርመንና የኢትዮጵያ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ  ግንኙነት ያላቸዉ ሀገሮች ናቸዉ።በሀገራቱ ያለዉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና  የመንግስት አወቃቀር ምንም ይሁን ምን የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ለማጠናከር  በተለያዩ ጌዜያት የጀርመን ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/3CKxK
Bundespräsident  Steinmeier Besuch in Äthiopien
ምስል Deutsche Botschaft

የጀርመኑ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት


የወቅቱ የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርም ከትናንት ጀምሮ ኢትዮጵያን በይፋ እየጎበኙ ነው ።ጉብኝቱ ኢትዮጵያ በለዉጥ ሂደት ላይ ባለችበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል። 
ኢትዮጵያና ጀርመን ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሁለንተናዊ ግንኙነት ያላቸዉ ሀገሮች ቢሆኑም ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለዲሞክራሲ መጎልበት የሚረዱ ተቋማትን በመገንባት ፤ በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት እንዲሁም በሌሎች ዲፕሎማሲያዊ ትብብሮች ላይ የነበረዉ ትስስር የሚፈለገዉን ያህል እንዳልነበረ ነዉ የሚነገረዉ።ለዚህም ኢትዮጵያ ዉስጥ የነበረዉ የፖለቲካ ሁኔታ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ነዋሪነታቸዉ በጀርመን ሀገር የሆኑት የፖለቲካና የህግ ጉዳዮች ባለሙያ ዶክተር ለማ ይፍራ ሸዋ የተናገሩት።
ከትናንት ምሽት ጀምሮ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ወደ ኢትዮጵያ ከማምራታቸዉ በፊት ለDW እንደገለፁት ግን በሀገሪቱ አሁን እየታየ ያለዉ ለዉጥ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት  የበለጠ የሚያጠናከር  እንዲሁም  ጀርመን በኢትዮጵያ  የበለጠ ፍላጎት እንዲኖራት የሚያደርግ ነዉ። በዛሬዉ ዕለት ከኢትዮጵያ  አቻቸዉ  ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘዉዴ ጋር ባደረጉት ዉይይትም ኢትዮጵያ  በተለያዩ ዘርፎች ላይ ለውጥ እያካሄደች በመሆኑ ሀገሪቱን  ለመጎብኘት ትክክለኛ ሰዓት መሆኑን  አመልክተዋል።አሁን የሚታየዉ ለዉጥ ሀገሪቱን ወደ ዲሞክራሲና ምጣኔ ሀብታዊ መረጋጋት ሊወስዳት ይችላልም ነዉ ያሉት። ጀርመን በአዉሮፓ ካላት ተሰሚነት አንፃር ይህን መሰሉ የፕሬዝዳንቱ ንግግርም ይሁን ጉብኝት የለዉጡን ጎዞ ያጠናክረዋል ይላሉ የፖለቲካ ሳይንስ ሙህሩ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ።
 ፕሬዝዳንቱ በተለይም አዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት ሴቶች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ የተሰራውን ስራና ከኤርትራ መንግስት ጋር የተደረሰዉን የሰላም ስምምነት አድንቀዋል ።
እንደ ዶክተር ለማ ጀርመን ለዉጡን ከማድነቅ በዘለለ ለዉጡን ለማስቀጠል በተለለያዩ ዘርፎች ሀገሪቱን መደገፍ ያስፈልጋታል።
የጀርመኑ ፕሬዚዳንት  ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ በትብብር ለመስራት ሀገራቸዉ  ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል።በሀገራቸው የሚገኙ ትልልቅ ኩባንያዎች ያላቸውን እምቅ ዕውቀትና ገንዘብ ተጠቅመው በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ፍላጎት ያላቸው  መሆኑንም ጠቁመዋል።ለዚህም ዕሳቸዉ  የሚመሩት የጀርመን የንግድ ማህበረሰብ አባላት በጉብኝቱ እንዲሳተፉ ተደርጓል። ከመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በተጨማሪ  ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮችን የሚፈቱ የጀርመን ተሞክሮዎችን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣትም ሌላዉ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ዶክተር ለማ ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንቱ በዛሬዉ ዕለት ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር ሃገራቱ በምጣኔ ሀብት ላይ በሚኖራቸዉ ሚና እና የጋራ ጥቅም ላይ ተወያይተዋል። ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርም ከንግድና ከኢንቨስትመንት በተጨማሪ በስልጠናና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሀገራቸዉ በትብብርና የምትሰራ መሆኑን የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በዛሬዉ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። 
ለ4 ቀናት በሚዘልቀዉ የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት በቀጣይ ከሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮችና ከታዋቂ ግለሰቦች ጋር የሚወያዩ ሲሆን፥  በአዲስ አበባ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት እንዲሁም በሌሎች ታሪካዊና ሀይማኖታዊ ቦታዎች ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።

Äthiopien Frank-Walter Steinmeier am Addis Ababa Bole International Flughafen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Pedersen
Äthiopien Addis Abeba Nationalpalast | Bundespräsient Frank-Walter Steinmeier & Sahle-Work Zewde, Präsident
ምስል Deutsche Botschaft in Äthiopien

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ