1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሬዝዳንት ኦባማ መልዕክት፦ የኢራን ምርጫ፦ የኔትንያሁ መርሕ

ሰኞ፣ ሰኔ 8 2001

የአሕመዲኒጃድ ወይም የኻሜኒ-ኒትንያሁን ርቀት ለማቀራረብ ይረዳል የተባለዉ የኦባማ መልክትም ከሰወስቱ ልዩነት ጠቦች መሐል እንደሰነቀረ የመቅረቱ ቀቢፀ-ተስፋ መድመቁ ነዉ-የቀረዉ ጊዜ ቁጭት

https://p.dw.com/p/IACY
ኦባማምስል AP

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ለሰላም መቆማቸዉን ለሙስሊሞች፤ በሙስሊሞቹ ሰላማዊ-ቋንቋ-አሰላሙ አለይኩም፣ ከአረብ-ሙስሊማይቱ ሐገር-ግብፅ ቃል በገቡ በሳምንቱ እስላማዊቷ ሪፐብሊክ-ኢራን የአራት አመት መሪዋን በድጋሚ መረጠች።የሙስሊም አክራሪዉ አሕመዲነጃድ ድል በተሰማ-ማግስት የአይሁዳዊቷ ሐገር-አይሁድ አክራሪ መሪ ቤንያሚን ኔታንያሁ የሰላም መርሐቸዉን አወጁ።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።የሰወስቱ መሪዎች-የአንድ ሳምንት ሰወስት ሁነት-የሰወስትም-ሁለትምነት ርቀት-ቅርበት፤ለአለም ሰላም የሚኖረዉ እንድምታ እንዴትነት ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።
« አሰላም አለይኩም)
ፕሬዝዳት ባራክ ሁሴይን ኦባማ።ካይሮ።ዛሬ አስራ-ሁለተኛ ቀኑ።

«ግንኙነታችን በልዩነታችን እስከተበየነ ድረስ ከሰላም ይልቅ ጥላቻን-የሚነዙ ሕዝቦቻችንን ሙሉ ፍትሕና ብልፅግና እንዲያገኙ የሚረዳቸዉን ትብብር ከመመሥረት ይልቅ ግጭትን የሚያበረታቱ ሐይላትን እናጠናክራለን።እና እንዲሕ አይነቱ የጥርጣሬና የጠብ ኡደት ማብቃት አለበት።»

ኦባማ ካይሮ ላይ ያሉትን ከማለታቸዉ ካንድ አመት በፊት ለፕሬዝዳትነት ሲወዳደሩ ከተመረጡ ኑክሌር ቦምብ ለመስራት ታደባለች ከምትባለዉ ኢራን ጋር በቀጥታ እንደራደሩ አስታዉቀዉ ነበር።የእጩ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የሰላማዊ ድርድር እቅድ ኢራንን ከሳዳም ሁሴንዋ ኢራቅና ከሰሜን ኮሪያ ጋር ደብለዉ በዲያቢሎስነት ለፈረጇት ለያኔዉ ፕሬዝዳንት ለጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ የሚያንገሸግሽ መልዕክት ነበር።

«አንዳዶች» አሉ ቡሽ አምና ግንቦት ከአሸባሪ አክራሪዎች ጋር እንድንደራደር ይፈልጋሉ።የኢራኑ መሪ ቀጠሉ ቡሽ እስራኤል ዉስጥ ባደረጉት ንግግር መካከለኛዉ ምሥራቅን ወደ መካከለኛዉ ዘመን የኋሊት ለማዞር የሚያልሙ ናቸዉ።ከሳቸዉ ጋር ድርድር ማለት የናትሲታንኮች ፖላንድ ዉስጥ ሲርመሰመሱ ከናትሴ መሪዎች ጋር እንደራደር እንደማለት ነዉ።

እስራኤልን መጥፋት አለባት እያሉ የሚዝቱት፥ የዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋን በእብሪተኝነት የሚወነጅሉት የኢራኑ ፕሬዝዳት ማሕሙድ አሕመዲኒጃድ እንደ ሐገር መሪ ለሚሉት የማይጠነቀቁ፥ አክራሪ የፖለቲካ መርሕ የሚያጠነጥኑ ፖለቲከኛ መሆናቸዉ በርግጥ ብዙ አያከራክርም።የፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሹ አይነት ዛቻ፥ ዉንጀላ፥ ስድብ ግን የአሕመዲኒጃድን እምነት አስተሳሰብ ከማጠናከር ባለፍ የተከረዉ የለም።

Präsidentschaftswahlen im Iran
አሕመዲኒጃድና ደጋፊዎቻቸዉምስል FARS

ኦባማ ማብቃት አለበት ያሉት የጥርጣሬና የጠብ ኡደት ክረት የዛሬ አራት አመት ከጥንታዊቷ ሐያል፥ ሥልጡን ሐገር ቤተ-መንግሥት የዶላቸዉ አሕመዲኒጃድ ዘንድሮም ድል-አደረጉ።

አርብ-ቴሕራን።የአሕመዲኒጃድ ድል ከታወጀበት ካለፈዉ ቅዳሜ እስከ ትናንት ድረስ የቴሕራን አደባባዮች ባሸናፊና ተሸናፊ ደጋፊዎች ግጭት መታወካቸዉ የምርጫዉን ዉጤት አጠያያቂ ማድረጉ አልቀረም።ለአሕመዲኒጃድ ግን የተቃዋሚ-ደጋፊዎቻቸዉን ሰልፍ-ግጭት የዲሞክራሲያዊ ምርጫ ዉጤት መገለጫ ነዉ።
«ከየትኛዉም ምርጫ በሕዋላ በምርጫዉ ዉጤት ያልተደሰቱ ወገኖች የሚያሰሙት ቅሬታ አለ።አሁን (እኛጋ) የሆነዉም ይኸዉ ነዉ።»

የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች ከሰላሳ አመት በፊት ከስልጣን ባስወገዷቸዉ በሻሁ ዘመን ጠቀም ያለ ገቢ ይዝቁ ከነበሩት ኢራናዊ አባት የምትወለደዉ እዉቅ ጋዜጠኛ ክርስቲያን አማንፑር ባንድ የዝግጅቷ ማስተዋወቂያ እንደምትለዉ እኛ እንደ ሐገራቸዉ ሙላሆች ጥምጣም ሸደር የማያጠልቁት፥እንደ ምዕራቦቹ ኮት ከራቫት የማያዉቁት አጭር መጣጣ ሰዉዬ አለምን በሐይል መግዛት የሚሹ መሪዎች አብነት ናቸዉ።ለፕሬዝዳት ቡሽ ደግሞ የናትሴዎች አምሳያ፥ ለኔትንያሁ የነዉጠኞች ቀንዲል-አሸባሪ፥ ለተቀረዉ አክራሪ።አሕመዲኒጃድ።

ኢራናዊዉ ጋዜጠኛና የፖለቲካ አዋቂ አሊ ሳድርዛዳሕ እንደሚለዉ ግን ኢራን አለምን ለመግዛት፥ እስራኤል ለማጥፋት አቅም ፍላጎቱ ቢኖራት እንኳን አሕመዲኒጃድ ከመናገር ባለፍ ሊያደርጉ፥ ሊሞክሩቅ ቀርቶ ሐገራቸዉን እንኳን ሙሉ በሙሉ ለማስተዳደር ሥልጣን መብቱም የላቸዉም።

«በእስላማዊት ኢራን ሕገ-መንግሥት መሠረት የሐገሪቱ ፕሬዝዳት እዉነኛ ሥልጣን ብዙም የለዉም።የጦር ሐይሉን የማዘዝ፥ምክር ቤቱን ሥራ የመወሰንና የመበተን የዉጪ መርሑን መሥረታዊ አቅጣጫ የመቀየሱን የመሳሰሉ መወሳኝ ሥልጣኖች በሙሉ በአብዮታዊዉ (ላዕላይ ምክር ቤት) መሪዎች እጅ ነዉ። የሐገሪቱ ፕሬዝዳት የበላይ መሪዎቹ እና የእስላማዊቱ ሪፐብሊክ አጠቃላይ ሥርዓት ከሚፈቅዱለት ዉጪ ሌላ ማድረግም መናገርም አይችልም።የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ገደብ ይሕ ነዉ።»

ፕሬዝዳት ኦባማ እንደ ቡሽ ኔትንያሁ አማንፑር በአሕመዲ ኒጃድ ከመነጠል-ይልቅ በጥቅል ኢራን ላይ፥ከዛቻ ዉግዘት ስደብ ይልቅ በድርድር ላይ ማተኮራቸዉ መሠረታዊዉን ችግር ለማስወገድ ይበጃል ነዉ-ያብዙዎች ተስፋ።ግን እራሳቸዉ ኦባማ እንዳመኑት ሰላሳ ዘመን የደፈነዉን የጥላቻ መንፈስ ለማስወገድ ዉይይት ድርድሩ ፈርጆ ብዙ ሊሆን ይገባል።
«በሁለቱ ሐገሮቻችን መካካል ልንደራደርባቸዉ የሚገባቸዉ በርካታ ጉዳዮች አሉ።በነዚሕ ጉዳዮች ላይ በመከባበር ላይ በተመሠረተ መርሕ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁነን።»

ለኦባማ የድርድር ተስፋ እዉነተኛዉን የኢራንን ወሳኝ ሥልጣን የያዙት የሐገሪቱ ላዕላይ መሪ አያቶላሕ አሊ ኻሜኒ የሰጡት አፀፋ በጥያቄ የታጀበ ነበር።በጎ የሚባልም አይደለም።

«አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳት ሥልጣን ከያዙና መናገር ከጀምሩበት ዕለት ጀምሮ ኢራንን እና የእስላማዊት ሪፐብሊክን መንግሥትን ይወቅሳሉ።ለምን?»

ዩናይትድ ስቴትስን በትልቅ ሰይጣንነት-ከሚያወግዙት፥ምዕራቡን በእብሪተኝነት ከሚወነጅሉት አያቶላዎች ከጥያቄ ያላለፈ መልስ መሰማቱ የድርድር ተስፋዉን ባያጠናክረዉ የሚያቀጭጨዉ ግን አይደለም።

የኦባማ መልዕክት በሰወስት ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ ነበር።የአሜሪካና በአሜሪካ የሚወከሉ የምዕራብ-ኢራንን፥የምዕራብ-ሙስሊሞችን ልዩነት ማጥበብ።የፍልስጤም-እስራሎችን ግጭት ጠብ ማስወገድ።ከስልሳ ዘመን በላይ ሥር የሠደደዉ የፍልስጤም-እስራኤሎች ጠብ ከተፈታ ሁለቱ ባይወገድ የሚካረርበት ምክንያት የለም።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት የሰጡት አፀፋ እሰወስትም እሁለትም ለሚቦደነዉ ችግር የመቃለል ፍንጭ አለመሆኑ ነዉ-ሥጋቱ።

«የወታደራዊ ሐይል አልባነትንና የእስራኤልን ደሕንነትን በተመከተ የምንፈልገዉ ዋስትና ከተሰጠን፥እስራኤል የአይሁድ ሕዝብ ሐገር ለመሆንዋ ፍልስጤሞች እዉቅና ከሰጡ፥የጦር ሐይል የሌለዉ የፍልስጤሞች መንግሥት ከእስራኤል ጎን እንዲመሠረት ወደፊት ለሚደረገዉ የሰላም ዉል ዝግጁ እንሆናለን።»

Benjamin Netanjahu 2009
ኔታንያሁምስል AP

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትንያሁ ብዙ በተጠበቀዉ ንግግራቸዉ ብዙ ብለዋል።የፍልስጤም እስራኤሎችን የስልሳ ዘመን ግጭት ጠብ ለማስወገድ፥ በዉጤቱም የምዕራብ ሙስሊሞችን፥ የምዕራብ ኢራኖችን ዉዝግብ ለማርገብ ግን በርግጥ ምንም አላሉም።የአሕመዲኒጃድ ወይም የኻሜኒ-ኒትንያሁን ርቀት ለማቀራረብ ይረዳል የተባለዉ የኦባማ መልክትም ከሰወስቱ ልዩነት ጠቦች መሐል እንደሰነቀረ የመቅረቱ ቀቢፀ-ተስፋ መድመቁ ነዉ-የቀረዉ ጊዜ ቁጭት።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

dw

ነጋሽ መሐመድ/አርያም ተክሌ