1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ DAAD ና የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትብብር፣

ረቡዕ፣ ኅዳር 6 2004

ሃርቫርድ፤ እስታንፈርድ ወይም ኦክስፈርድ፤ የዩናይትድ እስቴትስና የእንግልጣር ዩኒቨርስቲዎች በዓለም አቀፍ የዩኒቨርስቲዎች ተወዳጅነት መመዘኛ መዘርዝር ጥናት መሠረት ቀዳሚውን ቦታ እንደያዙ መሆናቸው የሚታበል አይደለም።

https://p.dw.com/p/Rwsi
ምስል picture alliance/dpa

ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ፤ ጀርመንም ፤ ከግንባር ቀደምቱ ጎን ለመሰለፍ ጥረት ማድረጓ አልቀረም። የመጀመሪያ ዲግሪ ላገኙ ተማሪዎች፤ የትምህርቱን አሰጣጥ በእንግሊዝኛ ለማድረግ የተነሣሱት የጀርመን ዩኒቨርስቲዎች፤ የዶክተርነት ማዕረጋቸውን ለማግኘት በከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል ለሚፈልጉ የውጭ ሀገራት ተማሪዎች ሁኔታዎችን በማመቻቸታቸው ተወዳጅነታቸው እየጨመረ መጥቷል። ይህን ያስታወቀው

በዓለም አቀፍ ደረጃ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችንም ሆነ ተመራማሪዎች፤ የልውውጥ መርኀ-ግብርን በማነቃቃትና ተግባራዊ በማድረግ ወደር እንደሌለው የሚነገርለት፣ ዋና ማዕከሉ በቦን ፤ ጀርመን የሚገኘው የጀርመን የአከደሚ ልውውጥ አገልግሎት--Deutscher Akedemischer Austauschdienst (German Academic Exchange Service)በጀርመንኛው አኅጽሮት DAAD ፣ የጀርመን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በአጠቃላይ የኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች የጋራ ድርጅት ነው። ድርጅቱ፤ ለዓመት፤ ዓመታትም ሆኑ ወራት፤ ለረጅምና ለአጭር ጊዜ ነጻ የትምህርት ዕድል ከመስጠት ባሻገር፤ ፤ በተናጠልም ሆነ በቡድን ትምህርት ነክ ጉዞዎችንና ተግባራዊ የምርምር ሥራዎችን ይደግፋል። በጀርመንና በውጭ ሀገራት ዩኒቨርስቲዎች መካከል የሚደረግ ሳይንሳዊ ምርምርን፣ ፕሮጀክቶችን ፣ ከጀርመን ዩኒቨርስቲዎች ውጭ በሚገኙ የምርምር ተቋማት ለሚከናወኑ ትምህርታዊ ተግባራት ጭምር አስፈላጊ የሆነ ውጪን ሁሉ ጭምር ይሸፍናል። ለውጭ ሀገራት ተማሪዎች፤ በተለይ ዩኒቨርስቲ ለመግባት የሚያስችል በቂ መረጃ ላላቸው ወጣቶች በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ ፣ ነጻ የትምህርት ዕድል የሚሰጥ ሲሆን ፣ በአንዳንድ ረገድም የተወሰኑ ዓመታት በጥናት ላሳለፉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጭምር ነጻ የትምህርት ዕድል የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩ ነው የሚነገረው። በጀርመን ሀገር የምርምር ተግባር ለማከናወንም ሆነ ትምህርትን በሰፊው ለመቀጠል፤ በውጭ ሀገራት በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች የሚገኙ ጀርመናውያን ፕሮፌሰሮችም በዚህ ረገድ ፤ መረጃና ምክር ይሰጣሉ።

እ ጎ አ በ 1925 ዓ ም ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ DAAD ከ 1,5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የአከደሚ ምሁራን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ድጋፍ መስጠቱ ይነገራል። ድርጅቱ፤ የጀርመን ዩኒቨርስቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ ዓለም አቀፍ ገጽ እንዲኖራቸው የሚጥር ነው። ባለፈው 2010 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ብቻ፣ DAAD 74 ሺ ጀርመናውያንና የውጭ ሀገር ተወላጆች የሆኑ ተማሪዎችን ፣ ባሉት ከ 250 በሚበልጡ የትምህርትና ምርምር ዘርፎች እንዲሠማሩ በማድረግ ከመደገፍ አልቦዘነም።

DAAD በዓለም ዙሪያ ከአያሌ አገሮች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ትብብር የሚያደርግ እንደመሆኑ መጠን ፤ በፍሪቃ በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ስላለው ግንኙነት፤ ያስረዱን ዘንድ በጀርመን የአካደሚ ልውውጥ መርኀ ግብር አገልግሎት ፤ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪቃ የጥናት ጽሑፎች አቀራረብ ኀላፊ የሆኑትን Herr Cay Etzold ን አነጋግረናቸው ነበር።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ